ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል 

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝን (COVID-19) ለመከላከል የወጣ መመሪያ

ለጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማውያን፣ ካቶሊካውያን ምእመናን እና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሁሉ!

የእግዚአብሔር ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን!
እኛ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት የኮሮና ወረርሽኝ ዓለምን በማጥቃት እና ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ሀገራችን በመግባት ከፍተኛ ሥጋት መሆኑን ተገንዝበን ለሕዝባችን ደኅንነት በማሰብ ካቶሊክ ቁምስናዎች እና ተቋማት በሙሉ ይህንን መመሪያ ተግባራዊ እንዲያደርጉት አስተላልፈናል፡፡ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና በኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተላለፉ መመሪያዎችን በጥልቀት እየተከታተልን እንገኛለን ተግባራዊ እንዲደረጉም አጥብቀን እናሳስባለን።
ይህ ፈታኝ ወቅት ቢሆንም ቅሉ ራስን በመካድ እና ሌሎችን በማገልገል ክርስቶስን ለመከተል በምናደርገው ተጋድሎ በእውነተኛ ደቀመዝሙርነት እንድንጎለብት የሚያስችለን አጋጣሚ ነው፡፡ እንደ እምነት ሐዋርያነታችንም ይህንን ሥጋት በጸጋ በተቀበልነው ጽናት እና ሩህሩህ ልብ እንጋፈጠዋለን፡፡
የመጀመሪያው ኃላፊነታችንም የኮሮና ቫይረስን በመግታቱ ጥረት ውስጥ እግዚአብሔር ጣልቃ እንዲገባ መጮህ ነው፡፡ በዚህ የዐብይ ጾም ወቅት ሁላችንም በጸሎት እንድንተጋ፣ በጾምም እንድንበረታ እና የፍቅር ሥራችንን እንድንቀጥል እንበረታታለን፡፡ እርዳታችን ወደሚያስፈለጋቸው መድረስ እንድንችል፣ በስቃይ ያሉትን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በፍጹም ፍቅር ማገልገል እንድንችል እግዚአብሔር ልባችንን ይክፈትልን፡፡ እኛም እንደመልካም እረኞች በሥጋት እና በድንጋጤ ለምትገኙት ሕዝቦቻቸን የተስፋ ቃል ይዘን አብረናችሁ መሆናችንን እንገልጻለን፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን ተልዕኮዎች እና በመንግሥት የተላለፉ መመሪያዎችን መሠረት በማድረግ የሚከተሉትን እርምጃዎች ተግባራዊ ማድረግ ይገባናል፦
    1. ቁምስናዎች ተጨማሪ መመሪያ እስከሚተላለፍ ድረስ መደበኛውን የዕለት ተዕለት መሥዋዕተ ቅዳሴ ውስን ቁጥር ባላቸው ምእመናን     ተሳትፎ ብቻ ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን የዕለተ ሰንበት እና የበዓላት ቅዳሴዎችን በተመለከተ በተለይ ሕዝብ በሚበዛባቸው ቁምስናዎች ከአንድ     በላይ ተደጋጋሚ መሥዋዕተ ቅዳሴ ወይንም ለሕዝብ ተደራሽ በሆነ መልኩ ከቤተክርስቲያን ውጪ እንዲያደርጉ ተወስኗል።
    2. ቤተክርስቲያን መጸለይ ለሚፈልጉ ሰዎች ዘወትር ክፍት ይሆናል።
    3. በጳጳሳት ጉባኤ ወይም በሌላ የሚመለከተው የቤተክርሰቲያን አካል ተጨማሪ መመሪያ ካልተላለፈ በስተቀር ማናቸውም ታቅደው የነበሩ     ሱባኤዎች፣ ንግደት፣ ጉባኤዎች፣ ሥልጠናዎች፣ እና ብዙ ሰዎች የሚሳተፉባቸው ስብሰባዎች በሙሉ ታግደዋል።
    4. የቤተክርስቲያን ኃላፊዎች ሐዋርያዊ አገልግሎትን ለማበርከት በመንግሥት የተላለፉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ     የሚያስችሉ አዳዲስ ሃሳቦችን ጭምር በማፍለቅ የመተባበር እና የመደገፍ የሞራል ግዴታ አለባቸው።
    5. ካህናት መሥዋዕተ ቅዳሴ በሚያሳርጉበት፣ ምሥጢረ ጥምቀትን እና መጽሐፈ ቀንዲልን የመሳሰሉ ቅዱሳት ምሥጢራትን በሚያድሉበት     ጊዜ ሁሉ እጆቻቸውን በሳሙና በተደጋጋሚ መታጠብ አለባቸው ይህም በመሥዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ህብስትን በማዘጋጀት የሚሳተፉ፣     ዲያቆናትን፣ ገዳማውያትን እና የሳክርስቲ አገልጋዮችን ሁሉ ይመለከታል። ለቅብዓተ ሜሮን ታቅደው የነበሩ መርሃግብሮች ወደ ሌላ ጊዜ     ይተላለፋሉ።
    6. ምእመናን ቅዱስ ቁርባን በሚቀበሉበት ጊዜ ተገቢው ክብር እና ሥርዓት ሁሉ ተፈጽሞ ቅዱስ ቁርባን ብቻ (ያለ ክቡር ደሙ) ለቆራብያን     በእጃችው ይታደላል፡፡ ቆራብያኑ በካህኑ ፊት እጆቻቸውን አንዱን በሌላው ላይ በመስቀል ምልክት (አመሳቅለው) ይቀርባሉ፡፡ ቅዱስ ቁርባኑን     ከካህኑ በእጃቸው ይቀበላሉ፤ እዚያው በካህኑ ፊት ይቆርቡታል፡፡ ቆሞሳት አስቀድመው ሰለአደራረጉ ለምእመናን ማስረዳት ወይንም     ማብራራት አለባቸው።
    7. እጅ ለእጅ በመጨባበጥ፣ በመሳሳም እና በመተቃቀፍ የሚከናወኑ የሰላምታ ዓይነቶች በማናቸውም ጊዜ አይደረጉም ምእመናን ያለ አካል     ንክኪ የሚፈጸመውን ባህላዊውን ትሁት ሰላምታ እንዲለዋወጡ እንመክራለን።
    8. ቁምስናዎች የጸበል ቤቶችን እና በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙትን ማጥቀሻዎች እንዲዘጉ ውሳኔ የተላለፈ ሲሆን በምትኩ ምእመናን     ቤታቸው ወስደው መጠቀም እንዲችሉ በትንንሽ መያዣዎች እንዲያቀርቡላቸው እንመክራለን።
    9. ቁምስናዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ እና በሰዎች መካከል ተገቢ ርቀት እንዲጠበቅ በማድረግ ካቶሊካውያን በግል ወይንም በትንንሽ ቡድኖች     በቤተክርስቲያን ውስጥ ወይንም በውጭ እንዲጸልዩ እንዲጋብዟቸው ይበረታታሉ።
    10. ምሥጢረ ንሰሃን በከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አሰፈላጊ በመሆኑ መንበረ ንስሃዎችን ከመጠቀም ይልቅ በክፍት ስፍራ ማድረግ ይመከራል፤     እጅ በመጫን ወይንም በመንካት የሚሰጡ ቡራኬዎች ተከልክለዋል።
    11. የቀብር ጸሎተ ፍትሃት ውሱን የሆኑ ሰዎች ብቻ በተገኙበት ይከናወናሉ እንዲሁም ከቤተክርሰቲያን ውጪ በደጀሰላም እንዲደረግ     ይመከራል።
    12. በፍኖተመስቀል፣ በዐርብ ስቅለት ወይንም በሌሎች መርሃግብሮች ላይ መስቀልን የመሳለም ሥርዓት እና በማናቸውም ጊዜ የካህናትን እጅ     ወይንም መስቅላቸውን መሳለም ክልክል ይሆናል።
    13. ማናቸውም ዓይነት ጉንፋን፣ ብርድ ወይም መሰል ምልክቶች የሚሰማቸው ሁሉ በራሳቸው መልካም ፈቃድ እስከሚሻላቸው ድረስ     በቤታቸው እንዲቆዩ እና በመሥዋዕተ ቅዳሴ እንዳይሳተፉ ይመከራሉ።
    14. ቁምስናዎች፣ ገዳማት እና ካቶሊካውያን የጤና ተቋማት የኮሮና ቫይረስ ጸሎት በማዘጋጀት ወረርሺኙን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት     እግዚአብሔር በምሕረቱ ያግዘው ዘንድ ሰለመንጋቸው ደኅንነት እና ሰለታመሙ ሰዎች ፈውስ እንዲለምኑ እንጠይቃለን።
    15. ክርስቲያን ቤተሰቦች ሁሉ በየዕለቱ ምሽት በየቤታቸው በኪዳነምሕረት ፊት የመቁጠሪያ ጸሎት እንዲያደርሱ እንጠይቃለን።
    16. በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስር የሚሠሩ የጤና ተቋማት በሁሉም ደረጃ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እና በትብብር እንዲሠሩ     ይደረጋል።
    17. ተገቢውን ግንዛቤ ለማስጨበጥ፣ ማኅበራዊ እና የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ሕዝባችንን ለማስተማር ጥረት እናደርጋለን።
    18. በአገልግሎቱ ዘርፍ በፊት መስመር ተሰልፈው ለሚገኙ በተለይ ለሀኪሞች፣ ነርሶች፣ የጤና ባለሙያዎች እና የጤና እንክብካቤ ለሚያደርጉ     ሁሉ እንዲሁም ካህናት፣ ወንድም እና እህት መነኮሳት፣ ካቴኪስቶች ደኅንነታቸውን አጋልጠው ለሌሎች አገልግሎት ያቀረቡ በመሆኑ     እግዚአብሔር እንዲጠብቃቸው መጸለይ አለብን።
    19. የመጀመሪያ ትኩረታችን አረጋውያን እና በህክምና ክትትል ስር የሚገኙ ሰዎች መሆን አለባቸው።
    20. ሁሉም የካቶሊክ ትምህርት ተቋማት የዘርዓክህነት ት/ቤቶችን ጨምሮ በመንግሥት ተጨማሪ መመሪያ እስከሚተላለፍ ድረስ ዝግ ሆነው     ይቆያሉ የዐብይ ዘርዓክህነት ተማሪዎች በገዳም ሆነው ጥናታዊ ሥራዎቻቸውን ያከናውናሉ አበ/እመምኔቶቻቸው የመከላከያ ተግባራት     በተገቢው መተግበራቸውን ያረጋግጣሉ።
    21. በካቶሊክ ተቋማት የሚሠሩ ሠራተኞች በሙሉ በቢሮ፣ በመስክ ሥራ፣ ወይንም በሥራ አጋጣሚ ከሚያገኟቸው ሰዎች ጋር በሚኖራቸው     ግንኙነቶች ሁሉ የጥንቃቄ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው ብዙ ሰዎች የሚሳተፉባቸው የሠራተኛም ሆነ የአገልግሎት ተቀባይ     ስብሰባዎች እና ሥልጠናዎች ታግደዋል።
    22. በአረጋውያን፣ በህሙማን እንክብካቤ፣ በህጻናት ማሳደጊያ ማዕከላት የሚሠሩ እና ድጋፍ ለሚያስፈለጋቸው አካል ጉዳተኞች እንክብካቤ     የሚያደርጉ ሰዎች ከሰፊው ህብረተሰብ ጋር ተገናኝተው ወደ እንክብካቤ መስጫ ማዕከላቱ የሚመላለሱ በመሆኑ ተጨማሪ ጥንቃቄ     ያስፈልጋቸዋል በእነዚህ ተቋማት የሚገለገሉ ተገልጋዮች አብረው መሰብሰብ የሚችሉት ቁጥራቸው ከአምስት ካልበለጠ ብቻ ይሆናል     በማዕከላቱ በቂ የንጽህና መጠበቂያ ቀሳቁሶችን ማቅረብ እና ጉንፋን፣ ብርድ እና መሰል ምልክቶችን የሚያሳዩ ሰዎችን ለይቶ ለማቆየት     የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አስፈላጊ ነው።

በመጨረሻም ክርስቲያኖች እና በጎ ፈቃድ ያላቸው በሙሉ እግዚአብሔር የኮሮና ቫይረስን ከምድራችን እንዲያጠፋ ተግተው እንዲጸልዩ ዐደራ እንላለን።

እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታማልደን፡፡

ጸሎት
እጅግ ርኅርኅት የሆንሽ ድንግል ማርያም ሆይ በአንቺ ጥበቃ ከተማጠኑ እርዳታሽንም ከለመኑ አማላጅነትሽንም ከፈለጉ ሰዎች አንድ እንኳ የተኮነነ እንዳልተሰማ አስቢ የድንግሎች ድንግል የሆንሽ እናቴ ሆይ እኔም በዚህ እምነት ተጽናንቼ ወደ አንቺ እሮጣለሁ በኃጢአቴም እየተጨነቅሁ በፊትሽ ቆሜአለሁ፡፡ የቃለግዚአብሔር እናት ሆይ ራርተሽ ቃሌን ስሚ አድምጭኝ እንጂ ችላ አትበይኝ አሜን!

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል
የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ሊቀጳጳሳት
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት
የኢትዮጵያ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ፕሬዝዳንት

ለቡ፡ እነዚህ መመሪያዎች ጊዜያዊ ሲሆኑ እንደአስፈላጊነቱ ማሻሻያዎች ሊደረጉባቸው ይችላሉ።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
18 March 2020, 18:20