ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ በ2016 ዓ.ም በግሪክ ሌስቦስ የሚገኘውን የስደተኞች መጠሊያ ጣቢያ በጎበኙበት ወቅት ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ በ2016 ዓ.ም በግሪክ ሌስቦስ የሚገኘውን የስደተኞች መጠሊያ ጣቢያ በጎበኙበት ወቅት  

በግሪክ ሌስቦስ በመባል በሚጣወቀው ስፍራ የሚኖሩ ስደተኞች ወደ ሌላ ስፍራ እንዲወሰዱ ቤተክርስቲያን ጥሪ ቀረበች!

በግሪክ ከሚገኙ ደሴቶች አንዷ በሆነችው ሌስቦስ በመባል በምትታወቀው ደሴት ላይ በዓለማችን በተለያዩ አከባቢዎች በተካሄዱ እና እየተካሄዱ በሚገኙ አሰቃቂ ጦርነቶችን፣ የአሸባሪ ጥቃቶችን፣ በሐይማኖት ላይ የተቃጣውን ስደት እና መከራ በመሸሽ ከተለያዩ በርካታ አገሮች የተውጣጡ ስደተኞ በደሴቷ ላይ እንደ ሚኖሩ ይታወቃል። ከኢራቅ፣ ከፍጋንስታን፣ ከሶሪያ እና ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ስደተኞች የሚኖሩበት የስደተኞች መጠልያ ጣብያ ሥፍራ ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች በእዚያች ትንሽዬ ደሴት ላይ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እየኖሩ እንደ ሚገኙ ይታወቃል። እነዚህ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ስደተኞ በየአገራቸው በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ያጋጠማቸውን ችግር በመሸሽ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ አውሮፓ አህጉር የተሰደዱ ሲሆን እነርሱ እንዳሰቡት አውሮፓ እጇን ዘርግታ ግን አልተቀበለቻቸውም።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞ ወደ አውሮፓ አህጉር እየተሰደዱ እንደ ሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን የሚታየው ከፍተኛ የስደተኞች ፍልሰት ያስፍራቸው የአውሮፓ ሀገራት በተፈለገው መጠን ስደተኞን ለመቀበል ፍላጎት ባለማሳየታቸው እና በተጨማሪም ይህ የስደተኞ ፍልሰት ከመጠን በላይ ያስፈራቸው አገራት ድንበሮቻቸውን ዝግ በማድረጋቸው የተነሳ እነዚህ በባሕር ወደ አውሮፓ አህጉር ለመግባት የሞከሩ ስደተኞች በእዚህች የግሪክ ደሴት ላይ ለመቆየት ተገደዋል።

እ.አ.አ በሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ይህችን የግሪክ ደሴት የሆነችውንና ጦርነትን እና መከራን በመሸሽ ወደ አውሮፓ እየተሰደዱ ያሉትን ስደተኞች እያስተናገደች የምትገኘውን የሌስቦስ ደሴት በጎበኙት ወቅት ቅዱስነታቸው የሁኔታውን አስከፊነት እና አሳሳቢነት ከተመለከቱ በኋላ “ብዙ ስቃይን ተመልክቻለሁ!” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

በእዚህች የግሪክ ደሴት በሌስቦስ በአሰችጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነ ይኖሩ ከነበሩ ስደተኞች መካከል በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሥራ የሚተዳደረው የቅዱስ ሄጂዲዮ ማህበር በመባል የሚታወቀው የእርዳታ መስጫ ድረጅት ባደረገው ከፍተኛ ጥረት በቅርቡ በርካታ ስደተኞች የጣሊያን ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ሮም መግባታቸው ይታወቃል። ከእነዚህ ስደተኞች መካከል የተወሰኑት በታኅሳስ 08/2012 ዓ.ም የቅዱስ ሄጂዲዮ ማኅበር የበላይ ጠባቂ ከሆኑት ካርዲናል ኮንራድ ክራጅውሲኪ ጋር በመሆን በቫቲካን ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጋር ተገናኝተው እንደ ነበረ ተገልጹዋል።

በታኅሳስ 08/2012 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው ጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ያደረጉትን ሳምንታዊ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አሰተምህሮ ካጠናቀቁ በኋላ የቅዱስ ሄጂዲዮ ማኅበር የበላይ ጠባቂ ከሆኑት ካርዲናል ኮንራድ ክራጅውሲኪ ጋር በመሆን 33 ስደተኞች ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጋር መገናኘታቸው ተገልጹዋል። ከእነዚህ 33 ስደተኞች መካከል 14 የሚሆኑት ለአቅመ አዳም/ሔዋን ያልደረሱ ታዳጊ ሕጻንት የሚገኙበት ሲሆን ዐስር የሚሆኑ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንደ ሚገኙበት ተገልጹዋል።

በሞሪያ ካምፕ የሚገኙት ስደተኞች

ከኮረብታዎቹ አሻግሮ ለሚመለከት ሰው የሞሪያ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ በሌስቦስ ውስጥ ከሚገኙ ደሴቶች መካከል ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚታይበት ስፍር አይመስልም፣ ቀረብ ብሎ ለተመለከተው ግን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ድንኳኖች፣ በላሜራ የተሰሩ ቤቶች፣ ከፍተኛ የሆነ የንጹሕ ውሃ እጥረት የሚታይበት ስፍራ ሲሆን የመብራት አገልግሎት በከፍተኛ ሁኔታ  ማለት በሚቻልበት መልኩ አግልግሎቱ የማይታይበት ስፍራ ነው። ይህ የሞሪያ የስደተኞች መጠልያ ካፕ 14 ሺህ ሰዎች መያዝ የሚችል ሲሆን፣ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ከ 17 ሺህ በላይ ስደተኞች በእዚህ ሞሪያ የስደተኞች መጠልያ ጣቢያ ውስጥ ታጭቀው እንደ ሚኖሩ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል።

እ.አ.አ በሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የግሪክ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ከሆኑት በርቴለሜውስ እና የአቴንስ ሊቀ ጳጳስ ከሆኑት ኤሮንየሙስ ጋር ሆነው የሌስቦስ ደሴት መጎብኘታቸው የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በገለጹበት ወቅት “ስደተኞች በጣም አስከፊ ሊባል በሚችል ሁኔታ ላይ እንደ ሚገኙ” መግለጻቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስለሁኔታው ጨምረው እንደ ገለጹት የግሪክ ደሴት የሆነችሁን ለስቦስ በጎበኙበት ወቅት በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ስደተኞችን መመልከታቸውን መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን ዓለም ሊያገላቸው እና ሊያርቃቸው ቢፈልግም፣ እነርሱን የሚያቀርብ እና መከራቸውን መጋራት የሚችል ለሌላ ኃይል መኖሩንም ጨምረው መግለጻቸው ይታወሳል።

በለስቦስ የስደተኞች የመጠልያ ጣቢያ ውስጥ ከሚገኙ ስደተኞች መካከል “ብዙ ሕጻናት እንደ ሚገኙ፣ ከእነዚህም ሕጻናት አንዳንዶቹ ወላጆቻቸውን እና  ቤተ ዘመዶቻቸውን አስታመው የቀበሩ፣ አንዳንዶቹም ከባሕር አደጋ የተረፉ መሆናቸውን እና በአጠቃላይ ከፍተኛ የሆነ ሐዘን የሰፈረበት ቦታ መሆኑን ለመረዳት ችያለሁ” በማለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስለሁኔታው አስከፊነት መግለጻቸው ይታወሳል።

እ.አ.አ በሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የግሪክ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ከሆኑት በርቴለሜውስ እና የአቴንስ ሊቀ ጳጳስ ከሆኑት ኤሮንየሙስ ጋር ሆነው የለስቦስ የስድተኞች መጠልያ ጣቢያ በጎበኙበት ወቅት ያጋጠማቸውን አንድ ታሪክ ቅዱስነታቸው በወቅቱ ማጋራታቸው የሚታወስ ሲሆን በወቅት ቅዱስነታቸው “በጉብኝቱ ወቅት ያጋጠመኝን አንድ ሰው ታሪክ ባካፍላችሁ ደስ ይለኛል፣ ይህ ሰው የእስልምና እምነት ተከታይ ሲሆን የሚወዳት እና የምትወደው፣ የሚያከብራት እና የምታከብረው ክርስቲያን ሚስት እንደነበረው ገልጾ ነገር ግን ይህች የሚወዳት ሚስቱ እምነቷን እንድትቀይር በአሸባሪዎች በተጠየቀች ጊዜ እንቢ እንዳለች እና ክርስቶስን መካድ እና እምነቷን መለወጥ እንደ ማትፈልግ በመግለጿ ብቻ የተነሳ መታረዷን እያለቀሰ ነግሮኝ ነበር፣ ይህ ድርጊቷ እንደ ሰማዕት ልያስቆጥራት ይችላል” በማለት ስደተኞቹ የተሰደዱበትን አስከፊ የሆነ ምክንያት ቅዱስነታቸው መግለጻቸው ይታወሳል።

በግሪክ በምትገኘው እና ሌስቦስ በመባል በምትታወቀው በእዚህች ደሴት ላይ የሚኖሩ ከተለያዩ አገራት የተውጣቱ ስደተኞች ቀደም ሲል እንደ ገለጽነው በአሁኑ ወቅት የሚገኙበት እና የሚኖርበት ሁኔታ እጅግ በጣም አሳዛኝ እና ኢሰባዊ የሆነ በመሆኑ የተነሳ በአውሮፓ አህጉር ውስጥ ለሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት ጉባሄ የእዚህን ሁኔታ አሳሳቢነት በመረዳት ስደተኞቹ ከእዚህ አሰከፊ የሆነ ስፍራ ወደ ሌላ የአውሮፓ አገራት እንዲዛወሩ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ሦስት ካርዲናሎች በጋራ በአውሮፓ አህጉር ለሚገኙ የካቶሊክ ብጹዕን ጳጳሳት መልእክት ማስተላለፋቸው ተገልጹዋል።

ስደተኞች የሰው ልጆች በመሆናቸው የተነሳ ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ የሚኖሩበት ስፍራ ላይ መኖር እንደ ሚገባቸው የሚገልጸው መልእክት በቀዳሚነት ተፈርሞ የወጣው በአውሮፓ አህጉር ውስጥ በሚገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት ጉባሄ ፕሬዚዳንት በሆኑት ካርዲናል ክላውድ ሆሌርክ፣ በቅድስት መንበር ስር የሚተዳደረውና የተቀናጀ የሰው ሐብት ልማት እና የስደተኞችን ጉዳይ የሚመለከተው ጽሕፈት ቤት ምክትል ጸሐፊ በሆኑት በካርዲናል ሚካሄል ሼርኒ እና እንዲሁም በቅድስት መነበር ሥር የሚተዳደረውና ለቤተክርስቲያን የሚሰጡትን ምጽዋዕቶች የሚቆጣጠረው ጽሐፍት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ካርዲናል ኮርናድ ክራጃዋሲክ ተፈርሞ ይፋ የሆነ መልእክት እንደ ሆነ ከደርሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል።

20 February 2020, 15:22