የነፍሳችን ትልቅነት የነፍሳችን ትልቅነት 

የነፍሳችን ትልቅነት

እኛ ሰዎች ከፍጥረት ሁሉ ከፍ ብለን የምንገኘው በነፍሳችን ምክንያት ነው። ነፍስም ስላለችን ባለ አእምሮዎች የነጻነት ፍላጐት ያላቸው ምርጥ ፍጡራን ልንሆን ቻልን፡፡ በዚህች አስተዋይ ነፍሳችን እግዚአብሔርን እንመስላለን፣ ለዘለዓለም ከእርሱ ጋር እንኖራለን፡፡ ነፍሳችን ያለመጠን ትልቅ ናት፣ ሥጋችን ከአፈር የተሠራች ስትሆን ነፍሳችን ግን ከአምላክ እስትንፋስ የተሰጠችን ናት፡፡ እግዚአብሔር ነፍሳችንን ሲፈጥራት ለእርሱ የምትበቃ ማኀደር አደረጋት፡፡ «እግዚአብሔር ከመንፈሱ በመስጠቱ ከእኛ ጋር እንደሚኖር አወቅን´ (1ኛ ዮሐንስ 4፡13) ይላል ቅዱስ ዮሐንስ፡፡ ቅድስ ጳውሎስ ደግሞ «የእግዚአብሔር ቤተመስደስ አንደመሆናችሁና የእግዚአብሔር መንፈስ በእናነት እንደሚኖር አታውቁምን?” (1ቆሮንጦስ 6፡20) እያለ ስለ ነፍሳችን ትልቅነት ይናገራል፡፡

በእውነት ነፍስ ክቡር ናት፣ ክቡር ስለሆነችም በኃጢአት ስትበላሽ የአምላክ ልጅ ሊያድናት መጣ፡፡ ቅዱስ ደሙንም በማፍሰስ አዳናት፡፡ ክቡር ስለሆነችም አንደገና እንዳትጠፋ ብሎ ምስጢራትን ሠራላት፡፡ ለዘውትር ሊጠብቃት ሊመግባት ብሎ በምስጢረ ቁርባን ከእርሷ ጋር ሊኖር ወሰነ፡፡

«ሰው ክቡር መሆኑ ስላልታወቀው ማስተዋል እንደሌላቸው እንስሳት ሆነ፡፡ ሰው ግን ንጉሥ ሳለ አልታወቀውም በፍቃዱ ራሱን አዋረደ፣ ሊገዙት የማይገቡት ጌቶች ገዙት፡፡ ሰው ግን ሀብትም እንደሆነ አልታወቀውም፣ በፈቃዱ ራሱን ድኻ አደረገ´ የነፍሰችንን ትልቅነት አናውቅም፣ ለዚህች ክቡር ነፍሳችን የሚገባትን ግምት አንሰጣትም፡፡ ክቡር መሆኗን ረስተን አንደ ምንም ነገር እንቆጥራታለን ብዙ ቸል እንላታለን፡፡ ከነፍሳችን ሥጋችንን እንወዳለን፣ እናከብራታለን፣ መጀመሪያ ሥጋችንን በመቀጠልም ነፍሳችንን እንጠብቃን፡፡ ለሥጋችን ስንል ነፍሳችንን እንተዋታለን፡፡ ሥጋችን ከነፍሳችን በላይ ትሆናለች፣ ሥጋችን ተመችቷት ስትኖር ነፍሳችን ግን ትከፋለች፡፡ በዓለም ጉዳይ ተውጠን ነፍሳችንን በኃጢአት እናረክሳታለን፣ ከፈጣሪዋ ከእግዚአብሔር አርቀን በጠላት በሰይጣን እጅ እናስገባታለን፡፡

አንዲት የንጉሥ ልጅ አገልጋይዋ የሚገባትን ክብር ስላጐደለችባት ተሰምቷት «የንጉሥ ልጅ መሆኔን አታውቂም እንዴ?” እያለች ወቀቀሰቻት፡፡ ተገልጋዩዋም ደግሞ «አንቺስ እኔ የሰማያዊው ንጉሥ ልጅ መሆኔን አታውቂም እንዴ?” እያለች መለሰችላት፡፡ ነፍሳችንን ስንረሳትና ስናዋርዳት «የሰማያዊውን ንጉሥ ልጅ የመንግሥቱ ወራሽ መሆኔን አታውቅም እንዴ´ እያለች ሐዘኗን ትገልጽልናለች፡፡ የነፍሳችንን ትልቅነት ያስረዳናል፡፡ እግዚአበሔር ከሁሉም በላይ ክቡር አድርጐ የሰጠንን እርሱ እንደፈለገው አክብረን እንያዛት፣ በጥንቃቄ እንጠብቃት፣ በኃጢአት ቁንጅናዋን ክብሯን አንግፈፋት፡፡

አቅርቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

07 February 2020, 15:43