ተማሪ ከአስተማው፤ አገለጋይም ከጌታው አይበልጥም ተማሪ ከአስተማው፤ አገለጋይም ከጌታው አይበልጥም 

ተማሪ ከአስተማው፤ አገለጋይም ከጌታው አይበልጥም

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያቶቹ በእርሱ ላይ በመጣው ስቃይ ሲደነግጡ ሲያይ «ተማሪ ከአስተማሪው አገልጋይም ከጌታው አይበልጥም´ ተማሪ እንደ አስተማሪው አገልጋይም እንደ ጌታው ከሆነ ይበቃዋል፡፡ የቤቱን ጌታ «ብዔል ዘቡል አለበት ካሉ ቤተሰቦቹንም ከዚህ በከፋ ስም እንዴት አይጠሩዋቸውም; እንግዲህ ሰዎችን አትፍሩ´ (ማቴ. 8፣24-26) እያለ በእርሱ ምክንያት የሚመጣባቸውን መከራ እርሱን አይተው እንዳይደነግጡ በትዕግሥት እንዲቀበሉት አበረታታቸው፡፡

ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከመቀበላቸው በፊት እንደ ሌሎች ሰዎች ሁሉ ስቃይ ያስጠላቸው ያስፈራቸውም ነበር፡፡ ኢየሱስን መከተል ቢወዱም ሕይወቱ ከባድነትና መከራውን ያስደነግጣቸው ነበር፡፡ እንደ ጌታቸውና መምህራቸው በስቃይ ሊያልፉት፣ በሰው ሊጠሉ፣ ሊሰደዱ እስከ ሞት መድረስ አይሰማቸውም ነበር፡፡ ኢየሱስን የሚፈልጉት ያለ ፈተናና ተጋድሎ በቀላል ደስ በሚል መንገድ ነበር፡፡ እርሱም ደግሞ የተሳሳተ ሐሳባቸውን አውቆ አረማቸው፡፡ በእውነት የእርሱ መሆን ከፈለጉ ልክ እንደ እርሱ በጭንቀት እንዲያልፉ መስቀሉን መሸከም የግድ እንደሆነ ነገራቸው፡፡ «እኔ መምህራችሁና ጌታችሁ ከተዋረድኩና ከተሰቃየሁ እናንተ ተማሪዎቼና አገልጋዮቼ ሳትሰቃዩ ልትኖሩ ትፈልጋላችሁ? አስተማሪው እየተሰቃየ ተማሪው የማይሰቃይበት ምክንያት ምንድንነው? ተማሪ ከአስተማሪው ይበልጣል እንዴ? ተማሪ እንደ አስተማሪው አገልጋይ እንደ ጌታ መሰቃየት አለበት እኔን ካሳደዱኝ እናንተንም ደግሞ ያሳድዷችኋል፤ ስለዚህ አትፍሩአቸው´ አላቸው፡፡

እንደ ሐዋርያት እኛም ክርስቶስን መከተል የምንፈልግ ከሆነ ኢየሱስን እንደ መምህራችንና ጌታችን አድርገን እንመልከተው፡፡ ሕይወቱ፣ ቃሉ፣ ተአምራቱ ደስ ይለናል፡፡ መስቀሉን መሸከም ግን ያስጠላናል፡፡ የእርሱ ተከታዮች ለመሆን በችግር ውስጥ እንድንገባ ደቀመዛሙርቱ እንድንሆን በብዙ ፈተና ውስጥ ማለፍን አንፈልግም፡፡ ውርደት፣ ተጋድሎ፣ ስቃይ የሞላበት አኗኗሩ ወደ ኋላ እንድናፈገፍግ ያደርጉናል፣ መዳን እንፈልገለን፣ ግን በደኀንነት መንገድ ላይ የሚያጋጥመን ችግር ይከብደናል፣ የመዳን መንገድ ቀላላ እንዲሆንልን እንፈልጋለን፡፡

ኢየሱስ ስለዚህ እውነታ ሲያረጋግጥልን «ተማሪ ከአስተማሪው አይበልጥም አገልጋይም ከጌታው አይበልጥም´ እያለ ያሳስበናል፡፡ በአንድ ውጊያ ላይ ንጉሡ ከጄነራሉ ጋር ተማርኮ በጠላቱ እጅ ወደቀ፡፡ ሁለቱም ሞት ተፈርዶባቸው በእሳት እየተቃጠሉ ሳለ ጄነራሉ ለንጉሡ «ጌታዬ ሆይ እየተሰቃሁ ነው´ አለው፡፡ ንጉሡም ደግሞ «እኔስ እየተደሰትኩ ያለሁ መሰለህ?´ ሲል መለሰለት፡፡ ክርስቲያን መሆን ደስ የሚለን ከሆነ ክርስቶስን በሕይዋቱ እንከተለው፡፡ እንደ እርሱ መሰቀል ሲከብደን የኢየሱስን ስቃይ እናስታውስ፡፡ እኛ ከመምህራችንና ከጌታችን አንበልጥም፡፡ ስለዚህ እንደ እርሱ ተጋድሎ እናድርግ፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

 

14 February 2020, 16:10