የየካቲት 22/2012 ዓ.ም ስንበት ዘቅድስት የእግዚኣብሔር ቃል አስተንትኖ የየካቲት 22/2012 ዓ.ም ስንበት ዘቅድስት የእግዚኣብሔር ቃል አስተንትኖ 

የየካቲት 22/2012 ዓ.ም ስንበት ዘቅድስት የእግዚኣብሔር ቃል አስተንትኖ

“ስትጾሙ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ እነርሱ መጾማቸው እንዲታወቅላቸው ሆን ብለው በፊታቸው ላይ የሐዘን ምልክት ያሳያሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፤ እንዲህ የሚያደርጉ ዋጋቸውን በሙሉ ተቀብለዋል!“

የእለቱ ምንባባት

1.     1ተሰ.4፡1-12

2.     1ጴጥ 1፡13-25

3.     ሐዋ.ሥ.10፡17-29

4.     ማቴ 6፡16-24

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ስለ ጾም

“ስትጾሙ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ እነርሱ መጾማቸው እንዲታወቅላቸው ሆን ብለው በፊታቸው ላይ የሐዘን ምልክት ያሳያሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፤ እንዲህ የሚያደርጉ ዋጋቸውን በሙሉ ተቀብለዋል። አንተ ግን በምትጾምበት ጊዜ ፊትህን ታጠብ፤ ራስህንም ተቀባ፤ በዚህም መጾምህ በስውር ያለው አባትህ ብቻ የሚያውቀው፣ ከሰዎች ግን የተሰወረ ይሆናል፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል።

ሰማያዊ ሀብት

 “ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በሚችልበት በዚህ ምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ። ነገር ግን ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በማይችልበት በዚያ በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ፤ ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያው ይሆናልና።

“ዐይን የሰውነት መብራት ነው፤ ስለዚህ ዐይንህ ጤናማ ከሆነ መላው ሰውነትህ በብርሃን የተሞላ ይሆናል። ዐይንህ ታማሚ ከሆነ ግን መላው ሰውነትህ በጨለማ የተሞላ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ውስጥ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፣ ጨለማው እንዴት ድቅድቅ ይሆን? “አንድ ሰው ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል፤ ወይም አንዱን አክብሮ ሌላውን ይንቃል። እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም።

የእለቱ አስተንትኖ

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም መልካም ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!  ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘቅድስት የተሰኘውን ሰንበት እናከብራለን፡፡ ዛሬም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሉቃስ አማካኝነት ወደ እያንዳንዳችን ይመጣል፣ በቃሉም አማካኝነት እንዴት እግዚአብሐርን ደስ ማሰኘት እንደሚገባን በቅዱስ ሐዋርየው ጳውሎስ መልእክት አድርጐ ይመክረናል፡፡

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ሲናገር (1ተሰ.4፡1-12) እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው እንድ ነገር ብቻ ነው፣ ይኸውም “ለቅድስና ተጠርተናልና በቅድስና እንድንኖር” ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር የመረጠን ያለ ምንም ነውር በቅድስና እንድኖር መሆኑን በኤፌሶን መልእክት 1፣4 ላይ ይናገራል እንዲህም ይላል “በፊቱ ቅዱሳንና ነውር አልባ እንድንሆን ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ መርጦናል”። “እግዚአብሔር ቅዱስ ነው” ለዚህም ነው መላእክትና ቅዱሳን ዘወትር ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ የሚያመሰግኑትና የሚሰግዱለት፡፡

እግዚአብሔር ታዲያ በእርሱ አምሳል ፍጥሮናል የእርሱ ቅድስናም ተካፋዬች አድርጎናል ስለዚህ ይህንን ቅድስና በሕይወታችን ውስጥ እንድንይዘው በየእለቱ እንድንኖርበት ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር በቅድስና እንድንኖር ሲፈልግ በቅድስና ኑሩ ብቻ ሳይሆን በቅድስና ለመኖር የሚያስችለንን ጸጋ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት አብዝቶ ሰጥቶናል፡፡

ፍጹም ቅድስናና ፍጹም መልካምነት  ከእግዚአብሔር ብቻ ይመነጫል እኛም ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ከሌለን ይህንን ቅድስናና መልካምነት ከየትም ቦታ ልናመጣው አንችልም፡፡ ቅድስናችንን የሚያጐድፈው ነገር አንድ ነው ይኸውም “ኃጢያት” ነው፡፡ኃጢያት ባለበት ቦታ ቅድስና የለም ቅድስና በሌለበት ቦታ ደግሞ እግዚአብሔር የለም፡፡ ስለዚህ ማንኛውንም ዓይነት ኃጢያት ተሸክመን ስንሄድ በቅድስና ጐዳና ላይ እየተመላለስን እንዳልሆነ ልናውቅ ይገባናል፡፡

በምድር ላይ ስንኖር ደግሞ በቅድስና ጐዳና ካልተመላለስን እግዚአብሔርን ማየትም ማግኘትም አንችልም፡፡ ቅዱስ የሆኑ ሰዎች ልባቸው ከኃጢያት የጸዳ ንጹህ የሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡  ልባቸው ንጹህ የሆኑ ሰዎች ብጹዐን ናቸው፣  ይህ በመሆኑም እግዚአብሔርን እንደሚያዩ እግዚአብሔርን እንደሚያገኙ በማቴ. 5፡8 ላይ ተገልጿል፡፡ በዚሁ በተሰሎንቄ መልእክቱ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ምክር የማይቀበል ሁሉ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እንደሚቆራረጥና በዚሁም ምክንያት በእግዚአብሔር ላይ ማመጹን ሊገነዘብ ይገባዋል ይላል፡፡ እኛም ይህ ዕድል ተሰጥቶናል በተሰጠን ዕድል መጠቀሙ ደግሞ የእየንዳንዳችን ኃላፊነት ነው፡፡ ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህንኑ የቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስን ቃል ያጠናክረዋል “የጠራችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ እናንተም ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሆኑ ይለናል”።

ግብረ-ገባዊ ትምህርቶች ሁሉ የተመሰረቱት በእግዚአብሔር ባሕሪ እና በእግዚአብሔር ቅድስና ላይ ነውና እኛም ይህንን ቅድስና እንድንከተል የዛሬው መልእክት ያሳስበናል፡፡ የኛ የክርስቲያኖች እምነት መሠረቱ ዘለዓለማዊ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል እንጂ ሌላ ነገር ሊሆን እንደማይገባው ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ ያሳስበናል፡፡  ምክንያቱም  ምድርና በውስጡዋ ያሉ ሁሉ እንደሚያልፉ የእርሱ ቃልና በእርሱ አምነው ቃሉን የፈፀሙ ሁሉ ደግሞ ለዘለዓለም እንደሚኖሩ ተናግሯል፡፡  ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ በመልእክቱ “ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና ሥሩ ይጠወልጋል  አበባውም ይረግፉል  የጌታ ቃልም ለዘለዓለም ይኖራል” (1ጴጥሮስ 1፡13-25) ይላል፡፡ ይህም ቃል ይህ ጠፊ ለሆነ ዓለም ለጊዜአዊ ደስታና ሃብት ብቻ ፍጹም ተገዢ እንዳንሆን ያስተምረናል።  ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ኃላፊ ነው፣ ከእርሱ ጋር የሆኑት ብቻ በምድርም ሆነ በሰማይ የቅድስና ሕይወት ሊኖሩ ይችላሉ።ወንጌላዊው ማቴዎስም ይህንኑ በመደገፍ ሃብታችንን ብልና ዝገት በማያጠፋው በእግዚአብሔር ዘንድ እንድናከማች ይነግረናል፡፡ ለኛ ለክርስቲያኖች ሃብታቸን ምንድን ነው? ሃብታችን የእግዚአብሔር ቃል ነው፣ ከእግዚአብሔር የወሰድነውን መልካምነት ነው ከእግዚአብሔር የወሰድነውን ቅድስና ነው፡፡

ይህንን መልካምነት በሕይወታችን ከኖርነው ቃሉንም ከጠበቅን በእርግጥም ሃብታችንን በእግዚአብሔር ዘንድ አከማችተናል ማለት እንችላለን፡፡  ምክንያቱም ሃብታችን እርሱ ከሆነ ሃብት ባለበት ቦታ ደግሞ ልብም በዛ ይሆናልና፣ ልባችን በእርሱ ላይ ብቻ ያርፋል ይህም ሁሌ የእርሱን ትእዛዝና ፈቃድ ብቻ እንድንፈፅም ሙሉ በሙሉ እርሱን እንድንከተል ያግዘናል፡፡

እግዚአብሔር በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችን፣ በፍጹም ሐሳባችን፣ በፍጹም ኃይላችን እንጂ በከፊል እንድናገለግለው አልጠራንም፡፡ በአንድ ጊዜ ደግሞ ሰው የእግዚአብሔርንም የገንዘብም ተገዢ ሊሆን እይችልም፡፡ አንዱን ለመምረጥ መንፈሳዊ ዓይናችንን ከፍተን መልካም የሆነውን ነገር ልንመለከትና ልንከተለው ይገባናል፡፡

ሰው በክርስትና ሕይወት ውስጥ እግዚአብሔርን በጽናት ለመከተል እንዲችል ተጋድሎን ማድረግ ያስፈልገዋል፡፡  ተጋድሎአችን ደግሞ በጾምና በጸሎት ሲታገዝ ውጤታማ እንሆናለን፡፡ስለዚህ ጾማችንም ይሁን ጸሎታችን እንደ አይሁዳውያኑ ለታይታ ሳይሆን እግዚአብሔርን የሚያስደስት ለእኛም በረከትን የሚያመጣ መንፈሳዊ ለውጥን የሚያመጣልን ሊሆን ይገባዋል፡፡

“ስትጾሙ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ ለሰዎች እንደ ጾመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል” ይለናል የዛሬው ቅዱስ ወንጌል። ከሰውነት ክፍሎቻችን ውስጥ ፊት ማለት ለሰው ልጅ ብዙ ነገር ነው፣ ፊት ሁሉም የስሜት ህዋሳት የሚገኙበት ክፍል ስለሆነም ከሌሎች ጋር በሚኖረን የግንኙነት ሂደት ውስጥ ብዙ መልእክት ማስተላለፊያ መንገድ ነው። በዘልማድ ንግግራችን ውስጥ እንኳ “ፊት ነሣ’’፣ “ፊቱን አጠቆረ”፣ “ፊቱን ጣለ፣ ዘረገፈ... ስንል በክፉ ዓይን አየ፣ ምንም ቦታ አልሰጠም፣ ተቆጣ፣ አኮረፈና መሰል መልእክት ሲኖረው በአንጻሩ ደግሞ “ፊት ሰጠ” ስንል አቀረበ፣ ጥሩ ሁኔታን አሳየ ማለትን ያሰማል። ከሌላ ሌላም ብዙ አነጋገሮቻችን የፊትን መልእክት ማስተላለፊያነትና የሰውን ውስጣዊ ነገር ማንፀባረቂያነት መረዳት እንችላለን።

በዕለታዊው ውሎዋችን ፈገግታ ለሚያስፈልገው ፈገግታ፣ መኮሳተር ለፈለግንበት ተኮሳትረን፣ ጥርጣሬን፣ ንቀትን፣ ፍቅርን፣ አክብሮትን...ወዘተ በፊታችን ስናድል ውለን ያንኑ ፊት ይዘን ይመሻል። ነግቶ ዳግም ፊታችንን አስተካክለን ይዘን እስክንወጣ ሌሊቱን እንተኛለን። በዚህ ግንዛቤ እይታ ከተመለከትነው ክርስቶስ ፊታችንን እንዴት መጠቀም እንዳለብን መናገሩ አይገርመንም። እርሱ በፊታችን ለሌሎች የምናስተላልፈው መልእክት ጥሩ ይዘት እንዲኖረው በማለት በተለይም በጾም ወቅት እንዴት ሊሆን እንደሚገባው ነገረን “ተቀቡ! ታጠቡ!” አለን።

ፈሪሳውያን በጾም ወቅት በግንባራቸው፣ ጉንጮቻቸው፣ አፍንጫቸውና አገጫቸው ላይ አመድ በመነስነስ ማንም ፊታቸውን አይቶ እገሌ ብሎ መለየት እስኪያዳግተው ድረስ ይለወጡ ነበር። ይህንንም በማድረግ ራሳቸውን የደበቁ ቢመስላቸውም ቅሉ የበለጠ ራሳቸውን በሰው ዓይን እንዲገቡ በማድረግ በጾም ውስጥ መሆናቸውን የሚናገሩበት መንገድ ሆኖ ነበር። በዚህም ሁኔታ ከሰው ዘንድ ስለጿሚነታቸው ሙገሳን ይሸምቱ ነበር። ይህ ሁኔታ የጾምን መሠረታዊ ሃሳብ ስለሚቃወም ክርስቶስ በብርቱ አጽንዖት “እውነት እላችኋለሁ እነርሱ እንዲህ በማድረጋቸው ከሰው ዋጋቸውን ተቀብለዋል እላችኋለሁ” (ማቴ 6፡16) ይለናል።

ክርስቶስ በጾም ወቅት በቅድሚያ  የሚያጎላልን እውነተኛ ፊትን መንከባከብ ያስፈልጋል የሚል ሲሆን ሌላኛው መልእክትስ ምን ይሆን ብለን ማሰብ እንችላለን። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ማንነታችንም ሆነ ገጽታችን ክርስቶሳዊ መሆን አለበት፣ ሕይወታችን የርሱ የሆነውን የፍቅር፣ የትሕትና፣ የትዕግሥት፣ የይቅርታ፣ የመስዋዕትነት... መልእክት ማስተላለፍ አለበት። እግዚአብሔር አብ የልጁን መልክ በእኛ አትሞታል። ይህ መልክ ይበላሽና ይሸፈን ዘንድ የእርሱ ፈቃድ አይደለም። ቅዱስ ጳውሎስም ይህ የክርስቶስ መልክ በውስጣችን በምልአት ይቀረጽ ዘንድ ያሳስበናል። ከማሳሰብም በላይ ምን ያህል በጭንቅ የሚመኝልን ነገር መሆኑን መረዳት እንችላለን “ልጆች ሆይ! ክርስቶስ በእናንተ እስኪሣል ድረስ ዳግመኛ ስለ እናንተ ምጥ ይዞኛል” (ገላ 4:19)።

ምናልባት ሕይወታችን የኢክርስቲያናዊ መልእክት ማለትም የጥላቻ፣ የትእቢት፣ የቁጣ፣ የቂም፣ የቅናት...ማስተላለፊያ ከሆነ ክርስቶሳዊ ማለትም እውነተኛ ገጽታችን/ፊታችን በአመድና በጥላሸት ተሸፍኖ ክርስቶስን አይንጸባርቅም፣ እናም እውነተኛው ክርስቲያናዊ ፊታችን ያንጸባርቅ ዘንድ ፊታችንን መታጠብ ግድ ይለናል። የእግዚአብሔር ቃልን ከልብ ሰምተን እሺ ማለትን እንድንችል፣ ጊዜያዊ የሆነውን ፈቃዳችንን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ለማስገዛት ዝግጁዎች እንድንሆን እምነታችንን በቅድሳት ምሥጢራት መመገብ ይኖርብናል።

በዚህ መንፈስ ሆነን የጾም ወቅትን ለመኖር ከተጋን ለቀጣዩ የክርስትና ሕይወታችን የሚጠቅሙንን ራስን የመቆጣጠርና ራስን የመግዛት ልማድ ለክርስቶስ የተመቸን እንድንሆን ያደርጉናል። እንዳሻን በመሆን ክርስቶስን ማስደሰት የማይቻል ነገር ነውና ከሥጋዊ ነገሮች ጋር የምናደርገው ቁጥባዊነት ስለ ክርስቶስ ብለን ሲሆኑ ትልቅ ትርፍ ይኖራቸዋል፡ ስለዚህም በጾም ወቅት የምናደርጋቸው የጾም ልማዳዊ አካሄዳችንን በመሣሪያነት በመጠቀም ለክርስቶስ ፈቃድ መታዘዝን እንለማመድባቸው፡ በርግጥም ክርስቲያናዊ ገጽታችን ንፁሕና ወዛም የሚሆነው የርሱን ባህርያት መኖርን ስንችል ነውና በፍቅሩ፣ በትሕትናውና በይቅርታው ፊታችን ለሌሎች እንዲያንጸባርቅ እንትጋ!

እግዚአብሔር የሚፈልገው ጾም ደግሞ በትንቢተ ኢሳ. 58 ላይ እንደተጠቀሰው ትሕትናና መልካም ሥራ የታከለበት ጾም እንዲሆን ያስፈልጋል። ይህንንም ለማድረግ እንድንችል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የክርስቲያኖች እናት የሆነችው ታግዘን ጸጋና በረከቱን ከልጇ ታሰጠን፡፡

አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

29 February 2020, 11:51