ኢየሱስ በተወለደ በስምንተኛው ቀን ተገረዘ። ኢየሱስ በተወለደ በስምንተኛው ቀን ተገረዘ። 

ግርዛት

ኢየሱስ ከተወለደ ከስምንት ቀን በኋላ በሙሴ ስርዓት መሰረት ልጃቸውን ለማስገረዝ ወደ ቤተመቅደስ ወሰዱት። ከተወለደ ስምንት ቀን ካለፈው በኋላ ስሙ ኢየሱስ ተስሎ ተጠራ፡፡ ይህ መልአክ ገና ሳይጸነስ የሰጠውና ያወጣለት ስም ነው (ሉቃ. 2፣21) ፡፡ ዕብራውያን የእግዚአብሔር ሕዝቡ እንደመሆናቸውና ከሌሎች የዓለም ሕዝቦች እንዲለያቸው ብሎ ግርዛትን እንደ ምልክት አድርጎ ሰጣቸው። እንግዲህ በግርዛት አማካይነት ሕዝቡ መሆናቸውን አሳወቃቸው። በመጽሐፈ ሌዋውያን በአገልጋዩ በሙሴ በኩል እንደተጻፈው “ሕፃን በስምንተኛው ቀን ይገረዝ” (ዘሌዋውያን 12፡3) ሲል አዘዛቸው፡፡ እግዚብሔር አምላክ ልብህን ግረዘው እንዲሁም የልብህን ሁሉ ይህ ደግሞ በልብህ ሁሉ በነፍስህ እግዚአብሔር አምላክህን እንድታፈቅረው አንተም ብዙ ዘመን እንድትኖር ነው” (ዘዳግም 30፡6) እያለ ተናገራቸው፡፡ እንዲሁም ሕዝቅኤል “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ወንድ የሆነ ልጅ ሥጋውን ያልተገረዘ ወደ ቤተመቅደስ አይግባ፤ እንዲሁም በእስራኤል ልጆች መሐል ያለ የባዕድ ሀገር ተወላጅ” (ሕዝ 45፡9) ይላል፡፡

የእዚህ ዝግጅት  አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ግርዛት ለእስራኤላውያን ከትልልቅ ሥርዓቶች አንዱ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ ምንም እንኳ ግርዛት የማያስፈልገው ቢሆንም ሕግን ለመፈጸመ እንደ ሙሴ ሕግ የግርዛት ሥርዓትን እንደ ማንኛውም ተራ ሕፃን ፈጸመ፡፡ “ሰው ሆነ ያለኃጢአት የሰውን ሥራ ሁሉ ፈጸመ” ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሔር ከሴት የሚወለድ በሕግም የሚሄድ ልጁን ላከው፡፡ የኢየሱስ ግርዛት ሁለት ነገሮችን ያስተምረናል።

1ኛ/ ሕግን ማክበር እንደሚገባን

2ኛ/ መንፈሳዊ ግርዛት ማለት ከኃጢአት መንጻት እንደሚገባን

1. ሕግን ማክበር

ኢየሱስ የብሉይ ኪዳንን ሕግ ለመሻር በደንብ ይችል ነበር ግን አልፈለገም፤ አከበረው እንጂ አልናቀውም፤ ከዚህ የቃል ኪዳን ሕግ አልወጣም፡፡ የማይመለከተኝ ቢሆንም ለአዳም ልጆች ምሳሌና ትምህርት እንዲሆን ልፈጽመው አለና ፈጸመው፡፡ እኔ ኦሪትንና ነቢያትን ለመፈጸም እንጂ ለመሻር ወይም ለማፍረስ አልመጣሁም” (ማቴ. 5፣17) ይል ነበር፡፡ እርሱ አምላክ ከሕግ በላይም ሆኖ እያለ ሁሉን ሕግ ለመፈጸሙ ለእኛ የሕግን አክብሮት ምሳሌ ይሰጠናል፡፡ እኛ ብዙ ጊዜ ደጋግመን በቀላሉ ሕግን እንጥሳለን እናፈርሳለን፡፡ ይህ ሕግ ይህ ሥርዓት የድሮ በመሆኑ ጊዜ ያለፈበት ነው፣ ጥሩ አይደለም፣ አይጠቅምም የማይረባ ስለሆነ ብናፈርሰውና ብንጥሰው ምንም ጉዳት አያመጣም፣ የሚያሰጋ አይደለም በሚል ደካማ መንፈስ ንቀን እንረግጠዋለን፡፡ ባለን አቅም ተግባራዊ እንዳናደርገው ምክንያት በመፍጠር እንሸሻለን፡፡ በደኀንነትና በፍጽምና ጐዳና ወደፊት እንዳንገሰግስ ጠፍሮ የሚይዘንን ስንፍና ማስወገድ ይኖርብናል።

2. መንፈሳዊ ግርዛት የሥጋ ግርዘትን መንፈሳዊነት ማመልከት አለበት፡፡

እግዚአብሔር ለዕብራውያን ከሥጋ ግርዘት ጋር የመንፈስ ግርዘት እንደሚያስፈልግ ያስጠነቅቃቸው ነበር፡፡ “እንግዲህ የልባችሁን እድፍ አስወግዱ ግረዙ፣ እግዚአብሔር ልብህንና የልብህን ዘር ይግረዝ” (ሮሜ 9፡29) የሚል አደራ እናገኛለን፡፡ እግዚብሔር የሕዝቡን ልብ ከኃጢአት ሊገርዝ ሊጠራ ይፈልግ ነበር፤ የልብ ግርዘት የመንፈስ ዕብደትን ማስወገድ ነው፡፡

የመንፈስ ግርዘት በክርስቶስ ተገርዛችህኋል፡፡ “የሕግ ግርዘት በክርስቶስ እንጂ በሰው የተደነገገ አይደለም” ይላል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ቅዱስ አውጉስጢኖስም ደግሞ “ወንድሞቼ ሆይ! እኛ ደኀንነትን ብንፈልግ መገረዝ ያስፈልገናል፡፡ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ብንፈልግ ሥጋችንን መቅጣት ያስፈልገናል” (ቆላ 2፡11) እያለ ይመክረናል፡፡

በመንፈስ ሳንገረዝ ለእግዚአብሔር ብቁዎች ለመሆን አንችልም፡፡ አስራኤላውያን በግርዘት የእግዚብሔር የተመረጠ ሕዝብ ሆኑ፤ ለእርሱ ተሰጡ፡፡ እኛ ከኃጢአት ከተገረዝን ለእግዚብሔር ብቁዎች እንሆናለን፡፡ ልባችን ከክፉ ሐሳብና ምኞት ከነጻ በኋላ በጸጋ ያጌጠ ማኀደረ ስለሚሆን በእርሱ ተደስቶ ያርፋል፡፡ መንፈሳችን ከዓለም በተገረዘ የእግዚብሔር መንፈስ ይሞላልና ሕይወታችን ከፈቃዱ ተስማምቶና ተግባብቶ ይሄዳል፡፡

15 January 2020, 13:10