ብጹዕ ካርዲናል አንቶንዮ ታግለ፣ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ፣ ብጹዕ ካርዲናል አንቶንዮ ታግለ፣ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ፣ 

ካርዲናል አንቶንዮ ታግለ፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች መጸለይ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ።

በቅድስት መንበር፣ ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ እና በፊሊፒን የማኒላ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ በማኒላ ከተማ በተከበረው ዓመታዊ የናዝሬቱ ኢየሱስ ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ ባሰሙት ስብከት፣ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሰላም እንዲወርድ እንጸልይ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በፊሊፒን፣ የማኒላው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ ታኅሳስ 30/2012 ዓ. ም. በብዙ ሽህዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በተገኙበት ዓመታዊ የናዝሬቱ ኢየሱስ ክብረ በዓል ላይ እንደተናገሩት፣ በቅርቡ የኢራን ከፍተኛ የጦር አዛዥ፣ ጄነራል ቃሲም ሱሌይማኒ በአሜሪካ የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውን ተከትሎ በሁለቱ አገሮች፣ በሰሜን አሜሪካ እና በኢራን መካከል እያደገ የመጣውን የጦርነት ስጋት አስታውሰዋል።

በማኒላ ከተማ በሚገኝ የሪዛል መናፈሻ ውስጥ በተካሄደው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እና የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል፣ የዑደት ሥነ ሥርዓት ላይ ለተገኙት ምዕመናን ባሰሙት ንግግር በሁለቱ አገሮች መካከል ጦርነት እንደማይቀሰቀስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው ለዚህም ምዕመናኑ በጸሎት እንዲበረታ አደራ ብለዋል።

በሁለቱ አገሮች ማለትም በኢራን እና በሰሜን አሜሪካ መካከል ውጥረት እያደገ የመጣው፣ ያለፈው ታኅሳስ 24/2012 ዓ. ም. በባግዳድ ከተማ ውስጥ የአሜሪካ ሰው አልባ የጦር አውሮፕላን፣ የመካከለኛውን ምሥራቅ አገሮች በማስተባበር ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው ባሏቸው በኢራኑ ከፍተኛ የጦር አዛዥ በሆኑት በጄነራል ቃሲም ሱሌይማኒ ላይ የግድያ እርምጃ ከፈጸመ በኋላ መሆኑ ታውቋል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ ለምዕመናኑ ባቀረቡት የጸሎት ማሳሰቢያቸው በባሕረ ሰላጤው አካባቢ የተፈጠረው የጦርነት አደጋ ስጋት ወደ ሌሎች አገሮች እንዳይዛመት መጸለይ ያስፈልጋል ብለዋል። በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ውስጥ በሥራ ተሰማርተው የሚገኙትን በርካታ የፊሊፒን ዜጎችን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ ለእነዚህ እና ለሌሎች ዜጎችም ደህንነት መጸለይ ያስፈልጋል በማለት በሥፍራው ለተገኙት ምዕመናን አደራ ብለው በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር ሆነው የሕሊና ጸሎት አድርሰዋል። በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች እያደገ በመጣው የጦርነት ስጋት፣ የፊሊፒን መንግሥት በኢራቅ ከሚገኙ ዘጎቿ መካከል 1,500 የሚሆኑትን ማስወጣቱ ታውቋል።

በፊሊፒን የሰራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ ባወጣው መረጃ መሠረት፣ በሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ከሁለት ሺህ በላይ የፊሊፒን ዜጎች በኢራቅ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጾ ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ በአሜርካ መንግሥት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ መሆናቸውን አስታውቋል። የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በማከልም በኢራን የሚገኙ የፊሊፒን ዜጎች ቁጥር አንድ ሺህ እንደሚደርስ ገልጾ ከእነዚህም አንዳንዶቹ ከኢራናዊያን ጋር በጋብቻ የተሳሰሩ መሆናቸውን ገልጿል። በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ ሥርዓት ላይ በተነበበው፣ በዕለቱ የቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት የማኒላው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ ምዕመናኑ የፍቅር አገልግሎት ተልዕኮን በመፈጸም ኢየሱስ ክርስቶስን መምሰል እንዳለባቸው አሳሰበዋል። “የኢየሱስ ክርስቶስ የሰላም ተልዕኮ የእኛም ነው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ ራሳችንን የአደጋው መንሴ በማድረግ በወንድሞቻችን እና በእህቶቻችን ላይ አደጋን ማስከተል የለብንም ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ በማከልም እውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ የምሕረትን መንገድ የሚከተል መሆን አለበት ብለው፣ የፍቅር ምሳሌነት ከእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ የሚፈልቅ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

በፊሊፒን ውስጥ በየዓመቱ በሚከበረው የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ክብረ በዓል ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምዕመናን እንደሚካፈሉ ሲታወቅ፣ በክብረ በዓሉ ሥነ ሥርዓት ወቅት ምዕመናን በአንድነት ሆነው ቅዱስ መስቀልን በማኒላ  ከተማ ውስጥ ከሚገኝ ኪሪኖ ግራንድስታንድ ጸሎት ቤት ወደ የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ባዚሊካ ድረስ መንፈሳዊ ዑደት በማድረግ የሚያደርሱ መሆኑ ታውቋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ በቅድስት መንበር፣ ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ሆነው ከመሰየማቸው አስቀድመው በፊሊፒን የማኒላ ከተማ ሊቀ ጳጳስ በመሆን ለስምንት ዓመት ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ማበርከታቸው ይታወሳል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
13 January 2020, 17:16