ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ የዛሬ 50 አመት ገደማ ማዕረገ ክህነት በተቀበሉበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ የዛሬ 50 አመት ገደማ ማዕረገ ክህነት በተቀበሉበት ወቅት  

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ 50 ዓመት የክህነት ሕይወት እግዚአብሔርን እና ሕዝቡን ያገለገሉበት ነው።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የክህነት ሕይወት የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት ነገ ታኅሳስ 3/2012 የሚያከብሩ መሆናቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ ሴርጆ ቸንቶፋቲ የላከልን ዘገባ አመልክቷል። በሰላሳ ሦስት ዓመት ዕድሜአቸው የክህነት ማዕረግ የተቀበሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ራሳቸውን ያዘጋጁት የእግዚአብሔርን ምሕረት አውቀው ቆራጥ ውሳኔን ባደረጉበት ወቅት መሆኑን ዘገባው አመልክቷል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የእግዚአብሔር ምሕረት የሚታወስበት ጊዜ ነበር፣

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የክህነት ሕይወት መለኮታዊ ምሕረት የተገለጠበት መሆኑን የሚናገሩት ቅዱስነታቸው ካህናት ያለ ምንም ማመንታት ሕይወታችውን ለአገልግሎት አሳልፈው በሚሰጡበት ጊዜ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳደረገው ሁሉ የደከሙትን ለማገዝ፣ መሪ እንዳጣ መንጋ የተበታተኑትን ለመሰብሰብ ካላቸው ፍላጎት እንደሆነ አስረድተው “እኛ ካህናት ምሕረትን እና ርህራሄን በማድረግ፣ በሕዝቦቻችን መካከል በመገኘት ሁሉንም የምናገለግል፣ የቆሰለንም የምናክም፣ በማህበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ችግሮች ውስጥ የወደቁትን በጽሞና አዳማዳመጥ በማጽናናት እርዳታን የምናቀርብ መሆን አለብን” በማለት የእግዚአብሔር ምሕረት የሚታወስበት ጊዜን ምክንያት በማድረግ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር የካቲት 6/2014 ዓ. ም. ለሮም ከተማ ቁምስናዎች መሪ ካህናት መናገራቸው ይታወሳል።

ካህን ኢየሱስ ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ የቅዱስ ቁርባን ሰው ነው፤

የካህን ሕይወት ማዕከል ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን በመግለጽ ንግግራቸውን ለሮም ከተማ ቁምስናዎች መሪ ካህናት ያሰሙት ቅዱስነታቸው በየዕለቱ ለሚያቀርቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ካህናትን አመስግነው “በዕለታዊ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በኩል የክህነት ማንነታችንን ማወቅ እንችላለን” ብለዋል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን “ይህ መስዋዕት ሆኖ የቀረበ፣ ለእናንተ የሚሰጥ ስጋዬ ነው” በማለት በየቀኑ የክህነት ቃል ኪዳናችንን እናድሳለን ብለዋል። ቅዱስነታቸው ለሮም ከተማ ካቶሊካዊ ቁምስናዎች መሪ ካህናት ባደርጉት ንግግር ካህናቱ በገቡት ቃል ኪዳን በመመራት ለሚያበረክቱት ሐዋርያዊ አገልግሎት ለሌሎችም በርካታ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

የክህነት ሕይወት፣

ካህን ለእግዚአብሔር እና ለሕዝቡ በሚያበረክተው አገልግሎት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ተልዕኮ እንዳለ የገለጹት ቅዱስነታቸው ይህም የሚያገለግለውን ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር ምሕረት ማቅረብ መሆኑን አስረድተዋል። የእግዚአብሔርን ምሕረት ለማስገኘት የሰዎችን ንስሐ በጽሞና፣ በአክብሮት እና በእውነት ማዳመጥ ያስፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው ይህም ምዕመናንን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ የሚያግዝ መንገድ መሆኑን አስረድተዋል። ካህን በመልካም እረኛነቱ ምሕረትን የሚያደርግ፣ ይህን የሚያደርገው በርህራሄ የተሞላ የኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ስላለው ነው በማለት አስረድተዋል።

ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ የሚቀርብ ጸሎት ድልን ያቀዳጃል፤

ካህን የጸሎት ሰው መሆን እንዳለበት ያስረዱት ቅዱስነታቸው ካህን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ባለው የቀረበ ግንኙነት ቸርነቱንም ይማራል ብለው በዚህ በመታገዝ በሕይወቱ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች ማሸነፍ ይችላል ብለዋል። ካህናት ዘወትር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በማስታወስ የመቁጠሪያ ጸሎትን እንዲያቀርቡ አሳስበው ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረታትን ቤተክርስቲያንን ከጥቃት ለመከላከል ያግዛል ብለዋል።

በፈተና ጊዜ ኢየሱስን ያገኙባት የመጀመሪያ ቀን ማስታወስ ያስፈልጋል፣

ካህናትን ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ፈተናዎች መኖራቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፈተና ሲጋጥማቸው ኢየሱስን ያገኟትን የመጀመሪያ ቀን ማስታወስ እንደሚገባ አስታውሰው ያች በብርሃን የደመቀች ቀን፣ ሙሉ ሕይወታቸውን እግዚአብሔርን ለማገልገል መወሰናቸውን የሚያስታውስ መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው የክህነት ሕይወታቸውን በማስታወስ ባሰሙት ንግግራቸው ወደ ወንድሞች እና እህቶች የሚወስዱትን ብርሃን የሚያገኙት ከእግዚአብሔር ዘንድ ካገኙት የአገልግሎት ጸጋ መሆኑን ገልጸዋል።

የካህናት መልካም ድካም፣

ካህናት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ድካም ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተመሳስይ ድካም እርሳቸውንም እንደሚያጋጥም ገልጸው በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል፣ አስቸጋሪ እና አስጊ በሆኑት አካባቢዎች ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን የሚያበረክቱትን በሙሉ በጸሎታቸው የሚያስታውሷቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ካህናት ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ካህናት ሁል ጊዜ በምዕመናኖቻቸው መካከል በመገኘት አገልግሎታቸውን ማበርከት እንዳለባቸው አሳስበው ምዕመናንም ቢሆኑ ካህናቶቻቸውን በፍቅር ይዘው በጸሎት እንዲያግዟቸው አሳስበው ምክንያቱም ካህናት “ሐዋርያዊ እረኞች እንደ መሆናቸው መጠን ምዕመናንን የሚያገለግሉት በእግዚአብሔር ፍቅር ነው” ብለዋል። 

12 December 2019, 11:13