“ክርስቶስ ሕያው ነው” ወጣቶች ለእግዚአብሔር ጥሪ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ተባለ።

በወጣቶች መንፈሳዊ እና ማሕበራዊ ሕይወት ላይ በስፋት የተወያየው የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ከተካሄደ ከአንድ ዓመት ወዲህ ወጣቶች በያሉበት አገር “ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ታውቋል። “ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚለው እና የወጣቶችን ሕይወት በስፋት በሚመለከተው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት ላይ ትኩረት ካደረጉት ወጣቶች መካከል በፈረንሳይ የቴዜ ክርስቲያን ማሕበርሰብ አባል የሆነው ወጣት ሉካ፣ እንደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወጣቶች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም እና ከእርሱ ዘንድ ለሚመጣው ጥሪ መልስ ለመስጠት የተዘጋጁ መሆን ያስፈልጋል ብሏል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ክርስቶስ ሕያው ነው” የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት በቁ. 43 ላይ እንደገለጸው ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል ለሚፈልግ ሁሉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቀዳሚ ምሳሌ መሆኗን ጠቅሷል። በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በኩል የተላከላትን የእግዚአብሔር ጥሪ ስተቀበል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በወጣትነት ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ መሆኗን የ“ክርስቶስ ሕያው ነው” የሚለው ሐዋርያዊ መልዕክት ያስረዳል።

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አዎንታዊ መልስ ድፍረትን የተላበሰ እና ግልጽ እንደነበር የገለጸው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት ማርያም የእግዚአብሔርን ዕቅድ የተረዳች መሆኗን አመልክቷል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ በሐዋርያዊ መልዕክታቸው በኩል “የወጣቶችስ መልስ ምን ሊመስል ይችላል?” በማለት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእሽታ የተቀበለችው ተልዕኮ ቀላል እንደማይሆን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ማርያም አወንታዊ መልስ ከመስጠት በቀር ሌላ ምርጫ አልነበራትም ብለው በዚህም ጥንካሬዋን ገልጻለች ብለዋል።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የልጇን ጭንቀት እና መከራ በቅርብ ሆና ተመክተዋለች ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በመከራ ጉዞ ወቅት እሱን በመከተል ስቃዩንም በልቧ ተጋርታዋለች ብለዋል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለእግዚአብሔር ጥሪ አዎንታዊ መልስ በመስጠት የተስፋ ምንጭ ለመሆን መብቃቷን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በኩል ለእግዚአብሔር ጥሪ ምን ዓይነት መልስ መስጠት እንዳለብን መማር እንችላለን ብለዋል።

ማርያም ለልጇ ጥበቃ እና ከለላ እንደሚያስፈልገው ቀድማ በማወቅ ከዮሴፍ ጋር ሆና ወደ ሩቅ አገር መሰደድን መርጣለች ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሐዋርያት ጋር በጸሎት በመተባበር የመንፈስ ቅዱስን መምጣት ጠብቃለች ብለዋል። መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ሐዋርያቱ ወደ ዓለም ሁሉ በመሄድ የመልካም ዜና አብሳሪዎች ለመሆን እንደበቁ የገለጹት ቅዱስነታቸው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተባባሪነት ቤተክርስቲያን መመስረቷንም አስታውሰዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

    

04 December 2019, 16:33