ሰላም በቤተሰብ መካከል ሰላም በቤተሰብ መካከል 

ሰላም በቤተሰብ መካከል

ሰላም ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ፍጥረታትም የሚሹት የሕይወት ዋስትና ነው። በቤተሰብ መካከል ሰላም ከጠፋ አብሮ መኖር አይቻልም። በጎረቤት መካከል ሰላም ከጠፋ፣ በሕዝቦች መካከል ሰላም ከጠፋ ማሕበራዊ ኑሮ አደጋ ውስጥ ይወድቃል። በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት አይቻል። እርስ በእርስ ሰላማዊ ንግግር ወይም ሰላማዊ ውይይትን ማድረግ አይቻልም። እርስ በእርስ መወያየት እና መነጋገር ካልተቻለ ቤተሰባዊ ወይም ማሕበራዊ ሕይወት ምን ያሕል ሊጎዳ እንደሚችል ማሰብ አስቸጋሪ አይሆንም። ለወንድማማችነት ፍቅር ጥረት ካልተደረገ በሰዎች መካከል ብቻ ሳይሆን ለማዳ እና ለማዳ ባልሆኑ እንስሳት መካከል ሰላም ከጎደለ፣ ጸጥታቸው የሚታወክ ከሆነ ባሕርያቸው ወደ ቁጣ ሲቀየር እናያለን።

የፕሮግራሙ አዘጋጅ እና አቅራቢ ዮሐንስ መኮንን

ሰላምን የተወሰነ ግለሰብ፣ የቤተሰብ ወይም የማሕበረሰብ ክፍል ብቻውን ሊያመጣ አይችልም። ሰላም በገንዘብ የሚገዛ፣ በሃብት የሚለወጥ አይደለም። ሰላም የሚገኘው እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል እና የማሕበረሰብ ክፍል በአስተሳሰቡ፣ በንግግሩ እና በሥራው ትክክለኛነቱ የተረጋገጠለትን ተግባር ሲያከናውን ነው። ጥላቻን የሚቀሰቅስ ንግግር፣ በቀልን የሚመኝ ልብ፣ በሌሎች ላይ ጉዳትን የሚያስከትል ተግባር፣ እነዚህ በሙሉ ቅራኔን፣ አመጽን፣ ጦርነትን እና ጥፋትን እንጂ ሰላምን ሊያስገኙ አይችሉም። በሰዎች መካከል ሰላምን ለማንገስ ከተፈለገ ከሁሉ አስቀድሞ ስብዕናቸው መከበር አለበት።   

በቤተሰብ፣ በማሕበረሰብ፣ በአገር መካከል ሰላም በሚጠፋበት ጊዜ መንስኤው ምን እንደሆነ በጋራ መወያየት ለተፈጠሩት ችግሮች መፍትሄን ለማፈላለግ መልካም መንገድን ይፈጥራል። ወላጆች የልጆቻቸውን መልካም ስነ ምግባር በማነጽ የሚጨወቱት ሚና ከፍተኛ ነው። ልጆቻቸውን በመምከር እና በመገሰጽ ብቻ ሳይሆን መልካም ስነ ምግባርን በሕይወት በመኖር መግለጽ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም በተግባር የማይኖሩትን ስነ ምግባር እንዲህ አድርጉ፣ እንዲህ ሁኑ ብለው ልጆቻቸውን መምከር አይችሉም። ወላጆች የልጆቻቸውን መልካም አስተዳደግ ማየት ከፈለጉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የደስታ፣ የደግነት፣ የበጎነት፣ የታማኝነት፣ የገርነት እና ራስን የመግዛት ምሳሌ ከመሆን ሌላ ምንም ምርጫ የላቸውም። አመጸኛ ልጅ አምጽን የሚማረው ከአምጸኛ ወላጆቹ፣ ከአመጸኛ ዘመድ ወይም በአምጽ ከተሞላ አካባቢ ነው። በጥሩ የቤተሰብ እንክብካቤ እና ፍቅር ያደገ ልጅ ለሌሎች በመጨነቅ ፍቅርን መግለጽ ይችላል። ወላጆች የልጆቻቸውን መልካም ስነ ባሕርይ በመቅረጽ እና በማሳደግ ቀዳሚ ምሳሌ መሆናቸውን መዘንጋት የለባቸውም። 

የቤተሰብን፣ የአካባቢን እና የአገርን ሰላም የሚያውኩ በርካታ የሰላም እንቅፋቶች አሉ። በምንገኝበት የስልጣኔ ዘመን የብዙሃን መገናኛዎች መረጃን እና እውቀትን በማስተላለፍ በባሕል እድገት እና በትምህርት አገልግሎት ትልቅ አስተዋጽዖን በማበርከት ላይ ይገኛሉ። የመገናኛ ቴክኖሎጂ በዳበረ ቁጥር የአገልግሎት ቁጥርም ይጨምራል። የብዙሃን መገናኛዎች ሰላምን በማሳደግ ሰፊ እገዛ አላቸው። ይህ እውን የሚሆነው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሞያዎች ሆነ ግለሰቦች ወገናዊነትን አስወግደው እውነትን የሚመሰክሩ ከሆነ፣ ፍትሃዊ እና ሚዛናዊ መረጃዎችን የሚያዳርሱ ከሆነ ብቻ ነው።    

ክቡራት እና ክቡራን አድማጮቻችን፣ ሰላም በቤተሰብ ውስጥ በሚል አርዕስት የቀረበውን አጭር ዝግጅት በዚህ እንፈጽማለን፤ አብራችሁ በመቆየት ስለተከታተላችሁ ምስጋናችን በያላችሁበይ ይድረሳችሁ እንላለን። በዝግጅታችን ዙሪያ ያላችሁን ሃሳብ ብታካፍሉን ደስ ይለናል አስተያየታችሁንም እንቀበላለን። ሳምንት በሌላ የቤተሰብ ነክ ዝግጅት እስከምንገናኝ ሰላምን፣ ፍቅርን አንድነትን እና ጤናን የምመኝላችሁ የፕሮግራሙ አዘጋጅና አቅራቢ ዮሐንስ መኮንን ነኝ።    

18 November 2019, 09:35