የጥቅምት 30/2012 ዓ.ም ዘጽጌ 5ኛ የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የጥቅምት 30/2012 ዓ.ም ዘጽጌ 5ኛ የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የጥቅምት 30/2012 ዓ.ም ዘጽጌ 5ኛ የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በእለቱ ምንባባት

  1. ቆላ 1፡1-11      
  2. ያዕ 1፡1-12
  3. ግ.ሐዋ.13፡6-15    
  4. ማቴ 6፡25-34

የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል

ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን?  ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፥ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? 

ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው?  ስለ ልብስስ ስለ ምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም።

እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት?  እንግዲህ። ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና።  ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።  ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።

የእለት ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች  እንዲሁም መልካም ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ኣቆጣጠር የዘመነ ጽጌን 5ኛ ሰንበት እናከብራለን። በዚህም እለት መልካም ፈቃዱ ሆኖ በቤቱ ስብሰቦን የቃሉ ተካፋይ እንድንሆን ያደረገን እግዚአብሔር አምላካችን ስሙ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን። በዛሬው ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የሚያስተላልፍልንን መልዕክት ልክ እንደ ወትሮው ሁሉ ወደ ተግባር ለመቀየር እንድንችል ልባችንን ይክፈትልን በቃሉም እንመላለስ ዘንድ መንፈሳችንንም ያነሳሳልን።

ዛሬ በመጀመሪያው ንባብ  ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ ለቆላስያስ ሰዎች በጻፈው መልእክት ውስጥ የቆላስያስ ሰዎች እርስ በርሳቸው ስላላቸው ፍቅር  ስለ እምነታቸው ጠንካራነት ቃሉን በተግባር ለመኖር ስለሚያሳዩት ታታሪነት እግዚአብሔርን ሲያመሰግን ሰምተናል። እነዚህ ሁለቱ መንፈሳዊ እሴቶች ማለትም እምነትና ፍቅር አይነጣጠሉም እውነተኛ  እምነት በፍቅር ይገለጻል እውነተኛ ፍቅርም እንዲሁ ከእውነተኛ እምነት የሚመነጭ ነው ። እግዚአብሔርን የሚወድ ወንድሙንና እህቱን ይወዳል። ለእግዚአብሔር የሚታመን ወንድምና እህቱን ያፈቅራል በእነርሱም ይታመናል። በዐይን የሚታየውን ወንድሙን የሚጠላ በዐይን ያላየውን እግዚአብሔርን ግን እወዳለሁ ወይም አፈቅራለሁ የሚል ሰው  ሐሰት ይናገራል ይላል የመጀመሪያው የዮሐንስ መልእክት 4፡20 ላይ። እግዚአብሔርን መውደዳችን ማረጋገጫው መልካም አስተሳሰባችን ነው መልካም ሥነ ምግባራችን ነው መልካም አካሄዳችን ነው። ምክንያቱም እግዚኣብሔርን የሚወድ ሰው ፍቅር ምን መሆኑን ያውቃል ፍቅር በምን መልኩ እንደሚገለጽ ያውቃል በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ የፍቅር አምላክ የሆነውን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ይመለከታል።

ቅዱስ ሐዋሪያው ያእቆብ በ2፡14-17 መልእክቱ እንዲህ ይላል ወንድሞቼ ሆይ አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል ሥራ ግን ባይኖረው ምን ይጠቅመዋል? እንዲህ ያለው እምነት ሊያድነው ይችላልን?  አንድ ወንድም ወይም አንዲት እኅት የሚለብሱት ልብስም ሆነ የሚመገቡት ምግብ አጥተው ከእናንተ መካከል አንዱ በሰላም ሂዱ አይብረዳችሁ ጥገቡ ቢላቸው ለሰውነታቸው ግን የሚያስፈልጋቸውን ባይሰጣቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንዲሁ ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው ይላል። ስለዚህ እውነተኛ እምነት አለኝ የሚል ሰው ሕይወቱ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል። ዛሬ እያንዳዳችን በውስጣችን ያለው እምነት በየትኛው ኣቅጣጫ እየተጓዘ መሆኑን ለመረዳት የማንንም ኣስተያየት መጠየቅ አያስፈልገንም። ስለ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያለንን ኣመለካከትና ለእነርሱ የምንሰጠው ፍቅር ምን ያህል መሆኑን ሕሊናችንን መፈተሹ ብቻ በቂ ነው። ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ በቆላስያስ የሚኖሩትን ክርስቲያኖች እምነትና ፍቅር በማየት እግዚአብሔርን አመስግኗል ምክንያቱም እነርሱ እምነታቸው ከቀን ወደ ቀን እየጎለበተ ለቅዱሳኑና በመካከላቸውም ያለ ፍቅር ያለ መተሳሰብና መከባበር እጅጉን እየጨመረ የሚተገብሩት በጎ ተግባር ሁሉ ፍሬ እያፈራ በመሄዱ ነው ። ወደ እኛ ህይወት መለስ ብለን ስንመለከትስ  ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ ዛሬ እኛ ባለን እምነትና ፍቅር እግዚአብሔርን ያመሰግን ይሆን? ልክ በቆላስያስ እንደነበሩት ክርስቲያኖች እምነታችን ከቀን ወደ ቀን እያደገ በመካከላችን ያለ ግንኙነት ይበልጡን እየጎለበተ የምናከናውነው መልካም ተግባር ሁሉ አመርቂ ፍሬ እያፈራ ይገኛልን? በእምነታችን ጠንካሮችና እምነታችንንም በተግባር የምናውለው ከሆነ በእርግጥም እግዚአብሔርን ያመሰግናል ፤ በፍቅር የምንኖር ከሆነ እርስ በርሳችን የምንተሳሰብ ከሆነ እግዚአብሔርን ያመሰግናል ፤ መልካምነታችንን ለማጎልበት መልካምና አመርቂ ፍሬ ለማፍራት ዘወትር ያለመታከት የምንጥር ከሆነ እግዚአብሔርን ያመሰግናል ።

ምን አልባት በእምነታችን ጠንካሮች ካልሆንንና ፤ እምነታችንንም በተግባር የማናውለው ከሆነ መልካም ፍሬ ለማፍራት የማንጥር ከሆነ በመካከላችን ያለን መልካም ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የማንተጋ ከሆነ   ዛሬ ነገ ሳንል ለማስተካከል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚገባን ምክሩን ይለግሰናል። በእምነቱ ጠንካራ የሆነ ሰው ፤  እግዚአብሔር በሚሰጠው ጸጋና ኃይል ስለሚመራ ፤ ሕይወቱ ዘወትር የተቀደሰና የተስተካከለ ነው ይህ ደግሞ ለሌሎችም ኣብነትና መንፈሳዊ ኃይል ሰጪ ነገር ነው።

በሁለተኛው ንባብ ፤ ቅዱስ ሐዋሪያው ያዕቆብ በእምነታችን ጠንካሮች መሆን እንዳለብን ያሰምርበታል። በማቴዎስ ወንጌል በ7, 24-27 ላይ ያለውን የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ቃል በአሸዋና በዓለታማ መሠረት ላይ የተሠራውን ቤት እናስተውስ። ዝናብም ወረደ  ፤ ጎርፍም ጎረፈ ፤ ነፋስም ነፈሰ  ያንን ቤት መታው ቤቱ ግን መሠረቱ ዓለት ነበረና ምንም አልሆነም። ነገር ግን ይህንን ቃሌን ሰምቶ በተግባር ላይ የማያውለው ሰው ቤቱን በኣሸዋ ላይ የገነባ ሰነፍ ሰውን ይመስላል ዝናብም ወረደ  ፤ ጎርፍም ጎረፈ ፤ ነፋስም ነፈሰ  ያንን ቤት መታው ቤቱም መሠረቱ አሸዋ ነበረና ወዲያውኑ ወደቀ ኣወዳደቁም እጅግ የከፋ ሆነ። እንግዲህ ከአሁኑ ጀምረን እምነታችን የተመሠረተው በአሸዋ ላይ ይሁን በዓለት ላይ ልብ ልንለው ይገባል። ኣንዳንድ ጊዜ መሠረቱ ዓለት ቢሆንም እንኳን ይህ ዓለት ያለ ምንም ውስጣዊ መሰነጣጠቅና መሸርሸር ጸንቶ መቆሙን መከታተልና እንደየሁኔታው ኣስፈላጊውን ጥገና ልናደርግለት ያስፈልገናል። ኣብዛኛውን ጊዜ በክርስትና ሕይወት ውስጥ ልብ ልንለው የሚገባን ነገር በመንፈሳዊ ኣካሄዳችን ጠንክረን ለመገኘትና ወደፊት ለመጓዝ ስናስብ ብዙ እንቅፋቶችና ጋሬጣዎች ከፊታችን ይደቀናሉ። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን በፍጹም ልባችን በፍጹም ሓሳባችን በፍጹም ኃይላችን ለመከተል ስናስብ  እጅግ በጣም ብዙ ፈተናዎች ሊገጥሙን ይችላሉ የሆነ ሆኖ ግን ሁሉንም በትእግስትና በፅናት የምናልፍ ከሆንን አሸናፊዎቹ እኛ ነን አሸናፊ የሆነ ሰው ደግሞ ሽልማትን ይቀበላል ሽልማቱም በዚህ በምድራዊ ኑሮ መቶ እጥፍና በመጪዉም ደግሞ የዘለዓለማዊ ሕይወትን መውረስ ነው፡፡  በማቴዎስ ወንጌል 24፡13 በማርቆስ ወንጌል 13፡13 እንዲሁም በሉቃስ ወንጌል 21፡19 ላይ እስከ መጨረሻ የሚፀና እርሱ ግን ይድናል በትዕግስታችሁ ዓለምን ታድናላችሁ የሚለውም ይህንኑ ለማመልከት ነው፡፡

ሌላው ቅዱስ ሐዋሪያው ያዕቆብ የሚነግረን ነገር ቢኖር እግዚአብሔርን ስንለምን ወይንም ኣንድ ነገር እንዲፈጽምልን ስንጠይቅ ኣስቀድመን እንደሚያደርግልን ሙሉ በሙሉ እምነታችንን በእርሱ ላይ መጣል ያስፈልጋል፡፡ ሙሉ እምነት የታከለበት ልመና መልሱም እንዲሁ የፈጠነ ነው፡፡ በማቴዎስ ወንጌል 9፡ 27 ጀምሮ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን እነዛ ሁለቱ እውሮች እባክህ ራራልን ብለው ሲጠይቁት ምን ዓይነት መልስ እንደሰጣቸው ይተርካል ይህን ማድረግ እንደምችል ታምናላችሁን? አላቸው እነርሱም አዎ እናምናለን አሉ እርሱም እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ አላቸው ወዲያውኑም ተፈወሱ፡፡ ዛሬም እኛ የምንሻውን ሁሉ በሙሉ እምነት ከጠየቅነው በሙሉ እምነት እንደሚያደርግልን ከተማመንን እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ ይለናል። ስለዚህ በውስጣችን ያለው የእምነታችን ጥንካሬ በሕይወታችን ብዙ ነገሮችን ለመቀየር ዓይነተኛ ሚና ይጫወታልና የእምነታችንን ነገር ችላ ልንለው አይገባም፡፡ ከእግዚኣብሔርና ከወንድም እህቶቻችን ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖረን ከፈለግን ለእግዚኣንሔርም ሆነ ለወንድም እህቶቻችን ያለንን እውነተኛ ፍቅር በተገቢ መልኩ መግለጽ ከፈለግን እንዲሁም ሁልጊዜ መልካም የሆነ ኣስተሳሰብ እንዲኖረን ቀና የሆነ ኣካሄድ እንዲኖረን ከፈለግን በውስጣችን ያለውን እምነት ማሳደግ ይኖርብናል። እግዚኣብሔር ከእኛ የሚጠይቀው የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክል እምነትን እንዲኖረን ብቻ ነው ምክንያቱም የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክል እምነት ቢኖረን ይህንን ታላቅ የሾላ ዛፍ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል ብንለው እንደሚከናወንልን በሉቃስ ወንጌል 17፡6 ላይ ይናገራል።

በዛሬው በማቴዎስ ወንጌል 6፡25-34 ያለው ስለምትበሉትና ስለምትጠጡት ነገር አትጨነቁ ይለናል፡፡ ይህ ማለት ስለ ወደፊት ኑሮአችሁ አታስቡ እቅድ አታውጡ ማለት አይደለም፡፡ ወይንም ደግሞ እጃችንን አጣምረን ተቀምጠን እግዚኣብሔር የሚያደርገውን ተዓምር እንጠባበቅ ማለት ዓይደለም ነገር ግን በሚቻለን ሁሉ እግዚኣብሔር በሰጠን ጸጋና ጥበብ እንዲሁም ዕውቀት እየሠራን እንድንኖር ነው። ለሠራተኛ ደሞዝ የስፈልገዋለና ከምንሠራው ሥራችን ደግሞ የዕለት እንጀራችንን እናገኛለን።

የዛሬ ወንጌል እንደ ምሳሌ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ ብሎ አስቀምጦልናል ፤ እነርሱ እርግጥ ነው አይዘሩም አያጭዱም ፤ሰብስበውም በጎተራ ኣይከቱም ነገር ግን የሰማይ አባታቸው ይመግባቸዋል ይላል እንጂ እግዚኣብሔር የሚበሉትን ጥራጥሬ ከሚኖሩበት ከጎጇቸው ድረስ ሄዶ ያድላቸዋል ኣይልም፡፡ እነዚህ ወፎችም ቢሆኑ የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት እግዚኣብሔር የሚያዘጋጅላቸውን ለመልቀም ከቦታ ቦታ መዘዋወር አለባቸው፡፡

እንዲሁም እኛ በተመሳሳይ መልኩ የእለት ምግባችንን ለማግኘት መትከል  መኮትኮት ውኃ ማጠጣት ያስፈልገናል ፤ እግዚአብሔር በሰጠን በየትኛውም የሥራ መስክ ተሰልፈን ልንሠራ ይገባናል በተገቢ መልኩ እግዚኣብሔር በቸረን ኣቅምና ችሎታ መንቀሳቀስ ያስፈልገናል። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ  ሲናገር ፤ አባቴ ይሠራል እኔም እሠራለሁ ይላል ፤ ሐዋርያቶችም ይሠሩ እንደነበር በተሰሎንቄ መልእክት አይተናል ፤ ስለዚህ እኛም የዕለት ጉርሳችንን ለማግኘት ሥራን መሥራት ግድ ይለናል፡፡ ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ መልአክቱ እንዲህ ሲል ያዛል ፤ ሊሰራ የማይወድ አይብላ ፤ እኛም ሌሊትና ቀን በድካምና በጥረት እየሰራን እንኖር ነበር 2ተሰሎንቄ 3፡10

ብዙውን ጊዜ ሥራ መሥራት በአዳምና በሔዋን ኃጢያት ምክንያት ለሰው ልጅ የተሰጠ እዳ ተደርጎ ሲቆጠር ይስተዋላል ፤ ነገር ግን እውነታው ይህ አይደለም ፤ አዳምና ሔዋን በኤደን ገነት ሥራ ይሰሩ እንደነበር በኦሪት ዘፍጥረት 2፡15 ላይ የገልጻል "እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ማለትም ኣዳምና ሔዋንን ወስዶ ያበጁትም ይጠብቁትም ዘንድ በኤደን ገነት አኖራቸው" ይለናል። ስለዚህ ሥራ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጠው ልዩ ፀጋ ነውና ፤ ሁላችን የየድርሻችንንና የየአቅማችንን እንድንሠራ በላባችንም እንድንበላ ያስፈልጋል።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ የሚያዘን ፤ ጭንቀትን እንድናስወግድና  በቅድሚያ የእግዚአብሔርን ጽድቅ እንድንፈልግ እንጂ ፤  ሥራ ከመሥራት እንድንቆጠብ አይደለም እጃችንን አጣጥፈን እንድንቀመጥና እግዚኣብሔር በተዓምር እንዲመግበን እርሱን ብቻ እንድንጠብቅ አይደለም። እርግጥ ነው እግዚኣብሔር ለሰው ልጅ አእምሮን ሰጥቶታል ስለዚህ በዚህ በተሰጠው አእምሮ ተጠቅሞ ምን ማድረግ እንዳለበትና እንድሌለበት ሊረዳ ያስፈልጋል ተጠያቂነትን መሠረት ባደረገ መልኩ ኃላፊነቱን በሚገባ ሊወጣ ይገባል። እያንዳንዱ ሰው በየዕለቱ ከእግዚኣብሔርና ከወንድም እህቶቹ ጋር ያለውን ግንኙነት በመገምገም ማስተካከል ያለበትን በማስተካከል ቆርጦ መጣል ያልበትን ቆርጦ በመጣል ማሳደግ ያለበትን ይበልጥ በማሳደግ በዕለታዊ ሕይወቱ ደስተኛ ሆኖ እንዲኖር ይገባል። እግዚኣብሔርም በዚህ መልኩ ወደ እርሱ የሚቀርቡትን በሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ ገና ሳይጠይቁት ኣስቀድሞ ያከናውንላቸዋል። የእግዚአብሔር ጸጋ ፤ የእግዚአብሔር ጽድቅ በመካከላችን ካለ የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ ኣስቀድሞ ያውቃልና በሙላት ይሰጠናል። ይህም ደግሞ ካላስፈላጊ ጭንቀትና ውጥረት ይታደገናል። ሰው ከእግዚኣብሔር ጋር በሚኖረው መልካም ግንኙነት እንጂ በራሱ በመጨነቅና በመጠበብ ምንም የሚጨምረው የሚቀይረውም ነገር ኣይኖረዉም።

ምን አልባት ሰው ከመጠን በላይ በመጨነቅ የሚያሻሽለው ነገር ባይኖርም ፤ የሚያባብሰው ነገር ግን አለ ፤ ይኽውም ክፉ ሀሳብን፣ ተስፋ መቁረጥን ብስጭትን ንዴትንና ሃዘንን ይጨምራል። እነዚህ ነገሮች ደግሞ ፤ ሰውን ወደ ኣላስፈላጊ ህመምና ወደ ሞት ይወስዳሉ ፤ በዕለታዊ የኑሮው እንቅስቃሴ ብቻም ሳይሆን በእምነቱም ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ያሳድራሉ። ስለዚህ ከሁሉ ኣስቀድመን የእግዚአብሔርን ጽድቅ በመሻት ከእርሱም በምናገኘው ጸጋ ጭንቀትንና ኣጉል ሓሳብን አስወግደን በተቻለን አቅም ሁሉ በመሥራት ራሳችንንና በዙሪያችን ያሉትን ሁሉ ደስተኛ ኣድርገን እንድንኖር ያስፈልጋል።

ለዚህም የጭንቅ አማላጅ የሆነችው እናታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፤ ከልጇ ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጭንቀታችንን ሁሉ የምናራግፍበትና በእርሱ ብቻ ተመክተን መኖር የምንችልበትን ጸጋን ፣ በረከትን፣ ብርታትንና የእምነት መጠንከርን ከኣንድያ ልጇ ታሰጠን። የሰማነውን በልባችን ያሳድርልን በልባችን ያደረውን ቃል ደግሞ በዕለታዊ ኑሮኣችን ለመተግበር እንድንችል መንፈሳችንን ያነሳሳልን ፡፡

 

09 November 2019, 10:19