“ክርስቶስ ሕያው ነው” የተሰኘው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በሚስዮናዊ ሕይወት እንድካፈል አድርጎኛል!

ከመስከረም 23- ጥቅምት 17/2011 ዓ. ም. ድረስ የዛሬ አንድ አመት ገደማ ማለት ነው በቫቲካን 15ኛው የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ መደበኛ ጉባሄ ተካሂዶ ማለፉ የሚታወቅ ሲሆን የዚህ ጉባሄ ማጠቃለያ ሐሳብ “ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚል አርእስት የተዘጋጀ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በመጋቢት 16/2011 ዓ. ም. በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ተፈርሞ ይፋ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን ይህ ቃለ ምዕዳን በመጋቢት 24/2011 ዓ. ም. በይፋ ለንባብ መብቃቱ ይታወሳል።

ቫቲካን ኒውስ የአማርኛው አገልግሎት- ቫቲካን

ይህ “ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚል አርእስት የተዘጋጀው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ መልኩ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አባላት የሆኑ ወጣቶች እና እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ሁሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚል አርእስት ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ጥሪ በመከተል ለጥሪው ምላሽ በመስጠት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በቤተ-ክርስቲያን ተልዕኮ ውስጥ በመሳተፍ ቅዱስ ወንጌልን ለዓለም በማዳረስ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ በመሆን ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ የሚገኙ ብዙ ወጣት ካቶሊክ ምዕመን ሚስዮናዊያን ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱም ተገልጹዋል።

ከእነዚህም ውስጥ አንዷ የሆነችው ባርባራ የተባለች ወጣት ይህንን በተመለከተ ስትገልጽ “ወጣት ሚሲዮናዊ ምዕመን በመሆን ክርስቶስን በተለያዩ አጋጣሚዎች መመስከር እንደ ሚቻል፣ በገዳም ሕይወት ውስጥ በመሳተፍ ገድማዊ  ወይም ዳማዊት በመሆን ብቻ ሳይሆን ከእነዚህ መዋቅሮች ውጪ በሆነ መልኩ ወጣቶች በተሰማሩበት የሥራ መስክ ሁሉ በሚስዮናዊ ሕይወት የታጀበ ምዕመን መሆን እንደ ሚችሉ” በመግለጽ በእዚህ ረገድ የበኩሉዋን አስተዋጾ በማበርከት ላይ እንደ ምትገኝ እና “ክርስቶስ ሕያው ነው” የተሰኘው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በሚስዮናዊ ሕይወት እንድካፈል አድርጎኛል ማለቷ ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራት ቆይታ መግለጿ ተዘግቡዋል።

በእዚህ “ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚለው የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ውስጥ ወጣቶች በተሰማሩበት የሥራ መስክ ውስጥ በመሆን በጥምቀት የተሰጣቸውን ሚስዮናዊ የመሆን ኃላፊነት በያሉበት ቦታ ሁነው መወጣት እንደ ሚገባቸው የሚያመለክቱ መልእክቶች በስፋት የተነጸባረቁበት ቃለ ምዕዳን መሆኑ ይታወቃል።

ክርስቶስ ሕያው ነው

 “ክርስቶስ ሕያው ነው! እርሱ ተስፋችን ነው፣ በአስደናቂ መንገድ ወጣቶችን ወደ ዓለማችን ያመጣል።” በቅድሚያ ለእያንዳንዱ ክርስትያን ወጣቶች እነዚህን ቃላት ተጠቅሜ እንዲህ ለማለት እፈልጋለሁ፡ ክርስቶስ ሕያው ነው! እናንተም ሕያው እንድትሆኑ ይፈልጋል”። ይህ ቃል “ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚል አርዕስት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በቅርቡ ቅዱስነታቸው በጣሊያን ግዛት ውስጥ የምትገኘውን የሎሬቶ ከተማ በጎበኙበት ወቅት ለወጣቱ እና ለአጠቃላይ የእግዚኣብሔር ሕዝብ ካስተላለፉት መልእክት የተወሰደ ነው።

ይህ “ክርስቶስ ሕያው ነው” የተሰኘው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን 9 ምዕራፎች እና 299 አንቀጾች የተካተቱበት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ሲሆን ይህንን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በተመለከተ ቀድም ሲል ይህ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በሎሬቶ ይፋ በሆነበት ወቅት ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት ይህ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን እ.አ.አ ባለፈው አመት ጥቅምት ወር ላይ “ከተካሄደው ሲኖዶስ የመነሻ ሐሳብ ተወስዶ እና ዳብሮ የቀረበ” ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን መሆኑን በወቅቱ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ምዕራፍ አንድ

“የእግዚአብሔር ቃል ወጣቶች በተመለከተ ምን ይላል?"   

ምዕራፍ አንድ፡ “የእግዚአብሔር ቃል ወጣቶች በተመለከተ ምን ይላል? “ወጣቶች አድገው እስኪበቁ ድረስ ያላቸውን እድሜ እግዚኣብሔር ለየት ባለ መልኩ እንደ ሚመለከተው አንዳንድ ጥቅሶች ያሳያሉ” በማለት ቅዱስነታቸው በአንቀጽ ስድስት ላይ የጠቀሱ ሲሆን ለምሳሌ ያህል ዮሴፍ የቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ የነበረ ሲሆን (ዘፍጥረት 37፡2-3) ነገር ግን እግዚአብሔር በሕልሙ ታላላቅ ነገሮችን አሳየው እናም ዕድሜው ወደ ሀያ ዓመት ገደማ ሲሞላ እጅግ በጣም አስፈላጊ በሆኑት ጉዳዮች ላይ ለወንድሞቹ ማብራሪያ ይሰጥ እንደ ነበር ይገልጻሉ።

በተጨማሪም በጌዴዎን ታሪክ ውስጥ ደግሞ በግልጽ የሚናገሩ ወጣቶችን ሁኔታ እንመለከታለን። ጌታ ከእርሱ ጋር እንደሆነ ሲነግረው ጌዴዎን መልሶ “ጌታዬ ሆይ፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ እንዴት ሊደርስብን ቻለ?” (መሳፍንት 6፡13) ብሎ ለጌታ በግልጽ መልስ ሰጥቶ ነበር። እግዚአብሔር በዚህ ነቀፋ አልተቀየመም ነበር፣ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ወደ እርሱ ዘወር ብሎ፣ ‘ሂድ ባለህ ኀይል እስራኤላውያንን ነጻ እንድ ታወጣ የምልክህ እኔ አይደለሁምን? አለው” (መሳፍንት 6፡14) በማለት በአንቀጽ ሰባት ላይ አስፍረዋል።

በተመሳሳይ መንገድ እግዚኣብሔር ሳሙኤልን የጠራው ገና ትንሽ ልጅ እያለ ነበር። እርሱም የአዋቂዎችን ምክር ሰምቶ የእግዚኣብሔርን ጥሪ ለመስማት ልቡን ከፈተ “ጌታ ሆይ አገልጋይህ ይሰማልና ተናገር” (1 ሳሙኤል 3፡9-10) በማለት እግዚኣብሔርን ለማዳመጥ ያለውን ዝግጁነት ገለጸ። በዚህም አዎናትዊ ምላሽ የተነሳ በአገራቸው ታሪክ ውስጥ አስጨናቂ በተባለ ወቅት ውስጥ ጣልቃ የሚገባ ታላቅ ነቢይ ሆነ። ጌታ ተልዕኮውን እንዲፈጽም ሲጠራው ንጉሥ ሳውል ገና ወጣት ነበር (1 ሳሙኤል 9፡2) አንቀጽ ስምንት ላይ እንደ ተጠቀሰው። ንጉሥ ዳዊት ገና ልጅ ሳለ ነበር የተመረጠው (አንቀጽ 9) ላይ እንደ ተጠቀሰው በማለት እግዚኣብሔር ገና በወጣትነት እድሜ ደረጃ ላይ እያሉ ለልዩ ዓላማ የጠራቸውን ሰዎች እንደ ነበሩ ይገልጻል። ሰለሞን እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ባሪያህ በአባቴ በዳዊት እግር ተተክቼ እንድነግሥ አድርገሃል፤ እኔ ግን ገና ትንሽ ልጅ ስለ ሆንሁ፣ መውጫና መግቢያዬን አላውቅም” (1 ነገሥት 3፡7) በማለት ገና ወጣት መሆኑን በመግለጽ የእግዚአብሔርን ጥበብ ጠይቆ የእርሱን ተልዕኮ ለመፈጸም ግን ዝግጁ እንደ ሆነ መግለጹ ይታወቃል (አንቀጽ 10)። በተመሳሳይም የናማንን እና ወጣት የነበረችሁን የሩትን ታሪክ በመግለጽ በዚህ ዓይነት በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሱትን ወጣቶች በማስታወስ ወደ አዲስ ኪዳን ያመራሉ።

በአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ ደግሞ ወጣቶችን በተመለከተ የተገለጹትን ዋና ዋና ነጥቦች ከአንቀጽ 12 ጀምሮ የዳሰሱ ሲሆን “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ከእነርሱም ታናሹ ልጅ አባቱን፣ ‘አባቴ ሆይ፤ ከሀብትህ ድርሻዬን ስጠኝ’ አለው፤ አባትየውም ሀብቱን ለልጆቹ አካፈላቸው” (ሉቃስ 15፡11-32) በመባል የሚታወቀውን ጠፍቶ የተገኘውን ልጅ ታሪክ ቅዱስነታቸው ማንሳታቸው የተገለጸ ሲሆን በወቅቱ ኢየሱስ ራሱ ወጣት ስለነበረ ወጣት የሆነ ልብ ለዘለአለም ሊሰጠን መፈለጉን ደግሞ በአንቀጽ 13 ውስጥ በስፋት ገልጸዋል። በተጨማሪም “ኢየሱስ ወጣቶችን የሚንቁ ወይም በወጣቶች ላይ የበላይነትን መጎናጸፍ የሚፈልጉትን አዋቂ የሆኑ ሰዎችን እንደ ሚቃወማቸው ማስታወስ ይገባል” በማለት የገልጹ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ “እናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይሁን፤ ይልቁን ከእናንተ ታላቅ የሆነ እንደ ታናሽ፣ ገዥ የሆነም እንደ አገልጋይ ይሁን” (ሉቃስ 22፡26) በማለት ምክረ ሐሳብ ይሰጣል። ለኢየሱስ የእድሜ ባለጸጋ መሆን በራሱ ልዩ የሆነ ክብር የሚያስገኝ ነገር አልነበረውም፣ በተቃራኒው ደግሞ በወጣትነት እድሜ ላይ መገኘት በራሱ ደግሞ ክብር የሚነሳ እና ዝቅተኛ የሚያስብል ነገር እንዳልሆነ በግልጽ የሰፈረበት አንቀጽ ነው (17)።

29 November 2019, 10:49