የተአምረኛ ሜዳሊያ ሐውል አሜሪካ ፍላዴልፊያ የተአምረኛ ሜዳሊያ ሐውል አሜሪካ ፍላዴልፊያ  

የተአምረኛ ሜዳሊያ አጭር ታሪክ

እመቤታችን ማርያም የእግዚኣብሔርን ፍቅር ለመግለጽ የሰው ልጆችን ወደ ንስሐ ለመጥራት በተለያዩ ጊዜያት፣ በተለያዩ ቦታዎች፣ ለተለያዩ ሰዎች በመገለጽ፣ መልዕክቶችን እንደምታስተላልፍ ቤተ-ክርስቲያን በየጊዜው ታስተምረናለች። ሉርድ ማርያም፣ የፋጢማ ማርያም . . . ወዘተ ከፊሎቹ ሲሆኑ ከእነዚህ መገለጾች አንዱ ተአምረኛው ሜዳሊያ ነው። በፈረንሳይ ሀገር በፓሪስ ከተማ ልዩ ስሙ ሩድባክ በመባል በሚታወቀው ሥፍራ የፍቅር ሥራ ልጆች ገዳም አባል ለሆነችው ሲስተር ካትሪን ለምትባል፣ አሁን ቅድስት ካትሪን ብለን ለምንጠራቸው የመንፈሳዊ ሕነጻ ትምህርታቸውን በሚከታተሉበት ወቅት የተሞክሮ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ በነበሩበት ወቅት ማርያም በጸሎት ቤት ውስጥ ተገልጻላቸው ተአምራዊ ሜዳሊያ በመባል የሚታወቀውን ሜድሊያ ሰጠቻቸው።

ካትሪን ላቡሬ እናቷን ገና የ9 ዓመት ሕጻን በነበረችበት ወቅት ያጣች ሲሆን በወቅቱ ከፍተኛ ሐዘን ውስጥ በመግባቷ የተነሳ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እናት እንድትሆናት በልጅነት መንፈስ የተማጸነቻት ሲሆን በሕይወት ሂደቷ በሙሉ የማሪያምን አማላጅነት ትማጸን ነበር።

እ.አ.አ በሐምሌ 18/1830 ዓ.ም የላዛሪስት እና የፍቅር ሥራ ልጆች ማኅበር መሥራች የነበረው የቅዱስ ቪንሰንት ዓመታዊ በዓል በሚከበርበት የዋዜማ ሌሊት ላይ አንድ ትንሽ ልጅ ሲስተር ካትሪንን ከእንቅልፍ ቀስቅሶ ማሪያም ጸሎት ቤት እየጠበቀቻት እንደ ሆነ ነግሯት እንድትከተለው ይጠይቃታል። ካትሪን ስትከተለው ኮሪደሩ ሁሉ በመብራት አሸብርቆ ነበር፣ የጸሎት ቤቱ መብራቶች እና ሻማዎች በሙሉ በርተው ነበር። መንበረ ታቡት አከባቢ በሚገኘው እና ካህኑ የሚቀመጥበት ወንበር አጠገብ እንድትንበረከክ እጻኑ ልጅ ይነግራታል።  ጥቂት ከቆየች በኋላ ማርያም ፀሐይ የመሰለ በሐር የተሰራ ልብስ ለብሳ ፊቷ እንደ ፀሐይ እያበራ ተገለጸችላት፣ ወንበሩ ላይ ተቀምጣም ለሁለት ሰዓታት ያህል አነጋገረቻት። ካትሪንም በማሪያም ጉልበት ላይ እጆቿን አስቀምጣ ለሁለት ሰዓታት ያህል ማሪያምን አዳመጠቻት። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በተገለጸችበት ጊዜ ቅድስት ካትሪን በደስታ እና በትህትና ተመስጣ፣ ካትሪን እጆቿን አጣምራ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጉልበት ላይ አስቀመጠቻቸው። ይህንን ወቅት እና ሁኔታ ካትሪን ስትገልጽ “በሕይወቴ ውስጥ የተከሰተ ጣፋጭ ጊዜ” በማለት ትገልጸዋለች። ማሪያም ስለግል ሕይወቷ እና ከግልጸቱ ጋር ተያይዞ ስለሚደርስባት ተቃውሞ፣ በፈረንሳይ አገር በወቅቱ ስለሚከስተው ረሃብ እና ጦርነት ነግራት ነበር። በእዚህ ማርያም በተገለጸችበት የጸሎት ቤት ውስጥ ማሪያም በወቅቱ ተቀምጣበት የነበረበት ወንበር ዛሬም በእዚያው ይገኛል።

ቀጥሎም እ.አ.አ በኅዳር 27/1830 ዓ.ም የማታ ጸሎት በማደረግ ላይ በነበረችበት ወቅት እንደ ገና ማሪያም ተገለጸችላት። የሐር ልብስ ለብሳ፣ ውበቷን ለመግለጽ ምዳራዊ ቃላት ሊገኝለት በማይችል አኳሗን የእባብ ራስ በእግሮቿ ረግጣ መስቀል የተተከለበት ሉል ይዛ ተገልጻላት “ይህ የያዝኩት ሉል ዓለምን አልፎ እያንዳንዱን ሰው ማዳን የሚችል ነው” በማለት ትገልጽላታለች። የእባቡን ራስ መርገጧ ደግሞ ሰይጣንን የማሸነፊያ ምልክት እንደ ሆነ “በሴቲቱ እና በአንተ መካከል ጠላትነት እንዲኖር አደርጋለሁ፣ የእርሷ ዘር የአንተን ራስ ይቀጠቅጣል” (ኦ. ዘፍ 3፡15) የሚለው ቃል የተፈጸመበት ነው።

ከዚያም በኋላ ሜዳሊያው እንዲታተም ነግራት ምን መምሰል እንዳለበት አሳየቻት። እጇን ስትዘረጋ ከእጆቿ መሃል ብርሃን ይፈነጥቃል፣ ይህም ሜዳሊያ በፊለፊቱ በኩል ማሪያም ቆማ ከእጆቿ በብርሃን አማካይነት ፀጋ የሚፈስበት እና ዙሪያውን ደግሞ “ያለአዳም ኃጢአት የተጸነሰች ማርያም ሆይ ለምኝልን ለእኛ ደጅ ለምንጸናሽ”  የሚል ጽሁፍ ነበረበት። በጀርባው በኩል ደግሞ መስቀልና ከሥሩ ደግሞ ማሪያም በእጆቿ በእሾህ አክሊል የተከበበ የኢየሱስን ልብ እና በሰይፍ የተወጋ የማሪያም ልብ ሆኖ ዙሪያው በ12 ከዋክብት የተከበበ ነበር። “ይህንን ሜዳሊያ ከአንገቱ ላይ ያደረገ ሰው የእኔን ፀጋ ያገኛል” ብላ ማሪያም ለቅድስት ካቴሪና በነገረቻት መሰረት ሜድሊያው ታትሞ በአንገታቸው ላይ ያጠለቁ በሽተኞች በመፈወሳቸው የሀግሬው ሕዝብ ሜዳሊያውን “ተአመኛ ሜዳሊያ” በማለት ሰይሞታል። ከመጀመሪያው “የንፅህት ማርያም ሜዳሊያ” ተብሎ ይጠራ ነበርና ተአምራትና ፈውስን ስላመጣ ተአምራዊው ያለው ህዝቡ ነው፡፡ ተአምረኛነቱ ሲወራለትም ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመሄዱ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሜዳሊያዎች ታትመው ለህዝ በክርስቲያኑ ተሰራጭተዋል፡፡

በወቅቱ ተአምራዊ ተብሎ እንዲጠራ ካደረጉት ታምራት አንዳንዶቹን ለመግለፅ ያህል ወቅቱ በፈረንሳይ ሀገር ማሪያም ለካትሪን የተገለፀችበት ጊዜ የኮሌራ በሽታ የሚከሰትበት ወቅት ነበርና ብዙዎች ከኮሌራ በሽታ ድነዋል፡፡ ለምሳሌ

1.     አንዲት የ8 አመት ልጅ በት/ቤት በክፍል ውስጥ ተአምራዊ ሜዳሊያ በአንገቷ ያልነበራት እሷ ብቻ ነበረችና ኮሌራ ስትያዝ ሜዳሊያ ተደርጎላት ድና በነጋታው ወደ ት/ት ገበታዋ እንደተመለሰች ይነገራል።

2.     አንዲት እርጉዝ ሴት ኮሌራ ተይዛ ትሞታለች ከተባለ በኋላ ሜዳሊያ ተሰጥቷት በአንገቷ ካደረገች በኋላ እንደተፈወሰችና በሰላም ልጇን እንደተገላገለች ይነገራል።

3.     መራመድ ያቃተው ልጅ ሜዳሊያ በአንገቱ ካደረገ በኋላ በመጀመሪያው ቀን ኖቪና መራመድ እንደቻለም ይነገራል፡፡

ከእጇ የሚፈሰው ጨረር ግማሹ የበራ፤ ግማሹ ደግማ ያልበራ ነበርና ለምን እንደተለያየ ካትሪን ስትጠይቃት ማርያምም እንዲህ ስትል መለሰችላት ፡ “የበራው ለምለምኑኝ የምሰጣቸው ነው፤ ያልበራው ደግሞ ሰዎች ስለማይጠይቁኝ የተቀመጠ ነው” በማለት መለሰችላት፡፡

ይህ ከማሪያም እጅ የሚፈሰው ፀጋ ዛሬም ይፈሳል ሁሌም ይፈሳል፡፡ የጠየቋት ሁሉ ፀጋን አግኝተዋል፡፡ ባንገታቸው ሜዳሊያዋን አጥልቀው በሷ ጥበቃ የተማመኑ ሁሉ ጥበቃዋን ተለማምደዋል፡፡ ታዲያ ፀጋውን የሚያገኘው ሁሉ በእምነት በአንገቱ ያጠለቀ እንጂ እምነት ለሌለውማ እንደማነኛውም ሐብል ለሚያንጠለጥል ሁሉ ፀጋው አይፈስም፡፡

ሌላው ከተናገረቻቸው ነገሮች አንዱ ወደ መንበረታቦት ስር ኑ፣ ሁሌ ፀጋ ይፈስበታል ብላለች፡፡ በየቀኑ የልጇ የኢየሱስ ስጋና ደም የሚቀርብበት እንደመሆኑ ፀጋ ሁሌም ይፈሳል፡፡

ይህ ሜዳሊያ በሰው ሃሳብ የተሰራ አይደለም፡ ማርያም ራሷ ነች ዲዛይኑን ያሳየችው፡፡ ለዚህም ነው ፀጋ ሁል ጊዜ በዚህች ሜዳሊያ በኩል የሚፈሰው፡፡

የሜዳሊያውን ትርጉም ከተመለከትን

በፊትለፊቱ በኩል፡

·        ማሪያም ሉል ላይ ማለት ዓለም ላይ ቆማለች የምድርና የሰማይ ንግስት መሆኗን የሚያሳይ ሲሆን  የእባብንም ጭንቅላት በእግሯ ረግጣለች፤ ይህም ሰይጣንን የማሸነፏ ምልክት ነው፡፡ ከልጇ ጋር ሰይጣንን ድል አድርጋለች፡፡ የኛም ጠባቂ መሆንዋን የሚያሳይ ነው፤

·        ከእጇ የሚወርደው ጨረር ለለመኗት ሁሉ የሚተሰጠውን ፀጋ ያሳያል፤

·        በዙሪያው የሚገኘው ያለአዳም ሐጢአት የተፀነስሽ ማሪያም ሆይ፤ ለምኚልን ለኛ ደጅ የምንጠናሽ የሚለው ፀሎት የሁላችን አማላጅ መሆኗን የሚያመለክት ነው

·        እጇን መክፈቷ የእናትነት ምልክት ልትቀበለን ልትታቀፈን መሆኑን የሚያመለክት ነው

 

በጀርባው በኩል፡

·        “መ” ና መስቀል ተጣምሮ ይታያል፡፡ የማርያምንና የኢየሱስን ያለመለያየት፣ መስቀሉ ስር የቆመች መሆንዋን የሚያሳይ ሲሆን ማርያም አማላጃችን መስቀሉ ደግሞ አዳኛችን ነው፡፡

·        በዙሪያው የሚታዩት 12ቱ ኮከቦች 12ቱ የመጀመሪያን ቤ/ክን የመሰረቱትን ሐዋሪያት የሚያመለክት ነው፡፡ ይህ በዮሐንስ ራዕይ ም.12 ቁ 1 ላይ “ፀሐይን የለበሰች፣ ጨረቃን ከእግሯ በታች ያደረገች 12 ኮከቦችን እንደአክሊል በራስዋ ላይ የደፋች…. እንዳለው መሆኑ ነው፡፡

·        በግራ በኩል ያለ በእሾህ አክልል የተከበበ ልበ ኢየሱስ ስለሐጢአታችን የሞተ

·        በቀኝ በኩል ያለ በሰይፍ የተወጋ ልበ ማርያም ለኛ የሚማልድ

·        ከልቦቹ ላይ የሚታዩ ነበልባሎች ልበማርያምና ልበኢየሱስ ስለኛ ፍቅር የሚቃጠሉ መሆናቸውን የሚያሳዩ ናቸው፡፡

ታምራዊው ሜዳሊያ ሲነሳ አብሮት የሚነሳ ስለአንድ አልፎንስ ራትስቦን ስለሚባል አይሁዳዊ ልንገራችሁ፡፡ አልፎንስ በፈረንሳይ ሀገር የተወለደ አይሁዳዊ ሲሆን ሀብታም የህግና የባንክ ባለሙያ ነበር፡፡ ካቶሊክ ቤ/ክንን እጅግ በጣም የሚጠላ ሰው ነበር፡፡ ትዳር ከመመስረቱ በፊት አገር ጎብኝቶ ለመመለስ  አቅዶ ወደሮም ይሄዳል፡፡ የጓደኛው ጓደኛ ስለሞተ ቀብር ለማስተካከል ሰውዬው ካቶሊክ ነበርና  ወደቤ/ክን ከጓደኛው ጋር ይሄዳል፡ ሲሄድም ሳለ ስለካቶሊክ ቤ/ክን መጥፎነት እየተናገረ ሄደ፡፡ ጓደኛው ስለቀብር ሲያስተካክል እሱ እየዞረ ስዕሎችንና የቅዱሳንን ሐውልት እየተመለከተ ሳለ ማርያም ተገለፀችለት፡፡ የተገለጠችለትም የታምረኛው ሜዳሊያ  ማርያም ነበረች፡፡ አልፎንስ ደነገጠ፣ ተንበርክኮም አለቀሰ፡፡

ጓደኛውም ተንበርክኮ ሲያገኘው አልፎንስም እንዲህ አለ፡ ቤ/ክን ውስጥ ትንሽ እንደቆየሁ የሆነ ነገር ተሰማኝ፤ ቀና ብዩ ሲመለከት የነበርኩበት ቤቱ ራሱ ተነስቶ የሄደ መሰለኝ፤ ወደአንድ በኩል ብቻ መብራት ተሰበሰበ፤ በዚህ በአስደናቂ ሁኔታ በሸበረቀ መብራት ውስጥ ማርያም መንበረታቦቱ ላይ ቆመች፡፡ አሷም በግርማ የተሞላች የሚያምር ብርሃን የለበሰች ልክ ታምረኛው ሜዳሊያ ላይ ያለችን ትመስል ነበር፡፡ አሷም ተመለከተችኝና እንዲንበረከክ በምልክት ጠየቀችኝ፡፡ እሷ አላወራችም እኔ ግን ሁሉ ገባኝ አለ፡፡  አልፎንስ ተጠምቆ ካቶሊክ ሆነ፡፡ የማርያምን ገድልም መሰከረ፡፡ ያቀደውን ሁሉ ትቶ ገዳም ገብቶ ቄስ ሆኖ አይሁዳዊያንን ወደ ክርስትና ኃይማኖት ለመመለስ ዕድሜ ልኩን ሰበከላቸው፣ ቤተክርስቲያንንም አገለገለ፡፡

እንግዲህ ለማጠቃለል ያህል የማሪያምን አማላጅነት መጠየቅ ልክ ሽቦ አልባ ስልክ እንደመደወል ነው፡፡ ስልክ ያስከፍላል፡ ማርያምን ፀጋ እንዲትሰጠን መለመን ዋጋ አያስከፍልም፤ ኔትወርክ ሁሌም ክፍት ነው፡፡

በመተማመን ሜዳሊያን በአንገቱ ያጠለቀ ሁሉ ፀጋን ያገኛል ያለች ማርያም ትንሹን እምነታችንን ተቀብላ በአማላጅነቷ ይህንኑ ፀጋ አብዝታ እንዲትሰጠን ምኞቴም ፀሎትም ነው፡፡

የእመቤታችን አማላጅነትና ረደኤት አይለየ

27 November 2019, 15:59