ወጣቶች በመንፈሳዊ ጉዞአቸው ላይ፣ (ቴዜ) ወጣቶች በመንፈሳዊ ጉዞአቸው ላይ፣ (ቴዜ) 

የአብያተ ክርስቲያናት ወጣቶች መንፈሳዊ ጉባኤያቸውን በኬፕ ታውን በማካሄድ ላይ መሆናቸው ተገለጸ።

ከተለያዩ የአፍሪቃ አገሮች ተነስተው መንፈሳዊ ጉዞአቸውን (ንግደታቸውን) ወደ ደቡብ አፍሪቃ ያደረጉት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በኬፕ ታውን ከተማ መንፈሳዊ ጉባኤያቸውን በማድረግ ላይ መሆናቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቋል።  ከመስከረም 14/2012 ዓ. ም. ጀምሮ ለአምስት ቀናት የሚካሄደውን ይህን ጉባኤ ያስተባበረው ጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱን በፈረንሳይ፣ ቴዜ ከተማ ያደረገ የልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ማህበረሰብ መሆኑ ታውቋል።

 የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ይህን መንፈሳዊ ጉባኤ ለመካፈል ወደ ሥፍራው የተጓዙት ወጣቶች በማዳጋስካር፣ በኡጋንዳ፣ በታንዛኒያ እና በአይቮሪ ኮስት የሚገኙ የልዩ ልዩ እምነቶች ተከታዮች መሆናቸው ታውቋል። የቴዜ ማህበረሰብ የተቋቋመበት ዋና ዓላማም በአብያተ ክርስቲያናት መካከል የሚንጸባረቁ ልዩነቶችን ወደ ጎን በማድረግ፣ በቅዱስ ወንጌል በመመራት፣ የሕብረት ጸሎትንና ሱባኤን እያዘወተሩ ለአንድነት ለመትጋት እንደሆነ ታውቋል። ማህበሩ በተጨማሪ የልዩ ልዩ እምነት ተከታዮች፣ በየትኛውም የዓለማችን ክፍሎች ሆነው በሚኖሩበት አካባቢ በቡድን ይሁን በግል እንዲገናኙ፣ እንዲነጋገሩ፣ እንዲሰሩ እና እንዲጸልዩ የሚረዳ እና የሚያስተባብር መሆኑ ታውቋል። የከዚህ በፊትም በዛግረብ፣ በሳሪዬቮ፣ በቮሊቪያ ከተማ በሆነችው ኮቻባምባ እና በናይሮቢ የተካሄዱት መንፈሳዊ ጉባኤዎች በጦርነት ውስጥ የገቡ የሁለት ጠላት አገሮች ወጣቶችን በማገናኘት፣ በመካከላቸው የነበሩ ፍርሃቶችን፣ መሰናክሎችን፣ ጭንቀቶችን፣ ጭፍን ጥላቻዎችን እና ቂሞችን በማስወገድ  ሰላማዊ የወዳጅነት መስተንግዶን የተደረገበት መሆኑ ታውቋል።          

በደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የሚከሰተው አመጽ ለርጅም ዓመታት ያህል አብረው ኖረው፣ አብረው ሰርተው በኖሩት የአንድ አህጉር ወንድም እና እህት በሆኑ ሰዎች መካከል ጥላቻን፣ ሞትን፣ መቁሰልን እና ንብረት መውደምን ማስከተሉ የሚታወስ ሲሆን የቴዜ ማሕበረሰብም እነዚህ ማሕበራዊ ችግሮች በሚታዩባቸው አካባቢዎች በመሄድ በሕዝቦች መካከል እርቅን እና ሰላምን ለመፍጠር የሚጥር መሆኑ ታውቋል። በደቡብ አፍሪቃ ከተማ በሆነችው ኬፕ ታውን ከመስከረም 14-18 ቀን 2012 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄደው መንፈሳዊ ጉባኤ ዓላማ በሥራ ምክንያት በዚያች አገር ውስጥ በሚገኙ የውጭ አገር ዜጎች እና በአገሩ ዜጎች መካከል የተፈጠረውን የጥል እና የልዩነት ግድግዳን በማፍረስ፣ እርስ በእርስ በመተጋገዝ፣ በሰላም አብረው በመኖር፣ ተስፋቸውን እና እምነታቸውን እየተጋሩ የጋራ ጸሎታቸውን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ማቅረብ እንዲችሉ ለማድረግ መሆኑ ታውቋል።

ስብሰባው የተስፋ ጥሪ ነው፣

በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ወደ ደቡብ አፍሪቃ እንዲጓዙ ያደረገው ይህ ጉባኤ ከመንፈሳዊ ጉዞ ባሻገር አብያተ ክርስቲያናትን እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን በማሳተፍ፣ በኬፕ ታውን የተካሄደውን መሰል መንፈሳዊ ጉባኤን በየአገሮቻቸው እንዲያዘጋጁ የጋበዘ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተባባሪ ኮሚቴ ከሥፍራው እንዳስታወቀው በጉባኤው እንዲገኙ የተጋበዙት የልዩ ልዩ ሕይማኖት ተቋማት መሪዎችም በደቡብ አፍሪቃ የአንግሊካን ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ታቦ ማክጎባ፣ የኬፕ ታውን ከተማ ካቶሊካዊ ሊቀ ጳጳሳ ብጹዕ አቡነ ስቲፈን ብሪስሊን፣ የደቡብ አፍሪቃ ሜቶዲስት ቤተክርስቲያን ጳጳስ እና የአብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ብጹዕ አቡነ ሲዋ፣ እና የኔዘርላንድስ ተሃድሶ ቤተክርስቲያን ተወካይ ክቡር ዶክተር ጉስታቭ ክላሰን መሆናቸውን አስታውቋል።

በመርሃ ግብሩ መሠረት የጉባኤው ተካፋዮች በየዕለቱ በሚከናወኑ የጋራ ጸሎቶች የሚሳተፉ፣ በከተማው የሚገኙትን የልዩ ልዩ እምነቶች ቁምስናዎች እና ክርስቲያን ቤተሰቦችን ጎብኝተው አብሯቸው የጋራ ጸሎት የሚያደርጉ መሆናቸውን አስታውቋል። በከተማው የሚገኙት የልዩ ልዩ እምነት ተከታይ ቤተሰቦች በጉባኤው ቀናት ወጣቶችን በእንግድነት ተቀብለው በቤታቸው የሚያሳድሩ መሆናቸው ታውቋል። ወጣቶች በቀን ያደረጉትን ጉብኝት ፈጽመው ወደ ማታ ገደማ ወድ ጉባኤው ማዕከል በመመለስ በተለያዩ መንፈሳዊ ዝግጅቶች ላይ የሚሳተፉ መሆናቸውን ኮሚቴው አስታውቋል።    

የቴዜ ማሕበረሰብ ከዚህ በፊት፣ እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በ2017 ዓ. ም. ላዘጋጀው የአውሮጳ ወጣቶች ዓመታዊ ጉባኤ መልዕክታቸው የላኩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው እንዳስገነዘቡት የፕሮቴስታንት፣ የካቶሊክ እና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ወጣቶችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደስ እንዲላቸውና ለሐዋርያቱ የተሰጣቸው ዓይነት ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን ተቀብለው፣ ከወንጌል በሚገኘው ደስታ በመሞላት በመካከላቸው አንድነትንና ፍቅርን እንዲያሳድጉ የመንፈስ ቅዱስ እገዛን ጠይቀው ወጣቶቹ በወንድማማችነት ጉዞ ድፍረት እንጂ ፍርሃት እንዳይሰማቸው፣ ህብረታቸውም ለሌሎች የምስክርነት ብርሃን ሆኖ እንዲበራ ያስፈልጋል ማለታቸው ይታወሳል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
26 September 2019, 16:41