+ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ፣ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት፣ + ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ፣ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት፣ 

+ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2012 ዓ. ም. ዘመን መለወጫን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፅዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2012 ዓ. ም. የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት ለመላው ምዕመናን ያስተላለፋት መልዕክት።

“በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
አሐዱ አምላክ አሜን

“እግዚአብሔር ሆይ ከዘመናት እስከ ዘመናት መጠጊያ ሆነኸናል” (መዝ. 90፡1)

ብፁዓን ጳጰሳት፣
ክቡራን ካህናት፣ ገዳማውያንና/ዊያት፣
ክቡራን ምዕመናን፣
በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ፣
ክቡራትና ክቡራን፣
የጊዜና የዘመን ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር አባታችን እንኳን ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቴን እገልጽላችኋለሁ። ከሁሉ በፊትም እግዚአብሔር አምላካችን መጠጊያ ሆኖን በሕይወት እንኖርበት ዘንድ ዕድል ስለተሰጠን በአዲስ ዓመት አምላካችንን እናመሰግነዋለን።
እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጊዜ አንስቶ ዝናብን እየሰጠ ዘርን በማብቀል ፍጥረትን ከመመገብ ባሻገር ብርሃንን እና ጨለማ ፣ ወቅቶችን በማፈራረቅ ዓመታትን በወራትና ወራትን በሳምንታት ሳምንታትን በቀን በመከፋፈል የተፈጥሮን ሕግ የሰጠን ሲሆን እኛም ይህን የተፈጥሮ ሕግ ጠብቀን ዘመናትን እንጓዝባቸዋለን። ስለሆነም በአዲሱ በ2012 ዓመተ ምህረት መልካም ነገርን ለማቀድና ለመሥራት ብሎም ለመፈፀም ልባችንን ከፍተን በፍቅር፣ በይቅርታ፣ በአንድነትና በሕብረት መንፈስ ልንጀምረው ያስፈልጋል።
በዋናነት የሁሉ ነገር ዕቅዶቻችንን ክንውኖቻችን ፍፃሜ የሚያገኙት ሰላም ሲኖር ሲሆን በሃይማኖት እምነታችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "ሰላሜን እተውላችኃለሁ ሰላሜን እሰጣችኃለሁ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው ዓይነት አይደለም” (ዮሐ. 14፡17) ያለንን አስተውለን እንመርምር። የክርስቶስ ትዕዛዝ በልባችን ዝቅተኝነትን፣ መሠደድን ፣ ግራ የሚያጋባን ነገርና የመበቀል ፍላጐትን የሚያሳድር አይደለም እንዲያውም ሰላምን ያመጣልናል እንጂ የሕይወት ችግሮቻችንን ሊገዛቸው የሚችለው የትህትና ፀጋ ነው። ምክንያቱም ስህተቶች ሁሉም የሚታረሙት በእምነት እርማት ነው።
ባሳለፍነው ዓመት ብዙ መልካምና እና ያዘንባቸው ተግባራት አሳልፈናል ቢሆንም በአዲሱ ዓመት የሚስተካከሉትን በማስተካከል በአገራችንና በሕዝቦቻችን ላይ ለምን ሆኑ በማለት ማኀበረሰቦቻችንን በሰፊው በመወያየት ዝብርቅርቅ ሁኔታዎችን በብልህነት ማጥራትና ማስተካከል ላይ ትኩረት አድርገን መስራት ይገባናል። ይህ ደግሞ ለአሁኑ ትውልድ እና ለልጆቻችን ብሎም ለመጪው ትውልድ የተመቻቸ ሀገር በመፍጠርና እርስ በርሳቸው ተግባብተውና ተፋቅረው የሚኖሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር ሁላችን ጥረት ማድረግ እንቀጥል ።
ለዚህ ደግሞ በኋላችን ያለውን መልካሙን ዕሴት እያሳደግን ለጋራ ዕድገት እንቅፋት የሆነውን በማስወገድ በፊታችን ያለውን መልካሙን ዕድል ለመያዝ ልባችንን በመክፈት የእርቅና የአብሮነት እጃችንን መዘርጋት ይኖርብናል።
አዲሱ ዓመት እግዚአብሔር ከተስፋ መቁረጥ ከችግርና ከጥላቻ፣ ከመለያየትና እርስ በርስ ከመጠፋፋት ፋንታ የመረጋጋት፣ የማስተዋል፣ የመደጋገፍን በአንድ አምላክ የአንድ ሀገር ልጆች መሆናችንን አውቀን ከጥፋት መንገድ በመውጣት ሰብዓዊ ቀውስን በራሳችን ከማምጣት ይልቅ በአንድነት በህብረት እና ለሀገራችን ለእኛ ሆና በሰላምና በፍቅር የምንኖርባትና የምንሠራበት እንድትሆን እግዚአብሔር ውስጣችንን እንዲያድስልንና እውነተኛ የፈጣሪ ልጆችና ወዳጆች መሆናችንን የሚያስመሰክር ሥራና ተግባር እንድንፈጽም አደራ ማለት እወዳለሁ።
በዚህም መሰረት በአገራችን ሰላም እንዲጎለብት የሃይማኖት አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሊቃውንት፣ የሥነ-ጥበብ ሰዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን በሚያገኙት መድረክ ሁሉ ሰላምን በማስመልከት እየተናገሩ ይገኛሉ። ይህ መልካምና አንዱ አማራጭ ሲሆን ለሰላም አጥብቆ መቆም የሚያሻበት ወቅት ላይ በመሆናችን እንበረታታለን። በመሆኑም በዋናነት የእርቀ ሰላም ጉዳይ ተፈፀሚ ይሆን ዘንድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርቶስ በታላቁ ፀሎት ላይ “… እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ሁሉ ይቅር በለን…" (ማቴ. 5፡12) ብሎ በአስተማረን መሰረት ለእርቅና ለሰላም የተዘጋጀን ሆነን እንድንገኝ ይጠበቅብናል።
በዚህ አጋጣሚ የለውጡ ዋና ተጠቃሽ ለሆናችሁ ወጣቶች የማስተላልፈው መልዕክት የተጀመረው ለውጥ ሲኬታማ ይሆን ዘንድ የአጥፊዎች መሣሪያ ከመሆን ወይም እኩይ ተግባር ከሚፈጽሙ ጋር ከመተባበር በመቆጠብ ይልቁንም ከታላላቅ አባቶቻችሁ ምክርን በመሰነቅ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ዕውቀትና ጥበብ በመመራት አገራችንንና ሕዝባችንን በመታደግ ወደ ተሻለ የዕድገት ደረጃ ለማብቃት እንድትጥሩ ለማሳሰብ እወዳለሁ።
የተወደዳችሁ ምዕመናን በዚህ ርዕስ ዐውደ ዓመት ሁላችንም ባለን አቅም ከየአካባቢው የተፈናቀሉትን የተቸገሩትና አቅመ ደካሞችን በመርዳት በጐ ነገሮችን ሁሉ በፍቅር እንድታደርጉና የደስታ በዓል በጋራና በአንድነት እንድታከብሩ በአክብሮት እንጠይቃለን።
በመጨረሻም ከአገር ውጪ የምትኖሩና የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፤ በሕመም ደዌ ተይዛችሁ በየሆስፒታሉ፣ በየጠበሉና በየቤታችሁ የምትገኙ ሕሙማን እግዚአብሔር ምህረቱን እና ፈውሱን እንዲልክላችሁ፣ በማረሚያ ቤት ያላችሁ የሕግ ታራሚዎች መፈታትን እንዲሰጣችሁ፣ በሥራና በትምህርት እንዲሁም በስደት ከቤተሰቦቻችሁ እርቃችሁ የምትገኙ ልጆቻችንና ወገኖቸችን በሙሉ፣ የአገርን ፀጥታና ዳር ድንበር ለማስከበር በየቦታውና በየጠረፉ የምትገኙ የደህንነትና የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ እንኳን ለ2012 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
አዲሱን ዓመት እግዚአብሐር ባርኮልን በሰላም የምንኖርበት የሰላም፣ የፍቅር የትዕግስትና የመግባባት ዘመን ያድርግልን።

እግዚአብሔር አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅልን ይባርክልን”።


+ካርዲናል ብርሃነየሱስ
ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት

የብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2012 ዓ. ም. ዘመን መለወጫ መልዕክት፣
13 September 2019, 09:47