እርግብ፣ የሰላም ምልክት፣ እርግብ፣ የሰላም ምልክት፣ 

በጀርመን አስረኛው የሐይማኖት ተቋማት የሰላም ጉባኤ በመካሄድ ላይ መሆኑ ተገለጸ።

በመቶዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች የተገኙበት የሰላም ጉባኤ በጀርመን ከተማ በሆነችው በሊንዳው እየተካሄደ መሆኑን የቫቲካን ዜና ዘጋቢ፣ ፍራንቸስካ ሳባቲኔሊ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል። ዛሬ የተጀመረው የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች የሰላም ጉባኤ እስከ ነሐሴ 17 ቀን 2011 ዓ. ም. የሚቆይ መሆኑን ዘገባው አክሎ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ከዚህ በፊት ማለትም በ2005 ዓ. ም. በኦስትሪያ ዋና ከተማ ቬና፣ 600 ተሳታፊዎች የተገኙበትን ዘጠነኛ  የሰላም ጉባኤ አካሂደው እንደነበር ከዘገባው ለማወቅ ተችሏል። ከዛሬ ነሐሴ 14 ቀን እስከ 17 ቀን 2011 ዓ. ም. በጀርመን ከተማ በሆነችው ሊንዳው በሚካሄደው የሰላም ጉባኤ ላይ እንደሚገኙ የተጠበቁት 800 እንግዶች፣ የልዩ ልዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ የመንግሥት ተወካዮች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የሕዝባዊ ማሕበራት ተወካዮች መሆናቸው ታውቋል። ዘንድሮ በሚካሄደው የሰላም ጉባኤ ላይ የሚወያዩበት ርዕስ፣ ዓለማችንን ባጋጠማት ወቅታዊ ችግሮች ላይ ጥልቅ የሞራል መግባባትን መገንባት የሚል ሲሆኑ፣ በሰላም ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ ዓለም አቀፍ ምክር ቤትን የሚመሩ አዲስ ኮሚቴን በመምረጥ፣ ሐይማኖት ለሰላም በሚለው መርህ በመመራት የእምነት ተቋማት በጋር የሚሰሩበትን መንገድ ለማመቻቸት መሆኑ ታውቋል።           

“መጭውን የወደ ፊት እድል በጋራ እንንከባከብ” በሚል ርዕሥ፣ ለአሥረኛ ጊዜ የተዘጋጀው የሐይማኖት ተቋማት የሰላም ጉባኤ ቀዳሚ ዓላማ በተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ማሳደግ፣ በአመጾች እና በግጭቶች ውስጥ በሚገኙት አገሮች፣ ከእነዚህም መካከል በሕዝባዊት ዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሰሜን እና በደቡብ ኮሪያ እና በንያርማር ሰላምን ለማውረድ የሰላም ውይይቶች የሚካሄዱበትን ቅድመ ሁኔታዎች ማመቻቸት ነው ተብሏል።

ማሕበራዊ ጥቅምን ወደሚጋሩበት አቅጣጫ ማምራት ያስፈልጋል፣

የሐይማኖት ተቋማት የሰላም ጉባኤ ፕሬዚደንት የሆኑት ክቡር አቶ ሉዊጂ ዴ ሳልቪያ፣ ከቫቲካን የጣሊያንኛ ቋንቋ ዝግጅት ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት የጉባኤያቸው ዓላማ በተለያዩ አገሮች ዘንድ የሚታየውን ራስን ብቻ የመከላለል የብሔርተኝነት አስተሳሰብን በማውገዝ፣ በአገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት በማሳደግ፣ ማሕበራዊ ጥቅሞችን በጋራ መካፈል ወደሚችሉበት አቅጣጫ ማምራት እንደሆነ ገልጸው ተስፋን የሚሰጥ ብቸኛው አቅጣጫም ይህ መሆኑን ክቡር አቶ ሉዊጂ አስረድተዋል። አቶ ሉዊጂ ዴ ሳልቪያ በገለጻቸው፣ ዘንድሮ ከነሐሴ 14 - 17 ቀን 2011 ዓ. ም. የሚካሄደው አሥረኛው የሐይማኖት ተቋማት የሰላም ጉባኤ በተግባር የሚተረጎሙ  ውሳኔዎችን፣ ከእነዚህም መካከል አመጽ በሚካሄድባቸው አግሮች ውስጥ ሰላም እና እርቅ እንዲወርድ ቀና የሆኑ መንገዶችን ማመቻቸት የሚሉ እንደሚገኝበት ገልጸዋል።   

ዓለም አቀፍ የሐይማኖት ተቋማት የሰላም ጉባኤ የተመሠረተው በ1962 ዓ. ም. ሲሆን፣ በዓለማችን የሚገኙ የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች የተሰባሰቡበት፣ ከዘጠና በላይ አገሮች ውስጥ የሚገኙ የሴቶች እና የወንዶች ማሕበራት የሚገኙበት፣ የተለያዩ የወጣት ማሕበራትም የሚገኙበት መሆኑ ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
20 August 2019, 17:18