የቨነዙዌላ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ አዟዬ አያላ፣ የቨነዙዌላ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ አዟዬ አያላ፣  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከቨነዙዌላ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ዘንድ ምስጋና ቀረበላቸው።

የቨነዙዌላ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ባለፈው ሳምንት ውስጥ ባካሄደው ጠቅላላ መደበኛ ሐዋርያዊ ጉባኤ ፍጻሜ ላይ እንደገለጸው አገሩን በማስተዳደር ላይ ያለው የፖለቲካ ስርዓት እንዲለወጥ በሕገ ወጥ መንገድ የመንግሥት ስልጣንን የያዙት ከስልጣናቸው እንዲወርዱ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአገሪቱ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እንዲካሄድ ጠይቋል።

የቨነዙዌላ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ አዟዬ አያላ፣ በአገራቸው ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ስም ሆነው ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። የቨነዟዌላ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው ያችን አገር ባጋጠማት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት በችግር ውስጥ ከወደቀው ከቨነዙዌላ ሕዝብ ጎን ሆነው በጸሎታቸው ስለሚያስታውሱን ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የደቡብ አሜርካ አገር ቨነዙዌላ ባሁኑ ወቅት በምግብ፣ በመጠጥ ውሃ፣ በመድሕኒት፣ በመብራት ሃይል እና በትራንስፖርት እጦት ምክንያት በከፍተኛ ችግር ውስጥ የምትገኝ መሆኗ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት በአገር ውስጥ የሚገኝ፣ ወደ 6 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በከፍተኛ ችግር ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በአገሩ ከተከሰተው ችግር ሸሽተው ወደ አጎራባች አገሮች እና ወደተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተሰደዱት የቨነዙዌላ ሕዝብ ቁጥር ከ4 ሚሊዮን በላይ መሆኑን የቫቲካን የዜና አገልግሎት ባልደረባ ዴቦራ ዶኒኒ ከላከችልን ዘገባ ለማወቅ ተችሏል። የቨነዙዌላ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ አዟዬ አያላ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት፣ ያለፈው እሁድ ሐምሌ 7 ቀን 2011 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለጸሎት ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በሙሉ ባሰሙት ንግግር የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ ቀውስ ያጋጠመውን ቨነዙዌላ፣ የፖለቲካ መሪዎች ለሕዝባቸው የሚበጀውን ማሰብ እንዲችሉ፣ የሕዝቡም ስቃይ የሚያበቃበት ጊዜ እንዲመጣ ወደ እግዚአብሔር እንጸልይ በማለት ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል። የቨነዙዌላ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ባለፈው ሳምንት ውስጥ ባካሄደው ጠቅላላ መደበኛ ሐዋርያዊ ጉባኤ ፍጻሜ ላይ እንደገለጸው አገሩን በማስተዳደር ላይ ያለው የፖለቲካ ስርዓት እንዲለወጥ ማለትም በሕገ ወጥ መንገድ የመንግሥት ስልጣንን የያዙት ከስልጣናቸው እንዲወርዱ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአገሪቱ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እንዲካሄድ መጠየቃቸው ታውቋል። ቨነዙዌላ ባሁኑ ወቅት በሁለት ፕሬዚደንቶች፣ በኒኮላስ ማዱሮ እና በተቀናቃኛቸው እና የብሔራዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት በሆኑት ዩዋን ጓይዶ መመራቱ ለፖለቲካው ቀውሱ ዋና ምክንያት መሆኑ ይነገራል።

የፖለቲካ ለውጥ ይካሄድ፣

የቨነዙዌላ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ አዟዬ አያላ፣ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ አገራቸውን ካጋጠመው የፖለቲካ፣ የኤኮኖሚ እና ማሕበራዊ ቀውስ ለማውጣት ከተፈለገ፣ የአገሩ ሕገ መንግሥትም እንደሚፈቅደው፣ ከአገር የተሰደዱትንም የሚያሳትፍ እና ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች የሚገኙበት ብሔራዊ ምርጫ እንዲካሄድ አስተያየታቸውን ገልጸው አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ዜጎች መሠረታዊ አገልግሎቶች እንኳ ሳይቀር ተጠቃሚ እንዳይሆን አድርጓል ብለዋል። የትውልድ አካባቢያቸው የሆነውን የሰሜን ቨነዙዌላ ክፍለ ሃገር ማራካይቦን ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ አዟዬ፣ በከተማቸው ከ5-6 ሰዓት ያህል መብራት እንደሚቋረጥ፣ ምንም እንኳን ነዳጅ የሚመረት አካባቢ ቢሆንም 50 ሊትር ቤንዚን ለመግዛት ሙሉ ቀን የሚወስድ ወረፋ መኖሩን አስታውሰዋል። አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው የአገራቸው መንግሥት ሕገ ወጥ መንግሥት ነው ያሉት ብጹዕ አቡነ አዟዬ ከአገራቸው ሕዝብ መካከል ከ12 እስከ 14 ከመቶ የሚሆን በስደት ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ለሕይወታቸው የተሻለ ሥፍራ ፍለጋ ወጥተው በባሰ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን፣ በሰው አዘዋዋሪ ወንጀለኞች እጅ መግባታቸውን፣ ልጆቻቸው ለባርነት ሕይወት የተቀሙባቸው በርካታ እናቶች መኖራቸውን አስረድተዋል።

መንግሥት ከሕዝቡ ጋር ግንኙነት የለውም፣

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ከፍተኛ ምክር ቤት አስተባባሪ ከሆኑት ከአቶ ሚኬሌ ባችሌት ጋር መገናኘታቸውን የገለጹት ብጹዕ አቡነ አዟዬ፣ ምክር ቤቱ ባለፈው ወር ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ በቨንዙዌላ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚፈጸም መግለጹን አስታውሰዋል። ብጹዕ አቡነ አዟዬ አክለውም መንግሥት የሚያራምደውን አይዲዮሎጂ በቴሌቪዥን ፕሮግራሞቹ በኩል ከማሰራጨት በቀር ከሕዝቡ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ብለዋል። በሌላ ወገን ነገር ግን ከፍተኛ ሰብዓዊ መብቶች እየተጣሱ መሆኑን፣ የመንግሥት ወታደሮች፣ ወጣት ተማሪዎች እየሞቱ እና እየቆሰሉ መሆናቸውን ብጹዕ አቡነ አዟዬ ተናግረዋል።

ምስጋና ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣

በመጨረሻም የቨነዙዌላ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ አዟዬ አያላ፣ በአገራቸው ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ስም ሆነው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ለቨነዙዌላ ሕዝብ ለሰጡት ትኩረት፣ ለጸሎት ድጋፋቸው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። የአገራቸው ብጹዓን ጳጳሳት ከመላው የአገሪቱ ሕዝብ ጋር በመሆን ለተደረገላቸው እርዳታ ምስጋናን ማቅረባቸውን ገልጸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለቨነዙዌላ ብቻ ሳይሆን በችግር ውስጥ ለወደቁት አገሮች የሚያደርጉት ከፍተኛ ድጋፍ ግልጽ ይሆናል ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
16 July 2019, 16:56