የአፍሪቃ እና ማስዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በኡጋንዳ-ካምፓላ፤ የአፍሪቃ እና ማስዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በኡጋንዳ-ካምፓላ፤ 

የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ 50ኛ ዓመቱን በማክበር ላይ ይገኛል።

በዩጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ ከሐምሌ 13 እስከ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ 18ኛው የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ በመካሄድ ላይ መሆኑ ታውቋል። “የእግዚአብሔር ቤተሰብ የሆነች የአፍሪቃ ቤተክርስቲያን ደስ ይበላት፣ በዕልም ታክብር! የኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት ትምስክር!” በማለት የአፍሪቃ እና ማስዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ምስረታ 50ኛን ዓመት የወርቅ ኢዩቤልዩን በማከበር ላይ መገኘቷን በቫቲካን የዜና አገልግሎት የአፍሪቃ ክፍል የላከልን ዜና አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በናይጀሪያ የኦዮ ካቶሊካዊ ሀገር ስብከት ጳጳስ እና የወቅቱ የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ኤማኑኤል ባደጆ ለባቲካን የዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት በጉባኤው ምስረታ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ላይ ብጹዓን ካርዲናሎች፣ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ክቡራን ካህናት የተለያዩ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ማሕበራት ተወካዮች፣ ከምዕመናንም ወገ እንደዚሁ፣ የካቶሊክ ሚዲያ አውታሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ በጠቅላላው 300 እንግዶች የሚገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል። የአፍሪቃ እና ማስዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በውስጡ የፓን አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ማሕበራዊ መገናኛ ኮሚቴን  የሚያካትት ሲሆን ዋና መቀመጫው በጋና ዋና ከተማ አክራ ላይ የሚገኝ መሆኑ ታውቋል።

የአፍሪቃ ታላቅ ወዳጅ የነበሩት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ በ1961 ዓ. ም. ወደ ኡጋንዳ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ባደረጉበት ወቅት የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ሲምፖዚየምን መመስረታቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ የአፍሪቃ ብጹዓን ጳጳሳት ሲምፖዜም በመሠረቱበት ወቅት አፍሪቃን አስመልክተው በጻፉት “የአፍሪቃ ምድር” በተሰኘው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው በኩል እንደገለጹት የአፍርቃ ምድር፣ ሕዝቦቿ እድገትን የሚያይበት የግል ይዞታዋ ነው ብለው፣ በምድራቸው የወንጌል መልዕክተኞች የሚያድረጋቸውን አዳዲስ ዘዴዎችን ማመቻቸት ይችላሉ ማለታቸው ይታወሳል። 

የ2011 ዓ. ም. የካምፓላ ሰነድ፣

በዩጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ ላይ ከሐምሌ 13 እስከ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄደው 18ኛው የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ የአፍሪቃን የወንጌል ተልዕኮ የደረሰበትን ደርጃ የሚገልጽ ሰነድ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። በዚህ ጉባኤ ወቅት ብጹዓን ጳጳሳቱ ከሚመለከቷቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል አንዱ በአፍሪቃ ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎትን በብቃት ማቅረብ የሚያስችሉ አዳዲስ መንገዶችን ለይቶ ማወቅ መሆኑ ታውቋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ በውይይታቸው ማጠቃለያ ላይ የካምፓላ ሰነድ የተሰኘ ሐዋርያዊ ሰነድ የሚያወጡ መሆናቸው ተገልጿል። ሰነዱም የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የ50 ዓመታት ሐዋርያዊ ጉዞን የሚያስታውስ እና ለሚቀጥሉት 50 ዓመታት ቅድሚያን በመስጠት ሊያከናውን የቀደውን ውጥን ይፋ ያደርጋል ተብሏል። ሰነዱ በሦስት ቋንቋዎች ማለትም በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛ እና በፖርቹጊስ ቋንቋ የሚታተም ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ www.secam.org በሚለው በብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤ ደረ ገጽ ላይ የሚወጣ መሆኑ ታውቋል።

በኡጋንዳ ሰማዕታት መታሰቢያ ሥፍራ የተለያዩ በዕላት ይከበራሉ፣

የአፍሪቃ እና ማስዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ምስረታ 50ኛን ዓመት የወርቅ ኢዩቤልዩ ክብረ በዓል ማጠቃለያ የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት የሚፈጸመው በካምፓላ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የናሙጎንጎ ሰማዕታት መታሰቢያ ቤተክርስቲያን ውስጥ እሁድ ሐምሌ 21 ቀን 2011 ዓ. ም. መሆኑ ታውቋል። በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ከጉባኤው ተሳታፊዎች በተጨማሪ ከተለያዩ ሀገረ ስብከቶች፣ ቁምስናዎች እና የክርስቲያን ማሕበራት እንዲሁም ከተለያዩ የአፍሪቃ ደሴቶች የሚመጡ ምዕመናን የገኙበታል ተብሏል። የመላው አፍሪቃ እና ማስዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በ1961 ዓ. ም. የተመሰረተው በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ማግስት  የአፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በበጎ ፈቃድ ተነሳስተው የቤተክርስቲያናቸውን ድምጽ ለኩላዊት ቤተክርስቲያን በጋራ ለማሰማት በማለት እንደሆነ ታውቋል። 

22 July 2019, 16:54