የጃፓን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት የሥጋ ደዌ በሽተኞችን ይቅርታ ጠየቁ የጃፓን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት የሥጋ ደዌ በሽተኞችን ይቅርታ ጠየቁ 

የጃፓን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት የሥጋ ደዌ በሽተኞችን ይቅርታ ጠየቁ

በጃፓን የሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጽዕን ጳጳሳት በጃፓን የሚገኙ በሥጋ ደዌ በሽታ የተጠቁ ሰዎችን ይቅርታ መጠየቃቸው የተገለጸ ሲሆን ይህ የብጹዕን ጳጳሳቱ ይቅርታ የአጋሪቷ ጠቅላይ ሚንስትር በተመሳሳይ መልኩ የሥጋ ደዌ በሽተኞችን ይቅርታ መጠየቃቸውን ተከትሎ የተደረግ መሆኑም ተገልጹዋል።

የእዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

“በጃፓን የሚገኙ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት በሥጋ ደዌ በሽታ ለተጠቁ ሰዎች፣ ለቤተሰቦቻቸው እና ከእዚህ ዓለም በሞት ተለይተው ወደ ሰማያዊ ቤታቸው ለሄዱ ሰዎች በሙሉ ይቅርታ እንጠይቃለን” በማለት ብጹዕን ጳጳሳቱ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

የሥጋ ደዌ በሽታ ምን ማለት ነው?

የሥጋ ደዌ በሽታ በአሁኑ ወቅት በሕክምና እርዳታ መዳን የሚችል በሽታ እንደ ሆነ የሚታወቅ ሲሆን ነገር ግን እ.አ.አ ከ1907-1996 ዓ.ም ድረስ የጃፓን መንግሥት በእዚህ በሥጋ ደዌ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ከተቀረው የማኅበረሰብ ክፍል ተገልለው እንዲኖሩ አድርጎ እንደ ነበር የሚታወስ ሲሆን በእዚህ መድሎ የተነሳ በዚህ የሥጋ ደዌ በሽታ የተጠቁ ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸው ለእንግልት እና ለስቃይ ተዳርገው እንደ ነበረ ለመረዳት ተችሉዋል።  

በጃፓን የሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት በመግለጫቸው ጨምረው እንደ ገለጹት “በወቅቱ መንግሥት በሥጋ ደዌ በሽታ የተጠቁ ሰዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን ከተቀረው የማኅበረሰብ ክፍል ተገልለው እዲኖሩ ማደረጉን ባለመቃወማቸው እና በእዚህ በሽታ ተጠቅተው የነበሩ የማኅበስረስብ ክፍሎች በተገቢው ሁኔታ እንክብካቤ ባለማድረጋቸው ጭምር፣ እንዲሁም ካሳ ይከፈላቸው ዘንድ የበኩላቸውን ጫና ባለማሳደራቸው፣ ችላ በማለታቸው የተነሳ በሥጋ ደዌ በሽተኞች ስቃይ በማባባሳቸው የተነሳ እና በተጨማሪም ከሥጋ ደዌ በሽተኞ ጎን ባለመቆማቸው እና መብታቸው እንዲከበር የበኩላቸውን ጫና ባለማድረጋቸው ጭምር” ይቅርታ መጠየቃቸው ተገልጹዋል።

በጃፓን የሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት በመግለጫቸው ጨምሮ እንደ ገለጹት “በ 1996 ዓ.ም ላይ የሥጋ ደዌ በሽተኞችን መብት የሚያስጠብቅ ደንብ ከተደነገገ በኋላ ኩማሞቶ በሚባል ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ፍርድ ቤት በሰጠው ብያኔ መሰረት በጉዳቱ ተጠቂ ለሆኑ የሥጋ ደዌ በሽተኞች ካሳ ይከፈላቸው ዘንድ ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት እ.ኤ.አ. በ 2001 ዓ.ም ለቀድሞ የሥጋ ደዌ በሽተኞች እና ቤተሰቦቻቸው ካሳ የተከፈላቸው መሆኑን የገለጸው መግለጫው የሥጋ ደዌ በሽተኞችን ጉዳት፣ ስቃይ፣ እንግልት እና መገለል በተመለከተ እ.አ.አ በ2005 ዓ.ም ላይ አጠቃላይ ሪፖርት በቀረበበት ወቅት ሳይቀር ይቅርታ አለመጠየቃቸው በራሱ እንዳሳዘናቸው በመግለጫው የጠቀሱ ሲሆን “ዛሬ ግን በእዚህ የቸልተኛ ተግባራችን የተነሳ ላደረስነው በደል ከልብ በመጸጸት ይቅርታ ለመጠየቅ እንወዳለን” ብለዋል።

መድልዎ እና መገለል

በጃፓን የሚገኙት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት በመግለጫቸው አክለው እንደ ገለጹት “እ.አ.አ በ1943 ዓ.ም የሥጋ ደዌ በሽታን ማዳን የሚችል ፕሮሚን በመባል የሚታወቅ መድኋኒት ተገኝቶ ነበር። እ.አ.አ በ1956 ዓ.ም ሮም የሥጋ ደዌ በሽተኞችን አስመልክቶ ባወጣችሁ መግለጫ የሥጋ ደዌ በሽተኞችን ማግለል እንዲቆም እና ከማኅበርሰቡ ጋር ተመልሰው የሚቀላቀሉበት ሁኔታ ይመቻች ዘንድ አዋጅ አወጣች። ይሁን እንጂ ጃፓን የሥጋ ደዌ በሽተኞችን እና ቤተሰቦቻቸው ጥበቃ እንዲደረግላቸው የሚያስገድድ ሕግ እ.አ.አ እስከ 2001 ዓ.ም ድረስ አለወጣችም ነበር። ይህም ብዙ የሥጋ ደዌ በሽታ ተጠቂ የነበሩ ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸው በሕይወት ሂደት ውስጥ ተገልለው እንዲኖሩ አድርጉዋቸዋል” በማለት መግለጫው ጨምሮ ይገልጻል።

“በቃላት ብቻ የተገለጸ ይቅርታ በቂ አይደለም” በማለት ጨምሮ የገለጸው በጃፓን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት መግለጫ “ከልብ መጸጸታችንን እና ማዘናችንን ለመግለጽ፣ እንዲሁም በእዚህ አድሎ እና መገለል የተነሳ ለከፍተኛ ስቃይ የተዳረጉትን ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸውን ተጨባጭ በሆነ መልኩ ይቅርታችንን ለመግለጽ ያስችለን ዘንድ ምንም እንኳን ቀደም ሲል የነበረውን ሥቃያቸውን ሙሉ በሙሉ ለመካስ የማይቻል እና አስቸጋሪ ቢሆንም ቅሉ በሁኑ ወቅት ግን ይቅርታ መጠየቃችን በጥቂቱም ቢሆን ለማሳየት ይችላ ዘንድ በእዚህ በሽታ ተጠቅተው የነበሩ አረጋዊያንን በአረጋዊያን መንከባከቢያ ተቋማቶቻችን ውስጥ ተቀብለን አሰፍላጊውን እገዛ እና እንክብካቤ እያደረግን እንገኛለን” ብለዋል።

በጃፓን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት መግለጫ ማጠቃለያ ላይ “እኛ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች እንደ መሆናችን መጠን የእዚህ ዓይነቱን ኃጢያት ደግመን ላለመሥራት ቃል እንገባለን” ካሉ በኋላ ለሰብአዊ መብት አድናቆት ከመስጠት ባሻገር ሰብአዊ መብቶችን ማክበር አለብን ካሉ በኋላ መግለጫው ተጠቃሉዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጲያ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አባል የሆኑት ሲ/ር ስንቅነሽ ገብረማርያም በኢትዮጲያ የሥጋ ደዌ በሽታን ለመከላከል በተደረገው ጥረት ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጾ በህይወት ዘመን የላቀ የሙያ አገልግሎት ተሸላሚ መሆናቸውን ከእዚህ ቀደም መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን ለረጅም ዓመታት በአለርት ሆስፒታል ሁለገብ አገልግሎት በመስጠት ይታወቃሉ፡፡

ሲስተር ስንቅነሽ እኤአ ከ1983 እስከ 2000 በአለርት ሆስፒታል በማኅበራዊ የምክር ሙያ አገልግሎት በመስጠት በስጋ ደዌ ታካሚዎች ላይ የነበረው መገለል እንዲቀንስ እንዲሁም ታካሚዎች ግንዛቤ ኖሯቸው ለህክምና አገልግሎት ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ እንዲበረቱ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ስራ ሰርተዋል፡፡በሆስፒታሉ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎችና ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመተባበር ተግባር ተኮር ስልጠና ህብረተሰቡ እንዲያገኝ በማድረግም ይታወቃሉ፡፡ 

ሲስተር ስንቅነሽ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መድህን ማህበራዊ አገልግሎት ማዕከልን በማቋቋም ባለፉት 30 ዓመታት ከተለያዩ ሆስፒታሎች ህክምናቸውን ከጨረሱ በኋላ ወደ ማህበራዊ ህይወትና ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀሉ ያልቻሉ ታካሚዎችን በማቋቋምና ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግም የሰሩት ስራ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ከ500 በላይ የሚሆኑ የስጋ ደዌ ተጠቂ ቤተሰብ ልጆችን ትምህርት እንዲማሩ በመደገፍ፣ የአዕምሮ ዝግመት ያለባቸውን ሰዎች የተለያዩ የሙያ ስልጠና አግኝተው ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግም ስማቸው በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ 

19 July 2019, 11:50