በሶርያ የጦርነት ሽሽት፣ በሶርያ የጦርነት ሽሽት፣ 

ከሶርያ-አሌፖ ካቶሊካዊ ቁምስና ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የምስጋና መልዕክት መላኩ ተገለጸ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሶርያ ሕዝብ ሰላም እና እርቅ ብለው ለሚያደርጉት የጸሎት ድጋፍ እና ጥረት በአገሩ ከሚገኝ የአሌፖ ቁምስና ምዕመናን የምስጋና መልዕክት መቀበላቸውን የቫቲካን የዜና አገልግሎት ባልደረባፌደሪኮ ፒያና የላከልን ዜና አመልክቷል። በአሌፖ ከተማ ለሚገኝ ካቶሊካዊ ቁምስና መሪ ካህን የሆኑት ክብሩ አባ ፊራስ፣ ቅዱስነታቸው ለሶርያ ሕዝብ ሰላምን እና እርቅን በመመኘት ያለፈው ሰኔ 21/2011 ዓ. ም. ለፕሬዚደንት በሽር አል አሳድ መልዕክት ማላካቸውን አስታውሰዋል።   

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አሁንም በጦርነት እና በአመጽ ውስጥ በምትገኝ ሶርያ፣ የሰው ሕይወት እየጠፋ፣ ንብረት እየወደመ መሆኑን የተገነዘቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለፕሬዚደንት በሽር አል አሳድ በላኩት መልዕክታቸው ሕዝቡ ከሞት እና ከመቁሰል አደጋ እንዲተርፍ፣ የኢድሊብ ከተማ እና አካባቢዋ ሕዝብ ከቤቱ እንዳይፈናቀል፣ የተፈናቀሉትም ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ፣ በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙት ነጻ እንዲወጡ፣ በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚቆዩትም ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙበትን ዕድል እንዲያገኙ፣ የፖለቲካ እስረኞች ሰብአዊ መብት እንዲከበር፣ የሚድረገላቸው እንክብካቤ እንዳይጎድልባቸው ለሶርያው ፕሬዚደንት ለአቶ በሽር አል አሳድ አሳስበው ፕሬዚደንቱ ለሕዝባቸው በጎውን ሁሉ እንዲያደርጉላቸው ማሳሰባቸው ይታወሳል። በአሌፖ ከተማ ውስጥ ለሚገኝ ካቶሊካዊ ቁምስና መሪ ካህን የሆኑት አባ ፊራስ በምስጋና መልዕክታቸው በኩል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ ሶርያን ሳያስታውሷት ያለፉበት አጋጣሚ የለም ብለው የእኔ ውድ ሶርያ ብለው የሚጠሯት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢድሊብ ክርስቲያኖችን መርሳት የለብንም፣

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን የቅዱስነታቸውን መልዕክት መነሻ በማድረግ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ለሶርያ ሕዝብ አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ ማስፈለጉን እና የኢድሊብ ከተማ እና አካባቢዋ ሕዝብ የሚገኝበት አስከፊ ሁኔታ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ያሳሰባቸው መሆኑን አስረድተዋል። በኢድሊብ ከተማ እና አካባቢዋ የሚኖር ሕዝብ ቁጥር ከሦስት ሚሊዮን በላይ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 1.3 ሚሊዮን የሚሆኑት ለሞት እና አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ የተገደዱ መሆናቸውን በአሌፖ ከተማ ለሚገኝ ካቶሊካዊ ቁምስና መሪ ካህን ኣባ ፊራስ ሉትፊ አስታውቀዋል። ከወታደራዊ ቀጠና ነጻ በሆነው አካባቢ እንዲሰፍሩ በተደረጉት ተፈናቃዮች ላይ በቅርቡ የተፈጸመው ጥቃት መከራቸውን የባሰ አድርጎታል ያሉት ኣባ ፊራስ ሉትፊ የኢድሊብ ከተማ እና አካባቢዋ ሕዝብ ሕይወት በከፍተኛ አደጋ ላይ የወደቀ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
24 July 2019, 16:18