የኮስታሪካ የትምህርት ሚኒስትር ሥራቸውን በለቀቁበት ጊዜ ንግግር ሲያደርጉ፣   የኮስታሪካ የትምህርት ሚኒስትር ሥራቸውን በለቀቁበት ጊዜ ንግግር ሲያደርጉ፣  

ማንኛውም የፖለቲካ ሂደት ለሰው ልጅ ቅድሚያን መስጠት እንደሚገባ ተገለጸ።

የኮስታሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ይፋ ባደረጉት መልዕክታቸው በማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ለሰው ልጅ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ አሳሰቡ። በአገራቸው ውስጥ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ እያደገ የመጣውን የሕዝብ አመጽ እና ሰልፍ የተመለከቱት የመካከለኛዋ የደቡብ አሜርካ አገር የኮስታሪካ ብጹዓን ጳጳሳት በጋራ ሆነው በጻፉት መልዕክታቸው እንደገለጹት ሕዝቡ ብሶቱን በይፋ መግለጽ እና ተደማጭነትም ሊኖረው ይገባል ብለዋል። የኮስታሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በማከልም ሕዝባቸው ይዞ የወጣው ጥያቄ ማሕበራዊ ፍትህ የሚያሻው፣ የሥራ እና የትምህርት ዕድል ጥያቄ እንጂ የአይዲዮሎጂ ጥያቄ አይደለም ብለዋል። የሕዝቡን ጥያቄ ሲዘረዝሩ፣ የስነ ምግባር እሴቶች ይከበሩ፣ በአገሪቱ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ይሰጥ፣ የአገሪቱ የተፈጥሮ ሃብት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለሁሉም ይዳረስ፣ ለአነስተኛ የምርት ማምረቻ ተቋማት ትኩረት ይሰጣቸው የሚሉ መሆናቸውን በመልዕክታቸው ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አመጽ ሳይሆን ውይይት ያስፈልጋል፣

የኮስታሪካ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በጽሑፍ ይፋ ባደረገው መልዕክቱ ሁኔታው ወደ ከፋ ደረጃ ከመድረሱ አስቀድሞ ገንቢ የውይይት መድረክ እንዲመቻች፣ ሃሳብን በነጻነት በመግለጽ መደማመጥ ያለበት መድረክ እንዲዘጋጅ አሳስበዋል። የሚዘጋጀው መድረክም የጥቂቶችን ፍላጎት የሚያስተናግድ ሳይሆን የጋራ ጥቅምን ያማከለ መሆን አለበት ብለው ይህ ካልሆነ አገሪቱ ወደ ከፋ አመጽ እንዳትገባ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል። ማሕበራዊ ሰላም መሰረታዊ ነው ያሉት ብጹዓን ጳጳሳቱ፣ ማሕበራዊ ሰላምን ለመገንባት የሁሉም ሰዎች መልካም ፈቃድ እና ቅንነትን ይጠይቃል ብለዋል።

አዲሱ የሥርዓተ ትምህርት አወቃቀር ምንን ያካትታል፣

በኮስታሪካ ለተቀሰቀሰው የሕዝብ አመጽ ቀዳሚ ምክንያት የሆነው የስርዓተ ትምህርት ለውጥ እና የትምሕርት ጥራት ማሻሻያ  ጥያቄ እንደሚለው መደበኛ ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ የተቃረቡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ከማጠናቀቃቸው አስቀድመው በየማምረቻ ተቋማት ተሰማርተው ወደ ሥራው ዓለም ከመግባታቸው አስቀድሞ በቂ የተግባር ልምድ መቅሰም አለባቸው የሚል መሆኑ ታውቋል። ተማሪዎቹ ይህን ካጠናቀቁ በኋላ መንግሥት ትምህርታቸውን በአግባቡ ላጠናቀቁት የሥራ እድልን ያመቻች የሚል ሲሆን በሌላ ወገን ሰራተኛ ማሕበራቱ አስቀድሞ በተለያዩ የማምረቻ ተቋማት ውስጥ በሥራ ተሰማርተው  ለሚገኙት ሰራተኞች የሚሰጠውን ወርሃዊ ደሞዝ ዚቅ ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋት አለ ተብሏል።

ከአንድ ዓመት በፊት ተመሳሳይ ሰልፍ ታካሂዶ ነበር፣

በመካከለኛዋ የላቲን አሜርካ አገር በሆነችው በኮስታሪካ ሕዝቡ ያላፈው ዓመት በመስከረም ወር ላይ ለአስር ቀናት ያህል የሥራ ማቆም አድማን በመምታት ለተመሳሳይ ጥያቄ ወደ አደባባይ መውጣቱ ይታወሳል። በዚህም ምክንያት በሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ የዋጋ ግሽበት መከሰቱን ይታወሳል። በሰልፈኞች እና በጸጥታ አስከባሪዎች መካከል ግጭት ተከስቶ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸው እና አንድ ወጣት ሕይወቱን ማጣቱ ይታወሳል።

በእነዚህ ሳምንታት በመደረግ ላይ ያሉትን የሕዝብ ሰልፎች ማቆም የሚችሉት በሠራተኛ ማሕበራት፣ ከእነዚህም መካከል የመምህራን እና የጤና ባለ ሞያዎች ማሕበራት ተገኝተው ከመንግሥት ጋር መደራደር ከቻሉ ብቻ ነው በማለት አስተያየታቸውን የሚገልጹ አሉ ተብሏል። በድርድሩ መካከል የኮስታሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤን የሚወክሉ ብጹዓን ጳጳሳት ይገኛሉ ተብሏል።                         

04 July 2019, 16:17