በአይቮርኮስት የሚገኘው  በያሙሱክሮየሰላም እመቤታችን ቤተመቅደስ ታሪክ በአይቮርኮስት የሚገኘው በያሙሱክሮየሰላም እመቤታችን ቤተመቅደስ ታሪክ  

በአይቮርኮስት የሚገኘው በያሙሱክሮየሰላም እመቤታችን ቤተመቅደስ ታሪክ

የሰላም እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ የሚገኘው በምዕራብ አፍሪቃ በአይቮርኮስት ሀገር፣ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት ፌልክስ ሁፉኤ ቧኜ በተወለዱበት መንደር በያሙሱክሮ ነው። ፌልክስ ሁፉኤ ቧኜ አይቦርኮስት ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነጻ ስትወጣ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት እንደ ነበሩ ከሀገሪቱ ታሪክ የምንረዳው ጉዳይ ነው። እ.አ.አ. ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ የነፃዋ አይቮርኮስት ዋና ከተማ በሆነችው በያሙሱክሮ የሰላም እመቤታችን ትልቅ ባዚሊካ እንዲሠራ የወሰኑት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ራሳቸው እንደ ነበሩም ከቤተመቅደሱ ታሪክ የምንረዳው ነው።

የፕሬዝዳንቱም ዋና ዓላማ በዓለም ታላቁ ቤተክርስቲያን ብለው አስበው በነበረው ቤተክርስቲያን ግንባታ ራሳቸውን በዓለም ላይ ለማሳወቅ ፈልገው እንደ ነበረም ይነገራል። የያሙሱክሮ እመቤታችን ባዚሊካ በሮም የሚገኘው የትልቁ የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅጂ ሲሆን በአፍሪቃ ሀገር ከሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ትልቁ ክብ ጣራ (ጉልላት) ያለው ቤተክርስቲያን ሲሆን በመላው ዓለም በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከተሠሩት ትላልቅ ጉልላቶች ካሏቸው አብያተክርስቲያናት አንዱ መሆኑ የታወቀ ነው።

የሰላም እመቤታችን የያሙሱክሮ ባዚሊካ የተሠራው እ.አ.አ. ከ1985 ዓ.ም. እስከ 1989 ዓ.ም. ድረስ በነበሩት አራት ዓመታት ውስጥ ነበር። የመሠረት ድንጋዩን እ.አ.አ. በነሐሴ 10 ቀን 1985 ዓ.ም. ባርከው ያስቀመጡት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ (1978-2005) ሲሆኑ ባዚሊካውንም እ.አ.አ. በመስከረም 10 ቀን 1990 ዓ. ም. በይፋ መርቀው የከፈቱት ራሳቸው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ነበሩ። ባዚሊካው በተመረቀበት ዕለት ፕሬዚዳንት ሁፉኤ ቧኜ ራሱ በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አማካይነት ባዚሊካውን ለቅድስት መንበር አስረከቡ። ከተመረቀ ከሁለት አሥር ዓመታት ጥቂት በሚበልጥ ጊዜ ውስጥ የያሙሱክሮው የሰላም እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ የአይቮርኮስት ሀገር ልዩ ምልክት ከመሆኑም በላይ ከሰሀራ በታች በአፍሪቃ ክፍለ አህጉር ሀገሮች ከሚገኙት አብያተክርስቲያናት ሁሉ መካከል ትልቁ ነው።

ባሁኑ ጊዜ የያሙስክሮው የሰላም እመቤታችን ባዚሊካ በሀገር ጎብኚዎችም ሆነ በመንፈሳውያን ተጓዦች ዘንድ በጣም የታወቀ ሆኖአል ለማለት ይቻላል። የያሙስክሮው የሰላም እመቤታችን ባዚሊካ በመላው ዓለም ከሚገኙት ትላልቅ አብያተክርስቲያናት አንዱ ነው። በምዕራብ አፍሪቃ ለሚገኙት የካቶሊክ እምነት ተከታዩች በሙሉ ታላቅ የእምነት ማስረጃ ነው ለማለትም ይቻላል።

የባዚሊካው ውጫዊ ቅርጽ በጣም አስደናቂ ነው። የባዚሊካው ዋና ማዕከላዊው ክፍል በጣም ረጅም በሆነ ዕብነ በረድ የተሠራ ሲሆን በዓለም ላይ ካሉት ትላልቅ ጉልላቶች በአንዱ ያጌጠ ነው። የያሙሱክሮው የሰላም እመቤታችን ባዚሊካ ጉልላት አሠራር በጅምላ ውዝግብ ፈጥሮ እንደ ነበር የሚታወቅ ነው። ምክንያቱም በሮም ከሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ጉልላት ርዝመት እንዲበልጥ ታቅዶ ስለ ነበረ ነው። ነገር ግን በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ማሳሰቢያ መሠረት ጉልላቱ ከቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ጉልላት ዝቅ እንዲል መደረጉም ይነገራል። ይሁን እንጂ በጉልላቱ ላይ በተጨመረው ረጅም መስቀል አማካይነት የያሙሱክሮው የሰላም እመቤታችን ባዚሊካ ጉልላት ርዝመት 158 ሜትር ሲሆን የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ጉልላት ርዝመት ግን 133 ሜትር ነው።

ምንም እንኳ የያሙሱክሮው የሰላም እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ በሮም ከሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በከፍታውና በርዝመቱ ቢበልጥም ብዙ ሕዝብ በመያዝ አቅም የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ይበልጠዋል። በርግጥ የያሙሱክሮው እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ለ7,000 (ሰባት ሺ) ሰዎች የሚበቃ መቀመጫ ሲኖረው በተጨማሪም ለ11,000 ሰዎች የሚበቃ መቆሚያ ቦታ አለው ማለትም ባዚሊካው ባንድ ጊዜ 18,000 ሰው የማስተናገድ አቅም አለው። የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ግን ባንድ ጊዜ 60,000 (ስልሣ ሺ) ሰዎች መያዝ ይችላል። በተጨማሪ ደግሞ የያሙሱክሮው የሰላም እምቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ የግድግዳው ውጫዊ ክፍል ትላልቅ የተዘጉ ቋሚዎችና ክፍት ቦታዎች ስላሉት እጅግ ብዙ ሰው ማስተናገድ ይችላሉ።

ይህ ሁኔታ በግምት ውስጥ ከገባ የያሙሱክሮው የሰላም እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ብዙ ሰው በመያዝ አቅሙ ከቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ይበልጣል ለማለት ይቻላል። ነገር ግን የባዚሊካው የውስጣዊ ክፍል ብቻ ሰው የመያዝ አቅሙ በግምት ከተወሰደ በዓለም ካሉ ትላልቅ ብዙ ሰው ከሚያስተናግዱት አብያተክርስቲያናት መካከል የያሙስክሮው የሰላም እመቤታችን ባዚሊካ 9ኛው ሲሆን በአፍሪቃ ክፍለ አህጉር ደግሞ አንደኛውና ትልቁ ቤተክርስቲያን ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ በያሙስክሮው የሰላም እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ በፍንጣቂ መስተዋት የተሠሩ 36 ክፍሎች ሲኖሩ በአጠቅላይ 7,400 ሜትር ካሬ ቦታ ይሸፍናሉ። እነዚህም ክፍሎች የተሠሩት በፈረንሳይና በጣልያን የእጅ ሙያተኞች ነበር። በተለይም ደግሞ በጣም የታወቀው ጣልያናዊ የእጅ ሙያተኛ የሚላኖው አልዶ ግራሲ በያሙሱክሮው የሰላም እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ በሚገኘው የፍንጣቂ መስተዋት ሥራ ከፍተኛ ሚና እንደ ተጫወተ ይነገራል። የያሙሱክሮው የሰላም እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ አጠቃላይ የእብነበረድ ሥራ በስፋት 70,000 ሜትር ካሬ ነው። ከእብነ በረዱም አብዛኛው ከጣልያን ሀገር የተገዛ እንደ ነበረም ይነገራል። የሰላምና የፍትሕ እውነተኛ ተዋንያን በመሆን ለእግዚአብሔር ክብርና ለቤተክርስቲያን እድገት ትላልቅ ነገሮችን እንድንፈጽም የያሙሱክሮው የሰላም እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ መልካም አብነት ይሁነን። የሰላምና የፍትሕ ንግሥት እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ለሀገራችንና ለቤተክርስቲያናችን ሰላምንና ፍትሕን ታማልድልን አሜን።

 

26 June 2019, 15:34