የሰኔ 23/2011 ዓ.ም ሰንበት ዘአስተምሮ 2ኛ እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የሰኔ 23/2011 ዓ.ም ሰንበት ዘአስተምሮ 2ኛ እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የሰኔ 23/2011 ዓ.ም ሰንበት ዘአስተምሮ 2ኛ እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

  1. ሮሜ 5፡12-21
  2. 3ኛ ዮሓ 1፡1-15
  3. ሓዋ ሥ 16፡1-13
  4. ማቴ 22፡1-22

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

በሰርግ ድግስ ላይ የተጠሩ ሰዎች ምሳሌ

ኢየሱስም እንደ ገና እንዲህ የሚል ምሳሌ ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ ለልጁ ሰርግ የደገሰ ንጉሥ ትመስላለች፤ ንጉሡም የተጋበዙትን ሰዎች እንዲጠሩ አገልጋዮቹን ላከ፤ እነርሱ ግን አንመጣም አሉ። “እንደ ገናም ሌሎች አገልጋዮች ልኮ፣ ‘የተጋበዙትን፣ እነሆ፣ በሬዎችንና የሠቡ ከብቶቼን አርጄ ድግሱን አዘጋጅቻለሁ፤ ሁሉም ነገር ዝግጁ ስለ ሆነ ወደ ሰርጉ ኑ በሏቸው’ አለ። “ተጋባዦቹ ግን ጥሪውን ችላ ብለው፣ አንዱ ወደ ዕርሻው ሌላው ወደ ንግዱ ሄደ፤ የቀሩትም አገልጋዮቹን በመያዝ አጉላልተው ገደሏቸው። 7ንጉሡም በመቈጣት ሠራዊቱን ልኮ ገዳዮቻቸውን አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ። “ከዚያም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ ‘የሰርጉ ድግስ ዝግጁ ነው፤ ነገር ግን የተጋበዙት የሚገባቸው ሆነው ስላልተገኙ፣ ወደ መንገድ መተላለፊያ ወጥታችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ድግስ ጥሩ።’ አገልጋዮቹም ወደ መንገድ ወጥተው ያገኙትን መልካሙንም ክፉውንም ሁሉ ሰብስበው የሰርጉን አዳራሽ በእንግዶች ሞሉት።

“ንጉሡም የተጋበዙትን እንግዶች ለማየት ሲገባ፣ አንድ የሰርግ ልብስ ያልለበሰ ሰው አየ፤እንዲህም አለው፤ ‘ወዳጄ ሆይ፤ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት እዚህ ልትገባ ቻልህ?’ ሰውየው ግን የሚመልሰው ቃል አልነበረውም።

“ንጉሡም አገልጋዮቹን፣ ‘እጅና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል’ አላቸው፤ 14የተጠሩት ብዙዎች፣ የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸውና።”

ግብር ስለ መክፈል

ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያን ወጥተው በመሄድ በአፍ እላፊ እንዴት እንደሚያጠምዱት ተማከሩ። ደቀ መዛሙርታቸውን ከሄሮድስ ወገኖች ጋር ወደ እርሱ ልከው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ እውነተኛና የእግዚአብሔርንም መንገድ በእውነት የምታስተምር እንደሆንህ፣ ለማንም ሳታዳላ ሁሉን በእኩልነት እንደምትመለከት እናውቃለን፤ ንገረን፤ ምን ይመስልሃል? ለመሆኑ ለቄሣር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?”

ኢየሱስ ግን ተንኰላቸውን በመረዳት እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ግብዞች ለምን በነገር ልታጠምዱኝ ትሻላችሁ? ለግብር የሚከፈለውን ገንዘብ እስቲ አሳዩኝ።” እነርሱም አንድ ዲናር አመጡለት። እርሱም፣ “በዚህ ገንዘብ ላይ የሚታየው መልክ የማን ነው? ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው። እነርሱም፣ “የቄሣር ነው” አሉት። እርሱም መልሶ፣ “እንግዲያውስ የቄሣርን ለቄሣር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ”አላቸው። ይህን ሲሰሙ ተደነቁ፤ ትተውትም ሄዱ።

የእለቱ አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር  ዘኣስተምህሮ 2ኛ ሰንበትን እናከብራለን። በዚህም ዕለት ቅድስት ቤተክርስቲያን ወደ እያንዳዳችን የምትልከው መልዕክት ኣላት፣ ይህም መልዕክት የሕይወታችን መመሪያ የሆነው የዕለቱ የመጽሓፍ ቅዱስ ንባብ ሲሆን መልዕክቱንም ኣንብበን ተረድተን በመጨረሻ ወደ ተግባር እንድንለውጠው ትጠይቀናለች ምክንያቱም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን መውደዳችን የሚለካው ወይም የሚመዘነው ቃሉን ሰምተን ወደ ተግባር በለወጥነው መጠንና ቃሉን ወደ ተግባር ለውጠን ባፈራነው ፍሬ ነው። ስለዚህ ዛሬም እንድወትሮው ሁሉ ቃሉን ሰምተን በተግባር ለማዋል እንድንችል መንፈስ ቅዱስ ራሱ ያግዘን። እንግዲህ በዚህ መልኩ ዛሬ በመጀመሪያው ንባብ ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች ሲጽፍ በኣንድ ሰው ምክንያት ኃጢኣት ወደ ዓለም ገባ በዚሁም ኃጢኣት ምክንያት ደግሞ ሞት ወደ ሰው ልጆች ገባ ይለናል። እውነት ነው እግዚኣብሔር ሰውን ከጅምሩ ሲፈጠረው የእርሱ ተባባሪ እንዲሆን በምድር ላይ በተፈጠሩት ፍጥረታት በሙሉ እንዲነግሥና እንዲያስተዳድር እንዲንከባከብም ጭምር ነበር፣ ነገር ግን ሰው ከእግዚኣብሔር የተሰጠውን ይህን ሁሉ ጸጋ ሳይመለከት እርሱ ራሱ እንደ እግዚኣብሔር ለመሆን ፈለገ በዚህም ምክንያት ኣትብላ የተባለውን ፍሬ በላ፣ በበላውም ፍሬ ምክንያት ከገነት ተባረረ የኃጢኣትና የኃጢኣት ውጤቶች እንዲሁም የሞትም ሰለባ ሆነ። ኣዳምና ሔዋን እርግጥ ነው ኣንድ ጊዜ ኃጢኣትን ሰሩ፣ በዛም ኃጢኣት ምክንያት በሰው ተፈጥሮ ላይ ትልቅ የሞት ጥላ ኣጠላ፣ እግዚኣብሔር ለሰው ልጅ ሰጠቶት የነበረው ክብር መልሶ ትገፈፈ፣ በሰዎችና በእግዚኣብሔር መካከል ክፍተት ተፈጠረ፣ የነበራቸውም ጥምረት ተላቀቀ። እንግዲህ ይታያችሁ ይህ ሁሉ መከራና ውርጅብኝ በኣንዱ ኣዳምና በኣንዷ ሔዋን ኃጢኣት ምክንያት ነው፣ እስቲ መለስ ብለን ወደ ራሳችን ኃጢኣት እንመልከት፣ እንደው በትንሹ በቀን ውስጥ በማሰብ በመናገር በማድረግ ስንትና ስንት እጥፍ ኃጢኣት በመፈጸም እግዚኣብሔርንና ወንድም እህቶቻችንን እናሳዝናለን?ዛሬ በኣኗኗራችን በኣነጋገራችን በኣካሄዳችን በኣስተሳሰባችን ልክ ኣዳምና ሔዋን እንዳደረጉት ሳይሆን፣ ከእነርሱ እጥፍ ድርብ በሆነ መልኩ ደጋግመን በኃጢኣት ውስጥ በመዘፈቅ  እግዚኣብሔርን በማሳዘን ላይ እንገኛለን? ኣዳምና ሔዋን ባጠፉት ጥፋት ይህ ኃጢኣትና የእርሱም ውጤት የሆነው ሞት ከመጣ፣ በእኛስ ኃጢኣት ምክንያት ምን ሊመጣ ይችላል? ምክንያቱም የኛ ኃጢኣት ኣንድና ሁለት ሳይሆን ከቁጥርም በላይ ነው። ኣዳምና ሔዋን ምናልባት የእኛን እድል ኣግኝተው ቢሆን ኖሮ ዕድሉን ከእኛ በተሻለ መልኩ በተጠቀሙበት ነበር። ምክንያቱም እኛ ይህንን የኣዳምንና የሔዋንን የሕይወት ተመክሮ ተመልክተን ከዛም በኋላ በተለያዩ ዓበይትና ንዑሳን ነቢያት በየጊዜው የተለያየ መመሪያና ትግሣጽ ተቀብለን፣ በስተመጨረሻም በኣንዱ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ኣማካኝነት ኣዲስ ሕይወት ተቀብለን ስናበቃ፣ ከዛም ባሻገር በየዕለቱ ኃጢኣታችን እንዲታጠብ ምስጢረ ንስሃ ተዘጋጅቶልን እያለ የዚህ ዕድል ተጠቃሚዎች ልንሆን ኣልቻልንም።  ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ በዚሁ በሮሜ መልዕክቱ 5፡17 ጀምሮ ሞት በደል ፍርድ በኣንዱ ሠው በኣዳም ምክንያት ወደ ሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እንደገባ ጽድቅ ጸጋና ሕይወት ደግሞ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እንደመጣ ይናገራል። እውነት ነው ይህንን ጽድቅ ጸጋና ሕይወት በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ተቀብለናል ነገር ግን ከእርሱ በተቀበልነው ጽድቅ ጸጋና ሕይወት መመላለስ ከልቻለን በተለይም ደግሞ ዘወትር በምስጢረ ንስሃ እየታገዝን ሕይወታችንን ማስተካከል ካልቻልን፣ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ተቀብለን ከእርሱ ጋር  መውጣትና መግባት ማሰብና መወሰን ካልቻለን በእኛ ምክንያት ከኣንዱ ኣዳምና ከኣንዷ ሔዋን የበለጠ መቅሰፍት በምድራችንና በራሳችን ላይ እናመጣለን ምክንያቱም እግዚኣብሔር የሰውን ደካማነት ተመልክቶ በመጀመሪያ ደረጃ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ደም ኣማካኝነት ኃጢኣታችንን ኣጠበልን ከዛም በመቀጠል በዚሁ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ኣማካኝነት በተሰራውና በተመሠረተው በምስጢረ ንስሃ ኣማካኝነት እንደገና በጸጋው ሊሞላን በደሙ ሊያጠበን ኃጢኣታችን ሊያስተሰርይልን ሲጠብቀን እኛ ግን ኣሁንም ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት በኃጢኣታችን ውስጥ መመላለስን መረጥን፣ ታዲያ ከዚህ የተነሳ፣ ኣይደለም ሞት ከዚህ የበለጠ ነገር ቢኖር እንኳን ይገባን ነበር። ይልቅስ የእግዚኣብሔን ርኅራሄ ተመልክተን ትዕግስቱንም ኣጢነን ወደ ድሮው የእግዚኣብሔር ልጅነታችን መንፈስ እንመለስ፣ ደግመን በምስጢረ ንስሃ ኣማካኝነት ግንኙነታችንን በማደስ የጽድቅንም ጉዞ በኣዲስ መንፈስ እንጀምር። በሁለተኛው ንባብ ቅዱስ ሓዋርያው ዮሓንስ በሦስተኛ መልዕክቱ ለጋይዮስ ለድሜጥሮስ ሲመሰክር ሰምተናል። ስለ ጋይዮስ ሆነ ስለ ድሜጥሮስ ወንድሞች ሁሉ በጽድቅ በእውነትና በፍቅር እንደሚኖሩ፣ በእውነት ውስጥ እንደሚመላለሱ በመመስከራቸው ቅዱስ ሓዋርያው ዮሓንስ የተሰማውን ደስታ ሲገልፅ ሰምተናል። ቅዱስ ሓዋርያው ዮሓንስ ዛሬ ለእነሱ የተሰጠ ምስክርነት በእኛም ሕይወት ውስጥ እንዲንፀባረቅ ይጋብዘናል። በምናደርገው ማንኛውም ዓይነት መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ለወንድሞችና እህቶች ጥቅም፣ ለማኅበረሰብ መታነፅና፣ ለእኛም መንፈሳዊ እድገት እንድናደርገው ይገባል ይለናል። በዚሁ በቅዱስ ሓዋርያው ዮሓንስ ሦስተኛ መልዕክት ምዕራፍ 11 ላይ ቅዱስ ሓዋርያው ዮሓንስ እንዲህ ሲል መልዕክቱን ያስተላልፍልናል። ወዳጆቼ ሆይ በጎ የሆነውን እንጂ ክፉውን ኣትምሰሉ ይለናል፣ ምክንያቱም በጎን የሚያደርግ ከእግዚኣብሔር ነው፣ ክፉን የሚያደርግ ግን ይላል እግዚኣብሔርን ኣላየውም እንደዉም ኣያውቀውም ይለናል። ስለዚህ የእኛ ጥሪ ሁልጊዜ መልካምን ማርደግ ብቻ ነው፣ የዚህ መልካምነታችንም መነሻ ራሱ እግዚኣብሔር ነው፣ ስለዚህ እግዚኣብሔር የሰጠንን ይህንን መልካምነት ሳናጠፋ ከእኛም ኣልፎ ለሌሎች እንዲተርፍ ለሌሎች እንዲተላለፍ ማድረግ ይገባናል፣ ይህንን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው እግዚኣብሔርን እናውቀዋለን ከእግዚኣብሔርም ጋር የጠበቀ ግንኙነት ኣለን ብለን መናገር የምንችለው። ይህንን መልካምነት ወይንም እውነት በዕለት ተዕለት ሕይወታችን መመስከር ካልቻልን፣ ሁለጊዜም ሓሳባችን ሆነ ሥራችን ክፋትና የመሳሰሉት ብቻ ከሆነ እግዚኣብሔርን ገና ኣላወቅነውም ማለት ነው፣ ከእርሱ ጋር እውነተኛ ግንኙነት ገና በተክክለኛው መንገድ ኣልጀመርንም ማለት ነው። የዛሬው የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 22 ላይ ያለው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ ኣድርጎ ተመሳሳይ ነገር ይናገራል፣ ይኸውም ልጁን ለመዳር የፈለገ ኣንድ ንጉስ ስላዘጋጀው ግብዣ እና ሰለተጠሩት ታዳሚዎች ያትታል። የምሳሌውም ትርጉም እንዲህ ይተነተናል፣ ለልጁ ሰርግ የደገሰው እና ታዳሚዎቹን እንዲጠሩ ባሮቹን የላከው እግዚኣብሔር ራሱ ነው፣ ታዳሚዎቹ ሕዝበ እስራኤል ናቸው፣ ባሮቹም በየጊዜው ይላኩ የነበሩ ነቢያቶች ናቸው። ታዳሚዎቹ የተለያየ ምክንያት በመፍጠር፣ ኣንዱ ወደ እርሻው ሌላውም ወደ ንግዱ ሄደ፣ ሌሎቹ ደግሞ በባሮቹ ላይ በተንኮል ተነሱ የኋላ ኋላም ኣንገላቷቸው በስተመጨረሻም ገደሏቸውም። ይህም የሚያመለክተው እስራኤላውያን ነቢያቶቹ ከእግዚኣብሔር ይዘው የመጡትን የድኅንነት መንገድ፣ የድኅንነት ዕቅድና የድኅንነት ጉዞ  ኣልተቀበሉም፣ በግዴለሽነት ቦታም ሊሰጡት ኣልወደዱም ነቢያቶቹንም ሊያዳምጧቸውም ኣልፈለጉም ትተዋቸው ሁሉም ወደየፊናቸው ወደየሥራቸው ሄዱ። ሌሎቹ ደግሞ የእግዚኣብሔር መልዕክተኛ የነበሩትን ኣያሌ ነቢያትን ገደሏቸው። በዚህ ጊዜ ንጉሱ ተቆጣ ጭፍሮቹንም ልኮ እነዚያን ገዳዮች ኣጠፋ ይለናል። ይህም የሚያመለክተው እግዚኣብሔር በላካቸው ነቢያት ላይ የተፈፀመው በደል ስላስቆጣው ከተማቸውን ኣቃጠለ ገዳዮቹንም ገደለ ይለናል። ይህም የቤተክርስቲያን ኣባቶች እንድሚሉት በ 70 ዓም የእየሩሳሌም ከተማ መደምሰስና ከተማዋም በጠላት እጅ መውደቋን የሚያመላክት ነው ይላሉ። የኋላ ኋላ እግዚኣብሔር ለግብዣው የተጠሩት ሰዎች የተገቡ ባለመሆናቸው ባሮቹ  ወደ መስቀለኛ መንገድ ወተው የገኙትን ሁሉ እንዲሰበስቡ ኣዘዛቸው እነሱም እንደተባሉት እደረጉ። ይህም የሚያመለክተው እግዚኣብሔር ለእስራኤላውያን የሰጠው ሥጦታ ከእነርሱ ተነጥቆ ለኣህዛብ ተሰጠ የሚለውን ነው። በክርስቶስ የተወደዳችሁ ውንድሞቼና እህቶቼ እንግዲህ በዚህ ታሪክ ውስጥ ራሳችንን የታሪኩ ባለቤት ኣድርገን መውሰድ መመልከት መልካም ነው። ምናልባት እግዚኣብሔር የራሱን ግብዣ ኣዘጋጅቶ በየእሑዱ ይጠራናል በቤተክርስቲያን ውስጥ ይጠብቀናል እና ስንቶቻችን ነን  ለእርሱ ግብዣ ቅድሚያ በመስጠት ወደ  ግብዣው ለመሄድ የምንጓጓው? ነው ወይስ እኛም የንጉሱን ጥሪ ላለመቀበል ወደየፊናቸው እና ወደየሥራቸው እንደሄዱት እድምተኞች እኔም ዕድር ኣለብኝ፣ እኔም የዘመድ ሠርግ ኣለብኝ፣ እኔ የምጠይቀው ሰው ኣለ፣ የምጠይቀው ኣራስ ኣለ፣ ገበያ የምገዛው ነገር ኣለ፣ ዛሬ ወደ እስፖርት እሄዳለሁ፣ ዕረፍት ማድረግ እፈልጋለሁ፣ ዘመዶቼን እጠይቃለሁ፣ ብለን በተለያየ ምክንያት ከእሑድ የቅዳሴ ግብዣ እንቀራለን? ወይስ በግዣው መሠረት ወደ ሠርጉ ግብዣ እንሄዳለን?  እዚህ ጋር ጠንቀቅ ብለን ማስተዋል ያለብን ነገር የምናደርገው ነገር ሁሉ ከቅዳሴ በኋላ ይደርሳል እና በሰንበት ቀን ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ለእግዚኣብሔር ቀን እንስጥ። እግዚኣብሔር ሰንበትን ማክበር ከኣስርቱ ትዕዛዛት ውስጥ ሦስተኛ ኣድርጎ ሰይሞታል ስለዚህ ሰንበትን ኣለማክበር ራሱን የቻለ ንስሃ የሚያስፈልገው ኃጢኣት ነው። በመቀጠልም በወንጌሉ ሲነበብ እንደሰማነው በሰርጉ ግብዣ ላይ የተገባ የሰርግ ልብስ ያለበሰ ሰው ነበር ምናልባት ዛሬ ይህ ሰው የሚወክለው እኛን እያንዳዳችንን ነው ምናልባት እኛም የተገባን ሳንሆን ምስጢራትን ለመቀበል እንጓጓ ይሆናል፣ ውስጣችን የተገባ ሳይሆን የተዘጋጀ ሳይሆን የልተገባንን ነገር ለመውሰድ እንሞክር ይሆናል፣ በዚህ መንፈስ የምንጓዝ ከሆነ መጨረሻችን በራሳችን ላይ ፍርድ ማምጣት ይሆናል፣ ልክ የሠርግ ልብስ ሳይለብስ ባልተገባው ሥፍራ የተገኘውና ወደ ውጭ እንደተጣለው እኛም እጃችንና እግራችን ታስሮ ወደ ጨለማው እንጣላለን በዛም ለቅሶና ጥርስ ማፏጨት ይሆናል።

የእግዚኣብሒር ጥሪ ለሁሉም ነው የሱን ድምፅ ሰምተው እሱን የሚከተሉ ግን ጥቂቶች ናቸው፣ እኛም ከተጠሩት ብቻ ሳይሆን ከተመረጡትም ወገን ነነና እርሱ በሚሰጠን ጸጋ በሄደበት ቦታ ሁሉ ልንከተለው እንትጋ። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለፈሪሳውያኑ እንደተናገረ እኛም የቄሳርን ለቄሳር የእግዚኣብሔርን ለእግዚኣብሔር ለመስጠት እንትጋ። ይህንንም ለማድርግ እንድንችል የዘውትር እረዳታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሓዋርያት የሰማዕታትና የጻድቃን ንግሥት የሆነች የክርስቲያኖችና  በእርሷ ታምነው ወደ እርሷ ለተጠጉት ሁሉ መጠለያ የሆነች እናታችን ከልጇ ጸጋንና በረከትን ታሰጠን፣ የሰማነውን በልባችን እንድናሳድርና በተግባር እንድናውለው መንፈሳችን እንዲነሳሳ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ለሁላችን ታሰጠን።

28 June 2019, 11:45