ሐዋርያው ቶማስ ከኢየሱስ ጋር በተገናኘበት ወቅት ሐዋርያው ቶማስ ከኢየሱስ ጋር በተገናኘበት ወቅት  

የሚያዝያ 27/2011 ዓ.ም. ዘዳግም ትንሣኤ ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ

ከሐዋርያቱ ኣንዱ ቶማስ የተባለው በመጀመሪያው የክርስቶስ መገለጽ ጊዜ ኣልነበረም በሁለተኛው ጊዜ ግን ነበረ የክርስቶስን ቁስሎች ተመልክቶ አመነ ጌታዬ ኣምላኬ በማለትም ሙሉ በሙሉ ማመኑን ገለጸ።

የእለቱ ምንባባት የተወሰዱት

1ኛ ቆሮ· 15፡ 1-19

1ኛዮሐ· 1፡1-10

ሐዋ·ሥራ 23፡ 1-9

የዮሐንስ ወንጌል  20፡19-31

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ታየ

በዚያኑ ዕለት፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን በምሽት፣ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን በመፍራት በሮቹን ቈልፈው ተሰብስበው ሳለ፣ ኢየሱስ መጣና በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ይህንም ብሎ እጆቹንና ጐኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርትም ጌታን ባዩት ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው። ኢየሱስም እንደ ገና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እኔን እንደ ላከኝ፣ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” አላቸው። ይህን ካለ በኋላም፣ እፍ አለባቸውና እንዲህ አላቸው፤ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ የሰዎችን ኀጢአት ይቅር ብትሉ፣ ኀጢአታቸው ይቅር ይባልላቸዋል፤ ኀጢአታቸውን ይቅር ባትሉ ግን፣ ይቅር አይባልላቸውም።”

ኢየሱስ ለቶማስ ታየ

በዚህ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው፣ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፣ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አልነበረም። ሌሎች ደቀ መዛሙርትም፣ “ጌታን አየነው እኮ!” አሉት። እርሱ ግን፣ “በምስማር የተቸነከሩትን የእጆቹን ምልክቶች ካላየሁ፣ ምስማሮቹ በነበሩበት ቦታ ጣቴን ካላደረግሁ፣ በጐኑም እጄን ካላስገባሁ አላምንም” አለ። ከስምንት ቀን በኋላም፣ ደቀ መዛሙርቱ በቤት ውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበር፤ በሮቹ ተቈልፈው ነበር፤ ኢየሱስ ግን መጥቶ በመካከላቸው ቆመና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ከዚያም ቶማስን፣ “ጣትህን ወደዚህ አምጣ፤ እጆቼንም ተመልከት፤ እጅህን ዘርጋና በጐኔ አስገባ፤ አትጠራጠር፤ እመን” አለው። ቶማስም፣ “ጌታዬ፤ አምላኬም!” አለው። ኢየሱስም፣ “አንተ ስላየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ግን ብፁዓን ናቸው” አለው። ኢየሱስ በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፉ ሌሎች አያሌ ታምራዊ ምልክቶችን በደቀ መዛሙርቱ ፊት አድርጓል፤ ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ፣ አምናችሁም በስሙ ሕይወት እንዲኖራችሁ ይህ ተጽፎአል።

 

የእለቱ የእግዚኣብሔር ቃል አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም መልካም ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዳግማዊ ትንሳኤ ወይም ደግሞ ዘቶማስ የተሰኘውን ሰንበትን እናከብራለን።

በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በበዓለ ትንሳኤው ያገኘነውን ጸጋና በረከት እንዴት ኣድርገን በሕይወታችን ለመተርጎም የምንችልበትን መንገድ ሊያሳየንና ሊያበረታታን ቀደም ባሉት ንባባት ኣማካኝነት ወደ እያንዳዳችን ልብ በመምጣት ያንኳኳል።

በዚህም መሠረት እንግዲህ በመጀመሪያው ንባብ 1ኛ ቆሮ· 15፡ 1-19 ላይ እንዳዳመጥነው ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነታችን መሠረት ስለሆነው ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሳትና በትንሳኤውም ኣማካኝነት ባገኘነው ጸጋ እንዴት ኣድርገን መጓዝ እንዳለብን ያስተምረናል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን የተበሰረውን  የክርስቶስ ትንሳኤ በማመን ከእርሱም በሚፈልቀው የማያልቅ መንፈሳዊ ጸጋ በመጋትና ሕይወታችንን በትክክለኛ ኣቅጣጫ በመምራት የዘለዓለማዊ ደኅንነት ተካፋዮች እንደምንሆን ይነግረናል።

ክርስቶስን ማመን ማለት ከእርሱ ጋር ኣብሮ መጓዝ ማለት ነው ከክርስቶስ ጋር ኣብሮ መኖር ማለት ነው። እምነታችን ከእርሱ ጋር ኣብረን በመጓዝና በመኖር ላይ ያልተመሠረተ ከሆነ በውስጣችን ኣለን የምንለው እምነት ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል ምክንያቱም ከእርሱ ጋር ካልሆንን በስተቀር ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ፍሬ ማፍራት ኣንችልም። እኛ በእርሱ ውስጥ እርሱ ደግሞ በእኛ ውስጥ ከሌለ በምንም መልኩ መንፈሳዊ ፍሬ ለማፍራት ኣንችልም። የዮሐንስ ወንጌል 15፡ 4-5 ላይ እንዲህ ይላል በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ እኖራለሁ ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር በራሱ ብቻ ፍሬ ሊያፈራ እንደማይቻለው እንዲሁ አናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ ፍሬ ማፍራት ኣትችሉም። እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተ ደግሞ ቅርንጫፎች ናችሁ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ ኣትችሉም በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ እኖራለሁ እርሱም ብዙ ፍሬ ያፈራል ይለናል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንጦስ ሰዎች የሰበከውን ቃል ዛሬም ለእኛ ለእያንዳዳችን ይደግምልናል ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የሞተው ኃጢኣት ሳይኖርበት የእኛን  ኃጢኣት ለማጠብ የእኛን ቅጣት እርሱ ለመሸከም የእኛን ክፋት የእኛን ውርደት የእኛን ስቃይ ለኣንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ነው። ይህንንም ኣድርጎ ከሞት በመነሳት እርሱ ዘለዓለማዊ ኣምላክ መሆኑን ኣሳይቶናል ሞት በእርሱም ላይ ሆነ በእኛ ምንም ዓይነት ስልጣን እንደሌለው ኣረጋግጦልናል።

ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጋር ኣብረን በመኖራችን ከእርሱ ጋር ኣብረን ወደ መቃብር እንወርዳለን ኃጢያታችንን በሙሉ በተከፈነበት በተልባ እግሩ ልብስ ጠቅልለን እዛ በመተው ከእርሱ ጋር ኣብረን አንነሳለን እኛም እንደሱ ዘለዓለማዊ ሞትን ኣሸንፈን  ዘለዓለማዊ ሕይወትን እንቀዳጃለን። ወደ ሮሜ 8፡11 ላይ አንዲህ ይላል ነገር ግን እየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር ክርስቶስ እየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን የሰጠዋል ይለናል።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ኣድርጎ በመነሳቱ በፍርሃትና በጭንቀት ተውጠው ተስፋ ቆርጠው በቤት ውስጥ በር ቆልፈው ተቀምጠው ለነበሩት ወንድሞቹ ኣዲስ ተስፋን ሰጣቸው ጥልቅ የሆነ መረጋጋትን ውስጣዊና ውጫዊ ሰላምን ኣላበሳቸው። እነርሱም ይህን ነገር ከሰው የሰሙት ሳይሆን በራሳቸው ዓይን የተመለከቱት በእጃቸው ዳስሰው ያረጋገጡት ታሪክም ሆነ የሰው ልጅ ሊሽሩት የማይችሉት ሃቅ ነው። ዛሬ በሁለተኛው ንባብ 1ኛዮሐ· 1፡1-10 ላይ አንዳዳመጥነው ይህንኑ ማለትም ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንጦስ ሰዎች የሰበከውን ቃል በሙላት ያጠናክረዋል አንዲህም ይላል ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያ የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውንና የተመለከትነውን እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን። ሕይወትም ተገለጠ ኣይተንማል እንመሰክራለንም ከኣብ ዘነድ የነበረውን ለእኛም የተገለጸውን የዘለዓለምን ሕይወት እናወራላቹሃለን ይለናል።  ስለዚህ ይህ ሞትን ድል ኣድርጎ የተነሳ ኣምላክ ዛሬም ለእኛ ለልጆቹ በመገለጥ የእርሱን ሰላም ያላብሰናል ኣዲስ ሰማያዊ ተስፋን ይሰጠናል ጥልቅ የሆነ ውስጣዊና ውጫዊ ሐሴትን ይሞላናል እንዲሁም ዘወትር የእርሱ እውነተኛ ምስክሮች ሆነን መቆም የምንችልበትን ጸጋና በረከት ያጎናጽፈናል።

ይህ ሞትን ድል ኣድርጎ የተነሳ ኣምላክ የብርሃን ኣምላክ የቅድስናና የጽድቅ ኣምላክ የፍቅርና የኣንድነት ኣምላክ ነው ይላል ቅዱስ ዮሐንስ በዛሬው መልእክቱ። ከእግዚኣብሔር የሚመጣ ብርሃን ጨለማን እንደሚያጠፋ እንዲህ8 ደግሞ ከእግዚኣብሔር የሚመጣ ፍቅርና ሕብረትም ክፉውን ሁሉ እንደሚያርቅ ዛሬ እኛም ከእግዚኣብሔር ጋር ያለንን ኣንድነት በማጥበቅ በብርሃን እንድንመላለስ  በሕይወታችን ያለውን ውስጣዊና ውጫዊ ጨለማን እንድናስወግድ ተጋብዘናል። ይህ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ኣማካኝነት ያገኘነውን ብርሃን የተቀበልነውን እውነተኛ መንፈስ በተግባር አንድንኖርበት ብሎም ይህ ብርሃን ከእኛ ኣልፎ ለሌሎችም አንዲያበራ ምክንያት እንድንሆን ግንባር ቀደም መስካሪዎች እንድንሆን ተጠርተናል።

እግዚኣብሔር ፍጹም ብርሃን ነው ስለዚህ እኛም ከዚህ ከብርሃን ኣምላክ ጋር ሕብረት ካለን ይህ ፍጹም ብርሃን በውስጣችን ያበራል ከብርሃኑ የሚወጣው ነጸብራቅም ልክ እንደ ጨረቃ በዙሪያችን ለሚኖሩት ሁሉ ያበራል በዚህ መልኩ እያንዳዳችን በእርሱ ብርሃን ብንመላለስ የኣንዳችን ብርሃን ለሌላው የሌላው ብርሃን ደግሞ ለሌሎች ስለሚያንጸባርቅ ዓለማችን በክርስቶስ ብርሃን ትሞላለች ጨለማንና የጨለማን ሥራ የዲያቢሎስንም ሴራ ሁሉ በቀላሉ ማስወገድ ትችላለች። በ1ኛ ዮሐንስ 3፡9 ላይ እንዲህ ይላል ስለዚህ የዲያቢሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚኣብሔር ልጅ ተገለጠ ከእግዚኣብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢያትን ኣያደርግም ዘሩ በእርሱ ይኖራልና ከእግዚኣብሔርም ተወልዷልና ኃጢያትን ሊያደርግ ኣይችልም ይለናል። ይህም ማለት ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ራሱ ከመሠረተው ዘወትር ከኃጢያት ርቀን እንድንኖር ከሚያደርገው ከምስጢረ ንስሃ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ኣለው ማለት ነው። በዚህ መልኩ የክርስቶስን ብርሃን ይዘን ከዓለም ጫፍ እስከ ዓለም ጫፍ እንጓዛለን።

 የዛሬው የዮሐስ ወንጌል ምዕራፍ 20 ላይ ያለው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛምርቱ እንደተገለጸ ይናገራል። ደቀመዛምርቱ ፈርተው በኣንድነት ተሰብስበው ወደነበሩበት ገባ ምን ኣልባት እነሱ ከድተውት በመሄዳቸው ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ወቀሳና ትችት ይመጣብናል ብለው ሰግተው ይሆናል እርሱ ግን ፍርሃታቸውን ተረድቶ ጭንቀታቸውንም ተገንዝቦ የማበረታቻና የመጽናኛ ቃል ሰጣቸው ሰላም ለእናንተ ይሁን ኣላቸው። በዚህም ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ቃል ብውስጣቸው የነበረ ስጋትና ጭንቀት ተወገደ።

ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ የስጣቸው ሰላም ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ይህንኑ ሰላም ወደ ዓለም ሁሉ ይዘው አንዲሄዱ ነግሮኣቸዋል። ኣብ እኔን እንደላከኝ እኔም ደግሞ እናንተን እልካችኋለው ኣላቸው ኃጢያትን ሁሉ ይቅር የማለትን ሥልጣን በመስጠት የእርሱን ሰላም የእርሱን ብርሃን የእርሱን ፍቅር የእርሱን ቃል የእርሱን ሕብረት በዓለም ሁሉ እንዲያዳርሱ ላካቸው። ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ ግን የእርሱ መንፈስ የእርሱ ኃይል ዘወትር ከእነርሱ ጋር እንደሚሆን ቃል ገብቶላቸዋል። ዛሬ ደግሞ እኛ በእነርሱ ቦታ ተተክተን እንደየስጦታችን እውነተኛ የክርስትና ሕይወትን በመኖር ይህንን የክርስቶስን ብርሃንና ሕብረት ፍቅርና ሰላም ወደ ዓለም ሁሉ ለማድረስ ጽዋውን ተቀብለናል።

ከሐዋርያቱ ኣንዱ ቶማስ የተባለው በመጀመሪያው የክርስቶስ መገለጽ ጊዜ ኣልነበረም በሁለተኛው ጊዜ ግን ነበረ የክርስቶስን ቁስሎች ተመልክቶ ኣመነ ጌታዬ ኣምላኬ በማለትም ሙሉ በሙሉ ማመኑን ገለጸ።

ይህ የቶማስ መጠራጠር የሚያመለክተው በእያንዳዳችን ውስጥ ያለዉን የኃጢያት ዝንባሌ ነው በእያንዳዳችን ውስጥ ያለዉ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ብርሃን ያልተጎበኘውን የእኛን ማንነት ነው። ነገር ግን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ምንም እንኳን የዚህ ዓይነት የድካም ዝንባሌ ብናንፀባርቅም እርሱ ግን ኣይዟችሁ ኣትፍሩ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ በማለት ያጽናናናል ያበረታንማል። እኛም ይህንን የእርሱን ማጽናኛ ቃል ስንሰማ ልክ አንደ ቶማስ ከልባችን ኣምላኬና ጌታዬ ብለን ለቀጣይ ተልዕኳችን ዝግጁ መሆናችንንንና እስከ መጨረሻ ከእርሱ ጋር ኣብረን እንደምንጓዝ ቃል ልንገባ ይገባል። እውነተኛ የትንሣኤው ብርሃን መስካሪዎች መሆናችንን በሕይወታችን ልናስመሰክር ይገባል።  ይህንንም ለማድረግ እንድንችል የዘውትር ኣጋዢኣችንና ጠበቃችን የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታግዘን ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የተቀበልነውን የትንሣኤ ብርሃን ይዘን እስከ መጨረሻ ይዘን መጓዝ እንድንችል ብርታትን ከአንድያ ለጇ ታሰጠን።

ምንጭ፡ የቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛው አገልግሎት

  

04 May 2019, 09:48