የዐብይ ጾም ወቅት የሰይጣንን ፈተና በእግ/ር ቃል የምናሸንፍበት ወቅት ነው! የዐብይ ጾም ወቅት የሰይጣንን ፈተና በእግ/ር ቃል የምናሸንፍበት ወቅት ነው! 

የዐብይ ጾም ወቅት መንፈሳዊ ለውጥ የምናመጣበት ወቅት ሊሆን ይገባል!

ጸሎት ከእግዚኣብሔር ጋር፣ ምጽዋዕት ከባልንጀራዎቻችን ጋር እና ጾም ደግሞ ከራሳችን ጋር ተመልሰን በአዲስ መልክ ሕብረት እንድንፈጥር ይረዱናል። እግዚኣብሔር፣ ባልንጀራ እና እኔው ራሴ፡ እነዚህ እንዲያው በከንቱ በነው የማይጠፉ እውነታዎች በመሆናቸው የተነሳ በእነዚህ ነገሮች ላይ አጥብቀን መሥራት ይኖርብናል።

አሁን የምንገኝበት ወቅት የዐብይ ጾም ወቅት እንደ ሆነ ይታወቃል። በዚህ የዐብይ ጾም ወቅት “በእውነተኛ ልብ እግዚኣብሔርን እንዳናመልክ ለማድረግ፣ ልባችንን በመጥፎ ነገሮች በመሙላት፣ ከእግዚኣብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት የሚያበላሹብንን ጣዖታት፣ ገንዘብ እና ምድራዊ የሆኑ የማያቋርጡ ፍላጎቶቻችንን በማስወገድ በዚህ የዐብይ ጾም ወቅት ልባችንን ከክፉ ነገሮች የምናጸዳበት የጸጋ ወቅት ሊሆን ይገባል(ከር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ስብከት የተወሰደ)።

የዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ በርካታ የንስሐ መገለጫ የሆኑ ሕይወቶች ሊኖሩ የሚገባ ሲሆን “የክርስቲያን ውስጣዊ ንስሐ በብዙና በተለያዩ መንገዶች ይገለጻል። መጽሐፍ ቅዱስ እና አበው ከሁሉም በላይ መለወጥን ከራስ፣ ከእግዚኣብሔርና ከሌሎች አኳያ የሚገልጹትን ጾምን፣ ጸሎትንና ምፅዋዕትን ያስተምሩናል። እንዲሁም በጥምቀት አማካይነት ወይም በሰምዕትነት ከሚገኘው መንፃት በተጨማሪ ከባልንጄራ ጋር ዕርቅ ማውረድን፣ ተንስሐ እንባን፣ ስለ ባልንጀራ ድኅነት መቆሮርን፣ የቅዱሳን አማላጅነትንና “የኃጢአትን ብዛት የሚሸፍነውን” ፍቅርን ገቢራዊ ማድረግን ያካትታል” (የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 1434።

የዐብይ ጾም ወቅት የጸሎት፣ ምፅዋዕትና የጾም ወቅት ሊሆን ይገባል!

በዚህ የዐብይ ጾም ወቅት ጉዞ ላይ በጣም አስፈላጊ ወደ ሆኑ ነገሮች መመለስ እንችል ዘንድ፣ ከግብዝነት እና ትክክለኛ ካልሆኑ ተግባራት እንቆጠብ ዘንድ የሚረዱንን ሦስት እርምጃዎችን እንወስድ ዘንድ ቅዱስ ወንጌል ሐሳብ ያቀርብልናል፡- እነዚህም ምጽዋዕት፣ ጸሎት እና ጾም ናቸው። ታዲያ እነዚህ ነገሮች ምንድናቸው? ምጽዋዕት፣ መጸለይ እና መጾም፦ እነዚህ ሦስቱ መንፈሳዊ ተግባራት በነው ሊጠፉ ወደ ማይችሉ ወደ ሦስት እውነቶች ይመልሱናል። ጸሎት ከእግዚኣብሔር ጋር፣ ምጽዋዕት ከባልንጀራዎቻችን ጋር እና ጾም ደግሞ ከራሳችን ጋር ተመልሰን በአዲስ መልክ ሕብረት እንድንፈጥር ይረዱናል። እግዚኣብሔር፣ ባልንጀራ እና እኔው ራሴ፡ እነዚህ እንዲያው በከንቱ በነው የማይጠፉ እውነታዎች በመሆናቸው የተነሳ በእነዚህ ነገሮች ላይ አጥብቀን መሥራት ይኖርብናል።

ዐብይ ጾም ልባችንን የሚያደነዝዙ ነገሮችን የምናስወግድበት ወቅት ነው!

የዐብይ ጾም ወቅት በቅድሚያ በጸሎት አማካይነት ሁሉን በሚችል በእግዚኣብሔር ላይ ትኩረት እንድናደርግ የሚጋብዘን የጸጋ ወቅት ሲሆን ይህም ለራሳችን የሚሆን ጊዜ እንድናገኝ በማድረግ እግዚአብሔርን እንድንረሳ ከሚያደርጉን ዓለማዊ ከሆነ ሕይወት ነፃ እንድንወጣ ያደርገናል። ምጽዋዕት መመጽወት ደግሞ በሌሎች ሰዎች ላይ እንድናተኩር የሚጋብዘን ሲሆን ይህም የልግስና ተግባር ከንቱ በሆነ መንገድ ቁሳቁሶችን ለራሳችን ጥቅም ብቻ ይሆን ዘንድ እንዳናጋብስና ለእኔ ጥሩ የሆኑ ነገሮች ብቻ ናቸው ጥሩ የሚባሉ ነገሮች ብለን እንዳናስብ ይረዳናል። በመጨረሻም የዐብይ ጾም ወቅት በጾም አማካይነት ወደ ራሳችን በመመለስ ልባችንን በጥልቀት እንድንመለከት፣ ይህም ደግሞ ከነገሮች ጋር ተጣብቀን እንዳንቀር እና ልብን የሚያደነዝዝ ዓለማዊ የሆነ ሕይወት እንድናስወግድ ይረዳናል። ጸሎት፣ ምጽዋዕት እና ጾም እነዚህ ሦስቱ ነገሮች ላይ የምናጠፍው ጉልበት እና ጊዜ ዘለዓለማዊ የሆነ ሐብት እንዲኖረን ያስችለናል።

ጸሎት፣ ምፅዋዕት እና ጾም። እነዚህን ሦስት ሥነ-ምግባራት በዚህ በያዝነው የዐብይ ጾም ወቅት ተግባራዊ ልናደርጋቸው የሚገባን፣ እነዚህን መንፈሳዊ የሆኑ ግዴታዎችን በምንወጣበት ወቅት ደግሞ በጸሎት ከእግዚኣብሔር ጋር፣ በምፅዋዕት ከባልንጀራዎቻችን ጋር፣ በጾም ደግሞ ከራሳችን ጋር ያልንን እውነተኛ ግንኙነት እናጠናክራለን ማለት ነው። እነዚህን መንፈሳዊ ተግባራት በምናከናውንበት ወቅት ደግሞ በጥንቃቄ እና በምስጢር እግዚኣብሔር ብቻ በሚያየን መልኩ መፈጸም እንደ ሚጠበቅብን ቅዱስ ወንጌል ያዘናል። ይህንን በተመለከተ ደግሞ ቅዱስ ወንጌል እንዲህ ይለናል. . .

ሰዎች እንዲያዩላችሁ መልካም ሥራችሁን በፊታቸው ከማድረግ ተጠንቀቁ። እንዲህ ካደረጋችሁ ከሰማዩ አባታችሁ ዋጋ አታገኙም። እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ፥ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኩራብ በመንገድም እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ምጽዋት ስታደርግ ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቅ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።

ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።  አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።  አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ።  ስለዚህ አትምሰሉአቸው፤ ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና።

ስትጦሙም፥ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ ለሰዎች እንደ ጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ስትጦም፥ በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል። ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤  ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ አብት ሰብስቡ (ማቴ 6፡1-8፣ 16-20)።

በዐብይ ጾም ወቅት የምናደርጋቸው ጸሎት፣ ምፅዋዕት እና ጾም መፈጸም የሚገባን ለታይታ ሳይሆን መንፈሳዊ ሕይወታችንን ለመቀየር በምስጢር የተሰራውን በስውር ተመልክቶ ዋጋችንን ለሚከፍለው ለእግዚኣብሔር ለየት ባለ መልኩ ጸሎት በማድረግ፣ ከባልንጀራዎቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት ማጠናከር እንችል ዘንድ በሚረዳን መልኩ ካለን በማካፈል እና እኛ ራሳችን መንፈሳዊ ትሩፋት እናገኝ ዘንድ የሚረዳንን ጾምን በስውር በመጾም ሊሆን እንደ ሚገባው ቤተ ክርስቲያን ታስተምረናለች።

በዚህ በያዝነው የዐብይ ጾም ወቅት ልባችን መልካም እና ዘላቂነት ያለው ሰላም እንዲኖረው የሚያደርጉት ምድራዊ የሆኑ ነገሮች ሳይሆኑ እግዚኣብሔር ብቻ መሆኑን የምንገነዘብበት የጸጋ ወቅት ነው። ስለዚህ እውነታ በይበልጥ ለመረዳት ያስችለን ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾምን በተመለከተ ራሱ በተግባር አሳይቶን፣ ለእኛ ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ የተወልንን፣ በበረሃ ውስጥ ለ40 ቀናት ያህል የጾመበትን እውነታ መመልከት ተገቢ ይሆናል። ከዚህም እውነታ በጾም ወቅት የሚገጥሙንን ማነኛውንም ዓይነት ፈተና፣ ተግዳሮት እና ያልተገባ ስሜት ራሳችንን መታደግ የምንችለው በእግዚኣብሔር ቃል ላይ መሰረቱን ባደረገ መልኩ መሆኑን እንረዳለን።

 “ኢየሱስ በመጥመቁ ዩሐንስ ከተጠመቀ በኋላ ወዲያውኑ በበረሃ ውስጥ ስላሳለፈው የብቸኝነት ጊዜ ቅዱስ ወንጌል ይተርካል። በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ወደ በረሃ በመሄድ በእዚያ ለዐርባ ቀናት በጾም እና በጸሎት ቆየ። ከሚያገለግሉት መልአክት እና ከዱር አራዊት ጋር አብሮ ኖረ። በእዚህም ጊዜም የእግዚኣብሔር ልጅነቱን ለድርድር እንዲያቀርብ ሰይጣን ለሦስት ጊዜያት ያህል ተፈታትኖታል። አዳምን በገነት፣ እስራኤላዊያንን በበረሃ የገጠማቸውን ዓይነት ፈተና የሚያስታውሱንን እነዚህን ፈተናዎች ኢየሱስ በትዕግሥት ተቃወማቸው፣ ዲያቢሎስም ለጊዜው ከእርሱ ራቀ” (የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ.538)።

የዐብይ ጾም ወቅት የሰይጣንን ፈተና በእግ/ር ቃል የምናሸንፍበት ወቅት ነው!

የዐብይ ጾም ወቅት ኢየሱስ በበረሃ ለዐርባ ቀናት ያህል በጽም ላይ በነበረበት ወቅት በሰይጣን 3 ጊዜ ተፈትኖ ሦስቱንም ጊዜ ይህንን ፈተና እንዳሸነፈ እኛም በእነዚህ የዐብይ ጾም ወቅት፣ በሕይወታችን የሚገጥሙንን ፈተናዎች ለመሸነፍ እና ከእግዚኣብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት አጠናክረን የምንቀጥልበት ወቅት ይሆን ዘንድ በእውነተኛ የጾም እና ጸሎት መንፈስ መትጋት ይኖርብናል ማለት ነው።

የአንድ ክርስቲያን ሥነ-ምግባር መገለጫ የሆኑ ተግባራት!

በእዚህ አሁን በያዝነው የዐብይ ጾም ወቅት ቤተ ክርስቲያን የሐሳብ ለውጥ እንድናደርግ ትጠይቀናለች፣  ከሐሳብ ለውጥ ባሸገር በመሄድ በእዚህ ባለንበት የዐብይ ጾም ወቅት የተግባር እና የስሜት ለውጥ ማምጣት ይኖርብናል። ቤተ ክርስቲያን በእዚህ በዐብይ ጾም ወቅት መልካም ተግባራትን እንድናከናውን ያግዘን ዘንድ ጾም መጾም፣ መፅዋዕት መመጽወት እና ለየት ባለ ሁኔታ ጸሎት በማድረግ ንስሐ መግባት አስፈላጊ እንደ ሆነ ትመክረናለች፣ እነዚህም ሦስቱ ተግባራት ደግሞ በጎ የሆኑ ምግባራትን እንድናከናውን ያነሳሱናል። እነዚህ በጎ የሚባሉ ተግባራት ደግሞ በማቴዎስ ወንጌል 25 ላይ የተጠቀሱት እና የአንድ ክርስቲያን መገለጫ ባህሪይ የሆኑትን በጎ ተግባራትን ማከናወንን ያጠቃልላል። እነዚህም በጎ የሚባሉ ተግባራት “ተርቤ አብልታችሁኛል፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛል፥ ታርዤ አልብሳችሁኛል” (ማቴ 25፡35) የሚሉት የአንድ ክርስቲያን ሥነ-ምግባር መገለጫ የሆኑ ተግባራትን በዚህ በዐብይ ጾም ወቅት መፈጸም ይኖርብናል ማለት ነው።

የዐብይ ጾም ወቅት ያልተገቡ ስሜቶቻችንን የምንልውጥበት ወቅት ነው!

ቤተ ክርስቲያን በተጨማሪም በእዚህ የዐብይ ጾም ወቅት የስሜት ለውጥ እንድናደርግ ጥሪ ታቀርባለች።  በእዚህ በያዝነው የዐብይ ጾም ወቅት ያልተገቡ ስሜቶቻችንን ወደ መልካም ስሜት የምንቀይርበት ወቅት ሲሆን የደጉ ሳምራዊውን ምሳሌ በመከተል በርኅራኄ የተሞላ ስሜት ሊኖረን ይገባል፣ ስሜቶቻችን በሙሉ የክርስቲያን ስሜት መገለጫ ሊሆኑም ይገባል።

መልካም ያልሆኑ ሥነ-ምግባራትን ማስወገድ በራሱ በቂ አይደለም!

በእዚህ የዐብይ ጾም ወቅት መልካም ያልሆኑ ተግባሮቻችንን እና ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ስሜቶቻችንን መቀየር ብቻ በቂ አይደለም፣ ነገር ግን አሁን ባለንበት ዓለማችን የሐስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ያስፈልጋል፣ ምን ማስብ እንዳለብን ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደምናስብ፣ ተገቢ ያልሆኑ ያስተሳሰብ ዘይቤዎቻችንን ሳይቀር መለወጥ አስፈላጊ ነው። የእኛ የአስተሳሰብ ሁኔታ እንደ አንድ ክርስቲያን ነው? ወይስ እንደ አንድ አረማዊ የሆነ ሰው? ከእነዚህ ከሁለቱ በየተኛው ጎራ ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ነው ያለኝ? ብለን በእዚህ በዐብይ ጾም ወቅት ራሳችንን እንድንጠይቅ ቤተ ክርስቲያን ጥሪ ታደርግልናለች።

በእዚህ ባለንበት የዐብይ ጾም ወቅት የአስተሰሰብ ዘይቤዎቻችንን በመቀየር፣ የእኔ አስተሳሰብ ምንጩ ምንድነው? በማለት ራሳችንን በመጠየቅ አስተሳሰባችን የመነጨው ከየት እንደሆነ ለይተን በማወቅ በእግዚኣብሔር መንፈስ እና በክርስቲያንዊ እሴቶች ላይ የተመሰረተ አስተሳስ ይኑረን ወይም አይኑረን ራሳችንን መርምረን በማወቅ መንፈሳዊ ለውጥ እንድናመጣ ይረዳን ዘንድ፣ የእግዚኣብሔርን ጸገ በመማጸን የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ያስችለን ዘንድ የጸጋ ስጦታዎችን ከእግዚኣብሔር የምንማጸንበት ወቅት ሊሆን ይገባል፣ የዐብይም ጾም ወቅት።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
14 March 2019, 14:53