የመጋቢት 15/2011 ዓ.ም የሁለተኛው የዐብይ ጾም ሣምንት ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ የመጋቢት 15/2011 ዓ.ም የሁለተኛው የዐብይ ጾም ሣምንት ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ 

የመጋቢት 15/2011 ዓ.ም የሁለተኛው የዐብይ ጾም ሣምንት ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ

“የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት!”

የእለቱ ምንባባት

1.     ዘፍጥረት 15፡5-12, 17-18

2.    መዝ. 26

3.    ፊሊፕ 3፡17-4፡1

4.    ሉቃስ 9፡28-36

የእለት ቅዱስ ወንጌል

ከዚህም ቃል በኋላ ስምንት ቀን ያህል ቈይቶ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ያዕቆብንም ይዞ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ተብለጭልጮ ነጭ ሆነ።  እነሆም፥ ሁለት ሰዎች እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤  በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር።  ነገር ግን ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ከበደባቸው፤ ነቅተው ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ።  ከእርሱም ሲለዩ ጴጥሮስ ኢየሱስን አቤቱ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ” አለው።  የሚለውንም አያውቅም ነበር። ይህንም ሲናገር ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ሳሉ ፈሩ። ከደመናውም ውስጥ “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ መጣ።  ድምፁም ከመጣ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ። እነርሱም ዝም አሉ ካዩትም ነገር በዚያ ወራት ምንም ለማንም አላወሩም ነበር (ሉቃስ 9፡28-36)

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ በጀመርነው የሁለተኛው የዐብይ ጾም ሳምንት እለተ ሰንበት ስርዓተ አምልኮ የኢየሱስ መልክ ተዐምራዊ በሆነ መልኩ መለወጡን በማሰብ እንድናሰላስል የሚጋብዘን ሲሆን ይህም የተከሰተው ኢየሱስ ደቀ-መዛሙርቱ ለሆኑት ለጴጥሮስ፣ ለያዕቆብና ለዮሐንስ የትንሳኤው ክብር ተምሳሌት የሆነውን ወደ ሰማይ በክብር የወጣበትን አጋጣሚ ገና እዚህ ምድር ላይ እያለ ቀድመው እንዲመለከቱ ያደርጋቸዋል። ወንጌላዊው ሉቃስ (9፡28-36) እንደሚያሳየን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የብርሃን ሥፍራ በሆነው በተራራ ላይ መልኩ መቀየሩን የገለጸልን ሲሆን ይህም ግልጸት ለየት ባለ ሁኔታ ለሦስቱ ደቀ-መዛሙርት ብቻ ለየት ባለ ሁኔታ የተሰጣቸው ልምድ ነው። እነርሱም ከኢየሱስ ጋር ወደ ተራራው ላይ ይወጣሉ እርሱም ለብቻው ለመጸለይ መሄዱን ይመለከታሉ፣ ከእዚያም በኋላ “የፊቱ መልክ መለወጡን ይመለከታሉ” (ሉቃ. 9፡29)። እነርሱ እርሱን በየቀኑ ሰብአዊ በሆነ ሁኔታ እንደ ማነኛውም ሰው አብሮዋቸው ሲኖር ይመለከቱት የነበረ ሲሆን አሁን ግን ሰብዓዊነቱን ባካተተ መልኩ ባሳየው አዲስ ክብር ፊት ለፊት ቆመው ይደነቃሉ። እነሆም ሁለት ሰዎች እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤  በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ፋሲካ ማለትም ስለ መከራው፣ ሞቱ እና ትንሳኤው ይናገሩ ነበር።  ከፋሲካ በፊት የተደርገ ግልጸት ነበር።  ጴጥሮስ ኢየሱስን “አቤቱ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው” (ሉቃ 9:33) በማለት ይናገራል። እርሱ ያ በብርሃን የተሞላ የጸጋ ዘመን ፈጽሞ እንዳያበቃ ፈልጎ ነበር!

ኢየሱስ መልክ ተአምራዊ በሆነ መልኩ መለውጥ በክርስቶስ ተልዕኮ እጅግ በጣም ትክክለኛ እና ወሳኝ በሆነ ጊዜ ውስጥ የተከናወነ ክስተት ሲሆን ይህም ማለት ደቀ መዛሙርቱ እርሱ "ብዙ መከራ እንደ ሚደርስበት [...] እንደ ሚሞት እና በሦስተኛው ቀን ከሙታን እንደ ሚነሣ” ቀድመው እንዲገነዘቡት አድርጉዋል። ኢየሱስ ይህን እውነታ የእርሱ ደቀ-መዛሙርት እንደማይወዱት ያውቃል - የመስቀል እውነታ፣ የኢየሱስ ሞት እውነታ የእርሱ ደቀ-መዛሙርት እንደ ማይፈልጉት ይገነዘባል- በዚህ ምክንያት ነው እንግዲህ የእርሱ ደቀ መዛሙርት የሰማይ አባቱ አንዲያ እና ምርጥ የሆነውን ልጁን ወደ ዘለዓለማዊ ክብር እንዲገባ የሚያደርግበት መንገድ ልጁን ከሙታን በማስነሳት መሆኑን ደቀ-መዛሙርቱ በሚገባ ይገነዘቡ ዘንድ፣ በዚህም ምክንያት በመስቀል ላይ የሚደርሰበትን መከራ እና ሞት መቋቋም ይችሉ ዘንድ ሊያዘጋጃቸው በመፈለጉ የተነሳ የፈጸመው ተግባር ነው። ይህም ደግሞ አንድ ደቀ-መዝሙር ሊከተለው የሚገባው መነገድ ነው፣ ማንም ሰው ወደ ዘለዓለም ሕይወት ሊደርስ የሚችለው በምድራዊ ሕይወቱ የኢየሱስን መስቀል ተሸክሞ ሲጓዝ ብቻ መሆኑን ያሳያል። እያንዳንዳችን የራሳችን የሆነ መስቀል አለን። የራሳችንን መስቀል ተሸክመን በምንጓዝበት ወቅት ጌታ የዚህ ጉዞ ጫፍ የሆነውን የትንሳኤውን ውበት የምንመለከትበትን አቅጣጫ ያሳየናል።

ስለዚህ የክርስቶስ መልክ መለወጥ የክርስቲያን ሕይወት የስቃይ ሁኔታ ያሳየናል። መከራ ማለት ሐዘን ውስጥ መግባት ማለት አይደለም: አስፈላጊ የሆነ ሂደት ነው፣ ጊዜያዊም ነው። እኛ እንድንደርስበት የተጠራንበት ስፍራ የክርስቶስ መልክ እንደ ተለወጠበት ሥፍራ እኛም የምንደርስበት ሥፋር በብርሃን የተሞላ ነው፣ በእሱ ውስጥ ደህንነት፣ ደስታ፣ ብርሀን የእግዚአብሔር ፍቅር፣ ያለ ገደብ እናገኛለን። በዚህ መንገድ የእርሱን ክብሩን ማሳየት መስቀል፣ ፈተናዎች፣ ትግል የምንገጥማቸው ችግሮቻችን ሁሉ  መፍትሄ የሚያገኙት እና ድል የሚሆኑት በእርሱ ፋሲካ  ወቅት መሆኑን ያረጋግጥልናል። በዚህም የተነሳ በዚህ አሁን ባለንበት የዐብይ ጾም ወቅት እኛም ወደ ተራራ እንውጣ! ነገር ግን በምን ዓይነት ሁኔታ ነው መውጣት የሚኖርብን! በጸሎት። በጸሎት መንፈስ ወደ ተራራ እንውጣ፣ በጽሞና መንፈስ በሚደረግ ጸሎት፣ በልባችን ውስጥ ብቻ በሚሰማ ጸሎት፣ ኢየሱስን ብቻ እንድንፈልግ በሚያበረታታን ጸሎት። ለተወሰነ ጊዜ በአስተንትኖ መንፈስ ውስጥ እንግባ፡ በእየለቱ ትንሽዬ ጊዜ ወስደን አስተንትኖ እናድርግ፣ ውስጣዊ ስሜቶቻችን በእርሱ ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ የእርሱ ብርሃን በሕይወታችን ውስጥ እንዲያንጸባርቅ እንፍቀድለት።

በእርግጥም ወንጌላዊው ሉቃስ "እርሱ በሚጸልይበት ጊዜ" መልኩ እንደ ተለወጠ ይተርክልናል። ከአብ ጋር በጥልቀት መወያየቱ፣ በዚያም የሕግ እና የነቢያት መገለጫዎች የሆኑት የሙሴና የኤልያስ -ቃላትን በማስተጋባት በመስቀሉ ላይ ያለውን ሞት ጨምሮ፣ በሙሉ ነፍሱን ለአብ የማዳን ፈቃድ ራሱን በማስገዛት የእግዚአብሄር የብርሃን ክብር ራሱ ተቀብሎ ለእኛም እንዲያንጸባርቅ አድርጉዋል።

ስለዚህ ወንድሞች እና እህቶች፡ በክርስቶስ እና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የሚደረግ ጸሎት ሰው ውስጣዊ የሆነ መንፈሳዊ ለውጥ እንዲያመጣ ያስችለዋል፣ ከእዚያም በዙሪያው ያለውን ዓለም ያበራል። ብርሃንን የሚያበሩ ሰዎች፣ ከዓይናቸው ደማቅ ብርሃን የሚወጣ ሰዎችን ስንት ጊዜ አግኝተናል! እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ጸሎተኛ የሆኑ ሰዎች ናቸው፣ ጸሎት ደግሞ ይህንን የማድረግ ብቃት አለው፡ ጸሎት በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ብርሃን መስጠት እንድንችል ያደርገናል።

ይህንን የዐብይ ጾም ወቅት መንገድ መራመድ በደስታ እንቀጥል። በእነዚህ ቀናት ውስጥ የአምልኮ ሥነ-ስርዓቶች በተደጋጋሚ በመካፈል ለጸሎት እና ለእግዚአብሄር ቃል ቦታ መስጠት ይኖርብናል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከኢየሱስ ጋር እንድንቆይ ታስተምረን ዘንድ እና በእርሱ መንገድ ላይ ለመጓዝ እንችል ዘንድ እርሷ ትርዳን። ምክንያቱ የእርሱን ክብር ማየት የምንችለው ከእርሱ ጋር ሆነን ስንኖር ብቻ በመሆኑ የተነሳ ነው።

 

ምንጭ፡ ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በመጋቢት 08/2011 ዓ.ም ሁለተኛው የዐብይ ጾም ሣምንት ሰንበት በተከበረበት ወቅት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደረጉት ስብከት የተወሰደ።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
21 March 2019, 13:39