ቅዱስ ቤተሰብ፣ ቅዱስ ቤተሰብ፣  

ካርዲናል ራቫዚ ቅዱስ ዮሴፍ የዝምታ ሃይል ትርጉም የተገለጠበት ቅዱስ መሆኑን ገለጹ።

ብጹዕ ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ ቅዱስ ዮሴፍ የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ባልደረባ እንደሆነም አስረድተዋል። የቅዱስ ዮሴፍን ማንነት የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ራቫዚ፣ ቅዱስ ዮሴፍ ትጉ ሠራተኛ፣ አናጺ እና ዕለታዊ ሥራዎቹንም በንቃት ሲያከናውን የኖረ ቀዳሚ የሠርቶ አደሮች ምሳሌ ሆኖ የቆየ ቅዱስ መሆኑን አስረድተዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ያልተነገረለት ቢሆንም፣ እንደዚሁም እርሱ ራሱ ወደ አደባባይ ወጥቶ የተናገረ ባይሆንም በዝምታው መካከል አንደበተ ርቱዕ እንደነበር ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እግዚአብሔርን በጽሞና ማዳመጥ የቻለ፣ የቅድስት ድንግል ማርያም ባለቤት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕጋዊ አባት ቅዱስ ዮሴፍ የዝምታ ሃይል ትርጉም የተገለጠበት ቅዱስ እንደሆነ፣ በዝምታውም ቁጣ እና አመጽ የታከለበትን ጩሄት መመከት የቻለ ቅዱስ መሆኑን በጳጳሳዊ ምክር ቤት የባሕል ተንከባካቢ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደናት እና የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቅ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ አስታወቁ።

የላቲን ሥርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠን በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዘንድ ዛሬ መጋቢት 10 ቀን 2011 ዓ. ም. የቅዱስ ዮሴፍ ቀን ተከብሮ መዋሉ ታውቋል። ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ ዕለቱን በማስታወስ ቃለ ምልልስ ያደረጉት ብጹዕ ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ ቅዱስ ዮሴፍ የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ባልደረባ እንደሆነም አስረድተዋል። የቅዱስ ዮሴፍን ማንነት የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ራቫዚ፣ ቅዱስ ዮሴፍ ትጉ ሠራተኛ፣ አናጺ እና ዕለታዊ ሥራዎቹንም በንቃት ሲያከናውን የኖረ ቀዳሚ የሠርቶ አደሮች ምሳሌ ሆኖ የቆየ ቅዱስ መሆኑን አስረድተዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ያልተነገረለት ቢሆንም፣ እንደዚሁም እርሱ ራሱ ወደ አደባባይ ወጥቶ የተናገረ ባይሆንም በዝምታው መካከል አንደበተ ርቱዕ እንደነበር ገልጸዋል።

ድምጽ ማሰማት እና መናገር ዋጋ በሚሰጥበት በዘመናችን የቅዱስ ዮሴፍ የዝምታ አቋም እንዴት ሊወሰድ ይችላል ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ መልሳቸውን የሰጡት ብጹዕ ካርዲናል ራቫዚ ስለ ቅዱስ ዮሴፍ ብዙ አልተነገረም ሲባል፣ ይህ ማለት ስለ ቅዱስ ዮሴፍ ምንም አልተነገረም፣ እርሱም አልተናገረም ማለት ሳይሆን የተናገራቸው አጋጣሚዎች ጥቂት ቢሆኑም ዛሬ በዘመናችን እንደምናየው አመጽን እና ጦርነትን የሚያስከትሉ፣ ወይም በማሕበራዊ ሚዲያዎች እንደሚከሰቱ የሕዝብን የተረጋጋ ሕይወት የሚያኩ፣ ወይም በፖለቲካው ዓለምም ያየን እንደሆነ መግባባት እና መስማማት የሌለበት ንግግር ሳይሆን፣ የቅዱስ ዮሴፍ ዝምታ መደማመጥ የታከለበት፣ ሰላምን የሚፈጥር እንደነበር አስረድተው አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ድምጻቸውን በሰላማዊ መንገድ ካላሰሙ፣ ቪክቶር ኡጎ የተባለ አንድ ፈረንሳዊ ባለቅኔ እንደተናገረው “ገደብን እና ሥርዓትን ያልተከተለ ንግግር ሰዎችን ወደ መቁሰል እና አልፎ ተርፎ ወደ ሞት አደጋ ሊያደርስ ይችላል” ማለቱን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለቅዱስ ዮሴፍ የሚሰጡት አክብሮት እና ፍቅር ከፍተኛ እንደሆነ የገለጹት ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ አንዳንድ የመንፈሳዊ ምስል ሥዓሊዎች ቅዱስ ዮሴፍን እንቅልፍ እደወሰደው አድርገው ሲያሳዩ በቅዱሳት መጽሐፍት አገላለጽ በሕልም አማካይነት የሚያደርጋቸው መንፈሳዊ ግንኙነቶች፣ የሚገለጥለት ራዕይ እንዳለ ለማስየት ፈልገው እንደሆነ ገልጸው፣ በሰዎች መካከል የሚደረጉ ግንኙነቶች በሙሉ እንደተለመደው የድምጽ ወይም የጽሑፍ ብቻ መሆን እንደሌለበት ነገር ግን መንፈሳዊ ግንኙነቶችም መኖራቸውን አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ በማከልም በመጽሐፍ ቅዱስ ባሕል አገላለጽ የዚህ ዓይነት ግንኙነት ጥልቅ፣ መንፈሳዊ እና ምስጢራዊ ግንኙነት እንደሆነ ተናግረው ቅዱስ ዮሴፍን የሚደርሱ መልዕክቶች በሌሊት ኢየሱስ ክርስቶስም ባለበት እንደነበር አስረድተዋል። በዚህ የተነሳ ቅዱስ ዮሴፍ ጥልቅ በሆነ ምስጢራዊ ችሎታው እና በተረጋጋ መንፈሱ ወደ ራሱ በመመለስ፣ የሚላኩለትን መልዕክቶች መቀበል እንደቻለ ገልጸዋል። ነፍሱ ልታልፍ በተቃረበች በመጨረሻዋ ሰዓት፣ ኢየሱስ ክርስቶስም በጎኑ በነበረበት ሰዓት፣ ቅድስት ድንግል ማርያምን እስከ ሕይወቱ መጨረሻ እንደወደዳት፣ ዘወትር ርህራሔን እና ቸርነትን ያሳያት መሆኑን አስረድተዋል።     

19 March 2019, 18:44