የየካቲት 10/2011 ዓ.ም 5ኛው እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

ኢየሱስ የመጀመሪያዎቹን ደቀ መዛሙርት ጠራ

“እኛ ለጋሾች ስንሆን እግ/ር ታላላቅ ነገሮችን በሕይወታችን ውስጥ ይፈጽማል”

በእለቱ የተነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች

1.     ት.ኢሳያስ 6፡1-8

2.    መዝ. 137

3.    1 ቆሮንጦስ 151-11

4.    ሉቃስ 5፡1-11

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

አንድ ቀን ኢየሱስ በጌንሳሬጥ ባሕር ዳር ቆሞ ሳል ብዙ ሰዎች ወደ እስሩ ቀርበው የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ይጋፉ ነበር። በባሕር ዳርም ቆመው የነበሩትን ሁለት ታንኳዎች አየ፤ ዓሣ አጥማጆች ግን ከእነርሱ ውስጥ ወጥተው መረቦቻቸውን ያጥቡ ነበር። ከታንኳዎቹም የስምዖን ወደ ነበረች ወደ አንዲቱ ገብቶ ከምድር ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ጠየቀው፤ በታንኳይቱም ተቀምጦ ሕዝቡን ያስተምር ነበር።  ንግግሩንም ከጨረሰ በኋላ፥ ስምዖንን ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ጣሉ አለው።  ስምዖንም መልሶ አቤቱ፥ ሌሊቱን ሁሉ አድረን ስንደክም ምንም አልያዝንም፤ ነገር ግን በቃልህ መረቦቹን እጥላለሁ አለው።  ይህንም ባደረጉ ጊዜ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ፤ መረቦቻቸውም ተቀደዱ።  በሌላ ታንኳም የነበሩትን ጓደኞቻቸውን መጥተው እንዲያግዙአቸው ጠቀሱ፤ መጥተውም ሁለቱ ታንኳዎች እስኪሰጥሙ ድረስ ሞሉአቸው። ስምዖን ጴጥሮስ ግን ባየ ጊዜ በኢየሱስ ጕልበት ላይ ወድቆ። ጌታ ሆይ፥ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከኔ ተለይ አለው።  ስላጠመዱት ዓሣ እርሱ ከእርሱ ጋርም የነበሩ ሁሉ ተደንቀዋልና፥ እንዲሁም ደግሞ የስምዖን ባልንጀሮች የነበሩ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ተደነቁ። ኢየሱስም ስምዖንን። አትፍራ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ አለው። ታንኳዎችንም ወደ ምድር አድርሰው ሁሉን ትተው ተከተሉት።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል (ሉቃ 5 1-11) ወንጌላዊው ሉቃስ የቅዱስ ጴጥሮስን ጥሪ የሚያመለክት ታሪክ ያቀርብልናል። የእርሱ ስም ስምዖን እንደ ሚባል እና ዓሳ አስጋሪ እንደ ነበረም ይታወቃል። ኢየሱስ በገሊላ ባሕር ዳርቻ አከባቢ ሲመላለስ በባሕር ዳርቻ ላይ ሆኖው የዓሣ ማስገሪያ/ማጥመጃ መረቦቻቸውን ስያበጃጁ ነበር የተመለከተው። በዚያ ምሽት ምንም ዓይነት ዓሳ ስላልያዘ በጣም ደክሞት እና ተስፋ ቆርጦ በነበረበት ወቅት ነበር ያገኘው። እናም ጴጥሮስ ባልጠበቀው መልኩ እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ ኢየሱስ ጴጥሮስን እንዲገረም ያደርገዋል፡ በእርሱ ጀልባ ላይ ይወጣና ጀልባዋን ወደ ባሕሩ ትንሽ ፈቀቅ እንዲያደርግ ይጠይቀዋል፣ ምክንያቱ በእዚያ ካሉ ሰዎች ጋር መነጋገር ፈልጎ ነበር - በእርግጥ በእዚያን ስፍራ ብዙ ሰዎች ነበሩ። በእዚህ ዓይነት ሁኔታ ኢየሱስ በስምዖን ጀልባ ላይ ተቀምጦ በባሕሩ ዳርቻ የተሰበሰቡትን ሰዎች ማስተማር ጀመረ። ነገር ግን የእርሱ ቃሎች መተማመንን የሚፈጥሩ በመሆናቸው የተነሳ የስምዖንን ልብ ዳግም በመክፈት በእርሱ እንዲታመን ያደርገዋል። ከዛም ኢየሱስ ሌላ አስገራሚ ነገር እንዲከሰት ለማድረግ "ተንቀሳቀሰ"  እንዲህ አለው: “ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ወደ ውሃ ውስጥ ጣሉ አለቸው” (ሉቃ 5፡4)።

ስምዖንም መልሶ “ሌሊቱን ሁሉ አድረን ስንደክም ምንም አልያዝንም”  በማለት የተቃውሞ መልስ ይሰጣል። እንደ አንድ የዓሳ አጥማጅ ባለሙያ “ማታ ምንም ዓይነት ዓሳ ካልያዝን፣ በቀን ደግሞ ምንም ልንይዝ አንችልም” በማለት ጨምሮ መናገር ይችል ነበር። ነገር ግን በተቃራኒው ኢየሱስ በእዚያ ስፍራ በመገኘቱ ተደስቶ እና በእርሱ ቃል ብርሃን ታግዞ “ . . . ነገር ግን በቃልህ ተማምኜ መረቡን እጥላልሁ” በማለት መለሰ። ይህም በእምነት የተሰጠ ምላሽ ነው፣ እኛም በዚህ መልኩ ምላሽ እንድንሰጥ ተጠርተናል፡ ይህም ጌታ የእርሱ ደቀ-መዛሙርት ሁሉ ሊኖራቸው የሚፈልገው ዓይነት ባህሪይ ሲሆን በተለይም ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተለያየ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች እንዲኖራቸው የሚፈልገው ዓይነት ባህሪይ ነው። የጴጥሮስ ታዛዥነት ከፍተኛ ውጤት ያስገኛል “ይህንንም ባደረጉ ጊዜ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ” (ሉቃ 5፡6) ይለናል።

ይህ ተአምራዊ የሆነ የዓሣ ጠመዳ ነበር፣ የኢየሱስን ኃይል ያመለክታል፡ እርሱን ለማገልገል እራሳችንን በልግስና ስናቀርብ በእኛ ውስጥ ታላላቅ ነገሮችን ይፈጽማል። በዚህ መንገድ እርሱ በእያንዳንዳችን ላይ ይሠራል: እንደገና ከእርሱ ጋር በአዲስ መልክ ሕይወትን ለመጀመር እንድንችል እና በአስደናቂ ሁኔታ የተሞላውን አዲስ ባህር ለመሻገር እንድንችል እርሱ በህይወታችን ጀልባ ውስጥ እንዲገባ ልንጋብዘው ያስፈልጋል። በአሁን ወቅት ካለው ክፍት ከሆነው ሰብዓዊ ውቅያኖስ እንድንወጣ እኛን በመጋበዝ የእርሱን  መልካምነት እና ምህረት መስካሪዎች እንድንሆን፣ ለእኛ ሕልውና አዲስ ትርጉም ይሰጣል። አንዳንዴ መለኮታዊው መምህር ለእኛ በሚያቀርበው ጥሪ በመገረም እና በመደነቃችን የተነሳ ‘እኔ የተገባው አይደለሁኝም’ በሚል እሳቤ ተነሳስተን ጥሪውን ላለመቀበል ልናገራግር እንችላለን። ስምዖን ጴጥሮስም ቢሆን በአስደናቂ ሁኔታ በጣም ብዙ ዓሳዎችን ከያዘ በኋላ “ጌታ ሆይ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከኔ ራቅ” ብሎ ተናግሮ የነበረውም በዝሁ ምክንያት ነው። “ጌታ ሆይ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከኔ ራቅ” የሚለው የዚህን ዓይነት ትሁት የሆነ የትሕትና ጸሎት በጣም አስፈላጊ ነው። እርሱ ግን ይህንን የተናገረው በወቅቱ “እርሱ ጌታ መሆኑን” በመረዳቱ የተነሳ በኢየሱስ እግር ሥር ተንበርክኮ ነበር የተናገረው። ኢየሱስም “ ስምዖንን ሆይ! አትፍራ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ” በማለት ያበረታታዋል። ምክንያቱም እግዚአብሔር በእርሱ ከተማመንን ከኃጢአታችን ነጻ ያወጣናል፣ በፊታችን አዲስ አድማስ ይከፍትልናል የእርሱ ተልዕኮ ተባባሪዎች እንድንሆን ያደርገናል።

ተስፋ ቆርጠው እና ደክመው ለነበሩ ለስምዖን እና ለሌሎች ዓሳ አስጋሪዎች በኢየሱስ የተከናወነው ታላቁ ተአምር መረባቸው እስኪሞላ ድረስ ዓሳ መያዛቸው ሳይሆን በተስፋ መቁረጥ መንፈስ የተነሳ የሽንፈት መንፈስ ውስጥ ገብተው እንዳይሰቃዩ በማሰብ ያደርገው ትላቅ ተዐምር ነው። በዚህም ተግባሩ የእርሱ ቃል እና የእግዚአብሔርን መንግሥት ምስክሮች እንዲሆኑ መንፈሱን ገለጸላቸው። እናም “ታንኳዎችንም ወደ ምድር አድርሰው ሁሉን ትተው ተከተሉት” እንደ ሚለው የአንድ ደቀ-መዝሙር ምላሽ በዚሁ መልክ ፈጣን እና ሁለንተናዊ ሊሆን ይገባል። ራሷን ለእግዚኣብሔር ፈቃድ ያስገዛችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚኣብሔር የሚያቀርብልንን ጥሪ መስማት እንችል ዘንድ ከእርሱ ጋር ተባብረን መስራት እንችል ዘንድ እንድታግዘን የእርሱን የደህንነት ቃል በመላው ዓለም ማዳረስ የምንችልበትን ጸጋ እንድትሰጠን ልንማጸናት ይገባል።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃን ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየካቲት 03/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደረጉት ስብከት የተወሰደ

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

16 February 2019, 12:28