የምስራቅ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ የምስራቅ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣  

የምስራቅ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ ወጣቶች የክርስቲያኖች ተስፋ መሆናቸውን አስታወቁ።

በኢራቅ ዋና ከተማ በባግዳድ የተካሄደው የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ዋና ዓላማ በየጊዜው የሚደርስባቸውን በደሎች ከእነዚህም መካከል መሰቃየትንና ስደትን ለመከላከል እንዲቻል ክርስቲያኖች በመካከላቸው ያለውን ሕብረት ለማጠናከር እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመካከለኛው የምስራቅ አገሮች ውስጥ ለሚኖሩት ክርስቲያኖች፣ ወጣቶች የተስፋ ምልክት መሆናቸውን ብጹዓን ጳጳሳት አስታወቁ። ብጹዓን ጳጳስቱ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ምሳሌ በመከተል በየአገሮቻቸው የወደ ፊት ተስፋ የሚሆን ትውልድን ለማፍራት የሚያስችል መሠረትን በመዘርጋት የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ብጹዓን ፓትሪያርኮች ህዳር 21 ቀን 2011 ዓ. ም. 26ኛ የሕብረት አገሮች ጳጳሳት ጉባኤ በኢራቅ ዋና ከተማ በባግዳድ ማድረጋቸው ታውቋል። በባግዳድ ከተማ የተቀመጡት ብጹዓን ጳጳሳት በጉባኤያቸው ማብቂያ ላይ ያወጣውን መልዕክት የጠቀሰው ኤዢያ ንውስ የተሰኘ የመረጃ ማዕከል እንደገለጸው፣ በካቶሊካዊት ቤተክስቲያን የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት መንፈሳዊ አባቶች ወጣቶች በእምነታቸው  ጠንክረው እንዲገኙ፣ ለሀገራቸው እድገት፣ ሰላም፣ ፍቅርና ፍትህ መጎልበት መስራት እንዳለባቸው ማሳሰባቸውን ገልጿል።

ለመካከለኛው የምስራቅ አግሮች ክርስቲያኖች ሕብረት መጠንከር፣

በኢራቅ ዋና ከተማ በባግዳድ የተካሄደው የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ዋና ዓላማ በየጊዜው የሚደርስባቸውን በደሎች ከእነዚህም መካከል መሰቃየትንና ስደትን ለመከላከል እንዲቻል ክርስቲያኖች በመካከላቸው ያለውን ሕብረት ለማጠናከር እንደሆነ ታውቋል። በጳጳሳቱ ጉባኤ ላይ በሊባኖስ የአንጾኪያ ማሮናዊያን ስርዓተ አምልኮን የምትከተል የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ቤካራ ቡትሮስ ራይ፣ የግሪክ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ አብሲ፣ የሶርያ ካቶሊካዊ ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ኢኛስ ዮሴፍ 3ኛ ዩናን፣ በኢየሩሳሌም የላቲን ስርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሾማሊ፣ ለጉባኤው የመክፈቻ ንግግራቸውን ያሰሙት፣ በኢራቅ የባቢሎን ካልዲያ ስርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ሉዊስ ራፋኤል ሳኮ 1ኛ መገኘታቸው ታውቋል። የጉባኤው ተካፋይ ብጹዓን ካርዲናሎች፣ ጳጳሳትና ካህናት በባግዳድ በሚገኘው በቅዱስ ዮሴፍ ካቴድራል ውስጥ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከአካባቢው አገሮች የመጡ በርካታ ወጣቶች መካፈላቸው ታውቋል። የጳጳሳቱን ጉባኤ የተካፈሉ፣ ከአካባቢው አገሮች የመጡ ወጣቶች ከጉባኤው ኣባላት ጋር በጋራ ሆነው በወቅታዊ ጉዳዮች፣ በሚያጋጥሟቸው ችግሮች፣ ስጋቶች፣ ምኞቶችና በወደፊት ተስፋዎች ላይ ሃሳባቸውን ተለዋውጠዋል።

የቤተክርስቲያን አባቶች ከኢራቅ የመንግሥት መሪዎች ጋር መገናኘት፣

በኢራቅ ዋና ከተማ በባግዳድ በተካሄደው 26ኛው የካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት አግሮች ብጹዓን ጳጳሳት ከኢራቅ ሪፓብሊክ ፕሬዚዳንት ከሆኑት ከክቡር አቶ ባራም ሳሊ እና ከሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከክቡር አቶ አደል አብዱል ማዲ ጋር ሆነው የጉባኤው መዝጊያ የሆነውን የመሰዋዕተ ቅድሴ ስነ ስርዓት በዋና ከተማዋ በባግዳድ ከተማ መካፈላቸው ታውቋል። በስነ ስርዓቱ ላይ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ወጣቶች፣ በማሕበራዊና መንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ብቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚጠይቅ መልዕክትም ይፋ ሆኗል።

የሶርያና የኢራቅን ጉዳይ በተመለከተ፣

በበርካታ የሶርያ ግዛቶች ውስጥ ቀስ በቀስ እየታየ የመጣው መረጋጋት የሰላም ተስፋን እንደሰጠ የጉባኤው ጳጳሳት ገልጸዋል። ይህን ተከትሎ በጦርነቱ ምክንያት በየአጎራባች አገሮች ተበታትነው የሚገኙ ስደተኞችና ተፈናቃዮች ወደ አገራቸው እንዲመለሱና የሶርያ ሕዝብ በሙሉ ለብሔራዊ አንድነት በሕብረት እንዲቆሙ ጥሪ ቀርቦላቸዋል። ከኢራቅ ጋር ያለውን የፖለቲካ ሁኔታን በተመለከተ በሁለቱ አገሮች መካከል እየተደረጉ ያሉ መልካም ውይይቶች ተስፋን የሚሰጡ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን የአክራሪነት አቋም ካላቸው ጽንፈኛ ቡድኖች ጋር ሰላማዊ ውይይቶች መደረግ እንዳለባቸው ጳጳሳቱ አምነውበት ይህን ውይይት ፍሬያማ ለማድረግ ወጣቶች ሃገራቸውን በመገንባትና ለሰላም በመሥራት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

ሊባኖስና ፍልስጤም፣

የሊባኖስ ዋና ትኩረት በሶርያ አዲስ መንግሥት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቋቁሞ ለወቅታዊ ችግሮች መፍትሄዎችንና መልሶችን የሚያቀርብ መሆን እንዳለበት ብጹዓን ጳጳሳቱ በመልዕታቸው ገልጸዋል። የጉባኤው ተካፋዮች ከሶርያ የሚሰደዱትን ቤተሰቦች ተቀብለው በክብር ላስተናገዷቸው፣ የእርዳታ እጃቸውን ለዘረጉ እንደ ሊባኖስ ለመሰሉ አገሮች ያላቸውን አድናቆት በጭብጨባ ገልጸዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ የዮርዳኖስ ምድርም ለሶርያ ስደተኞች ያደረገችው መስተንግዶና እርዳታ ከጉባኤው ተካፋዮች ዘንድ ምስጋናንና አግናቆትን እንድታገኝ ማደረጉን ኤዢኣ ኒውስ የዜና ማዕከል ገልጿል።

05 December 2018, 15:55