የኢትዮጲያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለሰላም ግንባታ የሚደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደ ምትደግፍ ተገለጸ
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አዲስ ከተቋቋመው የሰላም ሚኒስትር ጋር ተባብራ ለመሥራት ያላትን ቁርጠኝነት ገለጸች። ባለፈው ሕዳር 03/2011 ዓ.ም በኢትዮጲያ አዲስ የተቋቋመው የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር በመሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ መሐመድ የተመረጡት ወ/ሮ ሙፋሪያት ካሚል የኢትዮጲያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዋና ጽሕፈት ቤት በመገኘት ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን እና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ከሆኑት ከብጽዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ጋር መገናኘታቸውን የኢትዮጲያ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዋና ጽሕፈት ቤት ኦፊሴልያዊ በሆነው የፌስ ቡክ ገጹ ላይ ካወጣው መረጃ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በወቅቱ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ባደረጉት ንግግር እንደ ገለጹት “የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጲያ ሰላም ለመገንባት በሚደርገው እንቅስቃሴ የበኩሉዋን አስተዋጾ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑዋን” መግለጻቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ብጽዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ በግንኙነቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር እንደ ገለጹት አዲስ የተሾሙት የሰላም ሚኒስትር በኢትዮጲያ ሰላምና ደህንነትን በተሳካ ሁኔታ ለማረጋገጥ የሐይማኖት መሪዎችን እና ተቋማቸውን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሀግሪቷን ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ እና በሀገሪቱ ዘላቂ የሆነ ሰላም ለማምጣት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ያላቸውን እምነት መግለጻቸውን ከደርሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል።
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር እና በኢትዮጲያ የሚገኙ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የተምህርት መስጫ ተቋማትን በመጠቀም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጲያ እያደረገች የምትገኘው ሁለንተናዊ የሰው ሐብት ልማት በተመለከተ የቤተ ክርስቲያኗ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ምክትል ጸሐፊ በሆኑት በክቡር አባ ተሾመ አማካይነት በወቅቱ ማብራሪያ የተሰጠ መሆኑን ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በዚህም መሰረት ቤተ ክርስቲያኗ በትምህርት፣ በጤና እና በሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች እያደረገች የምትገኘውን ጥረቶች በስፋት ማብራራታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል። በተጨማሪም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የእርሷ ተልዕኮ አካል የሆነውን የፍትህ እና የሰላም ኮሚሽን በማቋቋም በእውነት ላይ የተመሰረት ዘላቂ ሰላም እና ፍትህ በሀገሪቷ ይሰፍን ዘንድ የበኩሉዋን አስተዋጾ በማድረግ ላይ እንደ ሆነችም ተገልጹዋል።
የሰለም ሚኒስትር የሆኑት ወ/ሮ ሙፋሪያት ካሚል በበኩላቸው እንደ ግለጹት ከሐይማኖት መሪዎች እና ተቋማት ጋር በትብብር መሥራት ጽሕፈት ቤታቸው በሥነ-ምግባር የተሞላ ሰላማዊ ትውልድ በመገንባት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ በጣም አስፈላጊ እንደ ሆነ ገልጸው የእዚህ ጉብኝት ዋና ዓላማ የሃይማኖት መሪዎች በሠላማ ግንባታ እና በብሔራዊ እርቅ ሂደት ውስጥ እያደርጉት የሚገኘውን ድጋፍ እንዲቀጥሉ እና አዲስ ለተመሰረተው የሰላም ሚኒስቴር ቡራኬያቸውን እንዲለግሱ በማሰብ የተደርገ ጉብኝት እንደ ሆነም ጨምረው ገልጸዋል። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን በመጎብኘታችን በጣም ተደስተናል ያሉት የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፋሪያት ካሚል ሰላምን ለማጠናከር በምናደርገው ጥረት ውስጥ ሰፊ የሆነ የማኅበረሰብ አጋርነት እንዳለን የበለጠ እንድንገነዘብ ረድቶናል ብለዋል። “በአሁኑ ወቅት ሀገራችን እያጋጠሟት የሚገኘውን አንዳንድ ፈተኝ የሆኑ ተግዳሮቶች ለማስተናገድ የእናንተ ትብብር እንደማይለየን እርግጠኛ ነኝ” ያሉት የሰላም ሚኒስትር ሙፋሪያት ካሚል በተጨማሪም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በካቶሊክ ትምህርት ቤቶች አማካኝነት በሥነ ምግባር የታነጹ ዜጎችን በማፍራት ረገድ እያበረከተች ያለው አስተዋጾ እና ያስገኘችው ውጤት በጣም አመርቂ እንደ ሆነ ከልማዳቸው እንደ ተረዱ የገለጹ ሲሆን ቤተ ክርስቲያኗም ይህንን ስኬት አሻሽላ እንደ ምትቀጥል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።