የፍልሰታ ማርያም በዓል የፍልሰታ ማርያም በዓል 

የፍልሰታ ማርያም በዓል

ስለ እመቤታችን ክብርና በርሷ ስለ ተደረገው ታላቅ የእግዚአብሔር ሥራ ገናናነት ለማወደስና አማላጅነቷን ለመማጠን ከሚደረጉ ጥልቅ መንፈሳዊነት በብዙዎች የአገራችን ክርስቲያኖች ልብ ዘንድ ልዩ ቦታን የሚይዘው የፍልሰታ ዘመነ ምህለላ መጀመሪያ ሳምንት ላይ እንገኛለን። ይህ ወቅት ከሚያስተላልፍልን መልእክቶች አንዳንዶቹን እንመልከት።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃይሌጊዮርጊስ ቫቲካን

የእመቤታችን ፍልሰታ ሰው ሙሉ ክብር የመጎናጸፍ ጥሪን ከእግዚአብሔር መቀበሉን ያሳስበናል። ሰው በፈጣሪው ፊት በሥጋው፣ በመንፈሳዊነቱ፣ በስሜቶቹ፣ በሃሳቡ... ባጠቃላይ ማንነቱ ዘላቂ ክብር ይኖረው ዘንድ መፈጠሩንና በጣም አላፊና ጊዜያዊ እንዲሁም ሽሚያና ሽኩቻ ለተሞላ ነገር ሳይሆን ለዘላለማዊ ክብር መታጨቱን ይነግረናል። በዘመናችን ሰው ሙሉነቱ ተዘንግቶ አንድም በሥጋው ብቻ ዘላለም ይኖር ይመስል ሌላ ማንነቱን ረስቶ ሲመለክ ሌላም ለስሜት ርካታ ብቻ የተፈጠረ እስኪመስል ድረስ ሁሉ ነገር ስሜትን ለማርካት የሚጋብዝ ሆኖ በሚሰበክበትና በምልአት ማደጉ ችላ በተባለበት በዚህ ወቅት ፍልሰታ ማርያምንቃ! የተፈጠርከው ለምልአት ነው ይለናል

የእመቤታችን በሥጋዋ ወደ ሰማይ መፍለስ ማለት እያንዳንዱ ክርስቲያን ለተሰጠው ክርስቶሳዊ ጸጋ ታማኝ እስከሆነ ድረስ የማይቀር የወደፊት ክስተት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ "የሚጠፋ ሟች አካል ሆኖ የተዘራው የማይጠፋ ሕያው አካል ሆኖ ይነሣል። በውርደት የተዘራው በክብር ይነሣል።" ይላል (1ቆሮ.15:42)። እመቤታችንም በተራዋ "እግዚአብሔር እኔን ዝቅተኛ አገልጋይቱን ተመልክቷልና ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ የተመሰገንሽ ነሽ ይለኛል" አለች (ሉቃ.1:48)። የትውልድ ክፍል ሆኖ የሚሰማው ግለሰብ ሁሉ እሷን የተመሰገንሽ የሚላትም ይህ እውነት በርሷ ስለተፈጸመ ነው፤ ማለትም የእግዚአብሔርን ቃል ጸንሳ ወልዳ ለዓለም (ለእኛ) ስላበረከትችና እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ መሆን ምን መሆኑን ስላሳየችን፤ የተዘጋጀልን ዘላለማዊ ክብርም ምን እንደሚመስል በፍልሰቷ እግዚአብሔር ስላሳየን በምህለላችን እሷን ብፅእት እያልን እግዚአብሔርንም ለታላቅ ሥራው በርሷ እናከብረዋለን።

እግዚአብሔር ይህን የሥጋ ፍልሰት አስቀድሞ ለእመቤታችን ለምን አደረገ ካልን፤ ምናልባት ከመጀመሪያውኑስ አንደኛ ልጁ ከርሷ እንዲወለድ ለምን መረጣት ወደሚል ተመሳሳይ ሀሳብ ሊያመራን ይችል ይሆናል። እውነቱ ግን አንድ ሰው ሕይወቱ በክርስቶስ ጸጋ የመስመጡን ያህል በክርስቶስም ክብር ከፍ ይላል፤ እንዲሁም ምድራዊ ሕይወቱ በክርስቶስ ሕይወት ውስጥ ሥር የመስደዱን ያህል በሰማያዊው ክብርም የላቀ ስፍራን ይይዛል። ታዲያ ሕይወቱ በእግዚአብሔር ጸጋ የሰመጠ፤ በአናኗሩም ከጽንሰት እስከ መስቀል ግርጌ፤ ብሎም የሰጠውን የመንፈስ ቅዱስ ተስፋ እስከመሳተፍ ድረስ በክርስቶስ ሥር የሰደደ ከእመቤታችን ንጽሕት ድንግል ማርያም የበለጠ ማን አለ? ቅዱስ ገብርኤል ከራሱም ያይደል ከእግዚአብሔር የሆነውን መልእክት ሲያበስራት "አንቺ ጸጋን የተሞላሽ፤ ከሴቶች ሁሉ የተባረክሽ ነሽ" እንዳላት ፍልስቷም ይህንኑ እውነት ያፈካልናል "ከሰዎች ሁሉ የተባረክሽ ነሽ" እንላታለን።

ምንጭ፡ በኢትዮጲያ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሲታዊያን መነኮሳት ማኅበር ድረ ገጽ ላይ የተወሰደ

የተወሰደበት ቀን እና ሰዓት፡ ነሐሴ 12/2010 ዓ.ም/04፡50

የተወሰደበት ቦታ፡ www.ethiocist.org/maede-wongel/amharic-sunday-reflections/1211-zm

በድምጽ የቀረበውን ዘገባ ለማዳመጥ ተጫወት የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
18 August 2018, 11:55