የግንቦት 12/2010 ዓ.ም የትንሳኤ ሰባተኛ ሰንበትን ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ የግንቦት 12/2010 ዓ.ም የትንሳኤ ሰባተኛ ሰንበትን ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ  

የግንቦት 12/2010 ዓ.ም የትንሳኤ ሰባተኛ ሰንበትን ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ

እየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ ንባቦች ኣማካኝነት ወደ እያንዳዳችን በመምጣት የሚያስፈልገንን ይሰጠናል

የግንቦት 12/2010 ዓ.ም የትንሳኤ ሰባተኛ ሰንበትን ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

የእለቱ ምንባባት

1.     ሮሜ 10፡ 1-13

2.    1ኛ ጴጥ 3፡ 15-22

3.    ግ ሓዋ 1፡15-26

4.     ሉቃስ 24፡45-53

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር የትንሳኤ ሰባተኛ ሰንበትን እናከብራለን። በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ ንባቦች ኣማካኝነት ወደ እያንዳዳችን በመምጣት የሚያስፈልገንን ይሰጠናል የጎደለውን ሁሉ ይሞላልናል በእርሱም ቃል እንድንኖር ያበረታታናል።

በዚሁም መሠረት እንግዲህ በመጀመሪያ ንባብ ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች መልዕክቱን ሲልክ የእርሱ የልብ ፍላጎትና የእርሱ ልመና የእስራኤል ሕዝብ እንዲድን መሆኑን ይናገራል። ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ የእስራኤል ሕዝብ እግዚኣብሔር በኣንድያ ልጁ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የገለጠውን እውነትን ከመቀበል ይልቅ ሕግን በመጠበቅ ብቻ ደህንነትን ለማግኘት እንደሚያስቡ ተረድቷል። ነገር ግን በዚሁ በዛሬው የሮሜ መልእክት ምዕራፍ 10፡4 ላይ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ራሱ የሕግ ፍጻሜ መሆኑን ይናገራል። ሰው በእርግጥም ሕግን በመፈፀም ብቻ የሚድን ቢሆን ኖሮ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር መምጣት ምንም ባላስፈለገ ነበር ነገር ግን ሰው በሕግ ብቻ ለመጽደቅ ባለመቻሉ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር መምጣትና ሰማይና ምድርን ማስታረቅ የግድ ነበር። ስለዚህ ጽድቅን ለማግኘት በመጀመሪያ ደረጃ እግዚኣብሔር ኣብ ዓለምን እጅግ ስለወደደ ዓለምንና በውስጧ የሚኖሩትን ልጆቹን ኣንዲያድን ኣንድያ ልጁን ወደ እኛ መላኩን በሁለተኛ ደረጃ ይህ የኣብ ኣንድያ ልጅ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ኣማካኝነት ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱንና ወደ ምድር መምጣቱን በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ  እኛን ለማዳን ሲል መሰቃየቱን መሞቱን መቀበሩን በሦስተኛውም ቀን ሞትን ድል ነስቶ መነሳቱን ማመን ያስፈልጋል። ስለዚህ ይህ ኣገላለጽ ጽድቅ በሕግ በኩል የሚመጣ ሳይሆን በ እግዚኣብሔርና በልጁ በማመን የሚመጣ መሆኑን የስገነዝበናል። ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ወደ ገላትያ 2፡16 ላይ በጻፈው መልዕክት እንዲህ ይላል፣ ነገር ግን ሰው በእየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንድማይሆን ኣወቅን፣ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ሰለማይጸድቅ፣ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ እየሱስ ኣምነናል ይላል። እዚህ ላይ ኣንድ መገንዘብ ያለብን ጉዳይ ቢኖር በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ኣምነናል ብለን ስንናገር እርሱን በሙሉ ልብ ተቀብለናል እርሱን ወደናል ማለታችን ነው። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን የተቀበለ እርሱን የወደደ ደግሞ በዮሓንስ ወንጌል 14፡15 ላይ እንደሚለው የእርሱን ቃል ይጠብቃል እንደ ፈቃዱም ይኖራል፣ ስለዚህ ጽድቅን የምናገኘው በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በማመናችን ቢሆንም እምነታችን የሚለካው ለእርሱ ያለን ፍቅር የሚለካው ደግሞ እርሱ የሰጠንን ትዕዛዝ ተግባራዊ በማድረጋችን ነው። በማቴዎስ ወንጌል 7፡21 ላይ በሰማያት ያለውን የኣባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማይ የሚገባ ኣይደለም ይላል ስለዚህ እኛም በዕለታዊ ተግባራችን እግዚኣብሔርንም ሆነ ሰውን ደስ የሚያሰኝ  ኣካሄድ በመሄድ የመንግሥተ ሰማይ እጩዎች እንድንሆን ተጠርተናል። በዛሬው በሁለተኛ ንባብ የመጀመሪያው የሓዋርያው ጴጥሮስ መልዕክት ምዕራፍ 3 ላይ ሲነበብ እንዳዳመጥነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ኣምነን ከተቀበልነው በልባችን እንድናስቀምጠውና እንድንቀድሰው ይጠይቀናል። እንድንቀድሰው ብለን ስንናገር እኛ በምንሰራው በየትኛውም ሥራ የእግዚኣብሔር ሥም የሚከብርብበትን እሱ በእኛ ላይ ያለው ዕቅድ ተፈፃሚ የሚሆንበትንና  እርሱ በኛ ሕይወት ውስጥ ደምቆ እንዲታይ እንትጋ ማለቱ ነው።  ይህም ማለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ወደ ውስጣችን ወደ ልባችን ሲግባ እኛነታችን በሙሉ ይቀደሳል ከዛም ይህ የተቀደሰውን እኛነታችንን ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ሌሎችም እኛን ተመልክተው በእኛ ሕይወት እንዲቀደሱና እነሱም በተራቸው ደግሞ ለሌሎች ቅድስና ምክንያት እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህንንም ለማድረግ ይላል ቅዱስ ሓዋርያው ጴጥሮስ በመልዕክቱ ሁል ጊዜ በልባችን የተዘጋጀንና በየዋህነት የምንንቀሳቀስ መሆን ይጠበቅብናል። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በየዋህነት ራሱን ስለ እኛ ሲል ኣሳልፎ በመስጠቱ እኛ ጽድቅን ኣገኘን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ስለሰራው መልካም ነገር ሁሉ  በሰዎች ዘንድ ተኮነነ ተሰቃየ በስተመጨረሻም በመስቀል ላይ ተሰቀለ። ምናልባት ይለናል ቅዱስ ሓዋርያው ጴጥሮስ እኛም በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በማመናችንና እርሱን በልባችን በማስቀመጣችን ብሎም በመቀደሳችንና ይህንንም ቅድስና ለሌሎች መዳኛ እንዲሆን በዕለት ተዕለት ኑሮኣችን ለመተግበር ጥረት በማድረጋችን ሌሎችም የዚህ ቅድስና ተካፋይ እንዲሆኑ በማበረታታታችን በሰዎች ዘንድ ተቃውሞና ስድብ ብሎም እንግልት ሊያደርስብን ይችላል ይህም ቢሆን ግን ይላል የቅዱስ ሓዋርያው ጴጥሮስ መልዕክት በቁጥር 17 ላይ ክፉ ስለማድረግ ሳይሆን በጎ ስለማድረግ መከራን ብትቀበሉ ይሻላችኋል ይለናል። ይህንን ማድረግ ከቻልን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በመከራ ውስጥ በማለፍ ዘለዓለማዊ ክብርን እንደተቀዳጀ እኛም የዚሁ የዘለዓለማዊ ክብር ተካፋዮች እንሆናለን። በዛሬው በሉቃስ ወንጌል ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለሓርያቶቹ ኣእምሮኣቸውን እንደከፈተላቸው ይናገራል ይህም ማለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለምን ዓላማ ወደዚህ ምድር እንደመጣና ስለ እርሱ በነቢያት መጽሓፍ የተጻፈው ሁሉ በተግባር መፈጸሙን ያስረዳቸዋል ምክንያቱም ገና ከመጀመሪያው ኣንስቶ ሓዋርያቶች ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የነበራቸው ግምት ሌላ ነበር እርሱን ይገምቱ የነበረው እስራኤልን ከሮማውያን ኣገዛዝ ነፃ የሚያወጣ የፖለቲካ መሪ አንጂ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ወደ እዚህ ምድር የመጣበትን ትክክለኛ ምክንያት ኣልተረዱም ነበር። ለዚህ ነው ቅዱስ ሓዋርያው ጴጥሮስ በማቴዎስ ወንጌል 16፡23 ላይ ተጠቅሶ እንደምናገኘው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለካህናት ኣለቆች ተላልፎ እንድሚሰጥ ከእነሱም ብዙ መከራ እንደሚቀበል በስተመጨረሻም በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እንደሚገደል ሲነግራቸው ጌታ ሆይ ይህማ በፍጹም በኣንተ ላይ ኣይድረስብህ ይህ ለኣንተ የተገባ ኣይደለም እያለ ይገስፀው የነበረው ለዚህ ነው። ዛሬ ግን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ይህ ሁሉ ትንቢት መፈፀም ይገባው እንደነበረና እንደተፈፀመም ይህንን የሚያስተውሉበትን ኣእምሮኣቸውን ከፈተላቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ወንጌል የሚያሳስበን ማንኛውም ነገር ይሁን በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በኩል ካልሆነ በስተቀር ዋጋ እንደሌለው ያስተምረናል ምክንያቱም ሓዋርያቶች ሁል ጊዜም ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ነበሩ ነገር ግን ጠለቅ ያለ ማስተዋል በፍጹም ኣልነበራቸውም በኋላ ግን እርሱ ኣእምሮኣቸውን ከከፈተው በኋላ ሁሉን ኣስተዋሉ በተለይም ደግሞ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ቃል እንደገባላቸው ኃይልን ከላይ ከሰማይ ከላከላቸው በኋላ ማስተዋልን ብቻም ሳይሆን ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በድፍረት በዓለም ሁሉ ለመመስከር ቻሉ ሕይወታቸውን ለእርሱ ኣሳልፈው ለመስጠት ለራሳቸው ቃል ገቡ። እንግዲህ ዛሬም እኛ የሚያስፈልገን ይህ ነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ልባችንንና ኣእምሮኣችንን እንዲያበራልንና እስከ መጨረሻ የእርሱን መንገድ ለመከተል ብሎም ዘወትር በቃሉ ለመኖርና ስለ እርሱ እውነተኛ ምስክሮች ሆነን ለመጓዝ እንድንችል ኣጥብቀን እንድንለምን ያስፈልገናል። በተለይም ይህ ለማርያም በተሰጠ ወር ኣካሔዳችንና ኣኗኗራችን የእርሷን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እንዲመስል የበኩላችንን ጥረት እንድናደርግ ያስፈልገናል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሕይወታችን ደስታችን ተስፋችን የሆነች ዘወትር ባዘንን ጊዜ ደስታን ተስፋ በቆረጥን ጊዜ የምሥራችን በተጨነቅን ጊዜ እፎይታን የምታመጣ እናታችን ናትና ዘወትር ወደ እንሷ እንድንሮጥ ያስፈልጋል። እንሷ በቃና ሰርግ ወይን እኮ የላቸውም ብላ በራሷ ተነሳሽነት እንዳማለደቻቸው ዛሬም እኛ እያንዳዳችን የሚያስፈልገንን ጸጋ ከኣንድ ልጇ ታሰጠናለችና ያለ ምንም ተስፋ መቁረጥና መጨነቅ ወደ እርሷ እንቅረብ እሷም ከጭንቃችን ሁሉ ትገላግለናለች ታበረታታንማለች።

 

20 May 2018, 15:04