ፈልግ

ሕይወታችንን መለወጥ ሕይወታችንን መለወጥ  (AFP or licensors)

ሕይወታችንን መለወጥ

ሞቅ ሲለንና ሲሰማን አልፎ አልፎ ሕይወታኝን ለመለወጥ በመሞከር ጥረት እናደርጋን። ከልባችን ተጸጽተን «ዛሬስ ከዚህ ጉድለት እጠነቀቃለሁ፣ አሁንስ ኑሮዬን ላሻሽል ይገባኛል” ብለን ፎክረን በመነሳት በመልካም ፈቃድ እንጀምራለን። ጥቂት ጊዜ ቆየት ብለን ግን ተግባር የሌለው ንግግር ብቻ ሆነን እንገኛለን።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

መወሰንና መጀመር በተግባር ግን ፍጻሜ የሌለው ባዶ ፉከራ ብቻ ሆነን እንቀራለን። በቀድሞ መጥፎ ኑሮአችን እንደገና እንወድቃለን። ምን ሆነን ነው የምንቀዘቅዘው? እንዳሰብነው የማንፈጽመው? ለምንድነው ውሳኔያችን የማይጸናው? ሃኬተኞች ስለሆንን ብርቱ ፈቃድ ስለሚጐድለን ማረምና መቀየር ማሻሸል ከባድ ሆኖ ይታየናል፣ ከመጥፎ ባሕርያችንና ከክፉ ዝንባሌያችን መዋደቅና መዋጋት ይሰለቸናል፣ በሥጋችን ልንጨክንበት የማንፈልግ ስለሆንን ተቃራኒው ያስጠላናል።

ሕይወታችንን መቀየር እንፈልጋለን፣ እንወዳለንም፤ ግን በቀላል መንገድ ብዙ ጥረት ሳናደርግ እምብዛም ሳንታገል እንዲሆንልን እንፈልጋለን። መጥፎ አመላችንን ለመተው ቁርጥ ፈቃድ ለማድረግ እንወስናለን፤ ግን ትግሉ ሲበረታብን ወደ ኋላ እናፈገፍጋለን። ቀስ በቀስ ወደ ክፉና ወደ ባሰ አዘቅት እንወድቃለን። «ሕይወትህን ለመቀየር የሚከተሉት ሁለት ነገሮች ያስፈልጉሃል…

ሀ. ከክፉ ዝንባሌ ጨርሰህ መለየት፣

ለ. የሚያሰፈልግህን መንፈሳዊ መንገድ በብርቱ መንፈሳዊ ምኞት መፈለግ ያስፈልጋል´ ይላል ቅዱስ መጽሐፍ።

ከሁሉ አስቀድሞ እንግዲህ መጥፎ አመላችንን ስንተው፤ ቀጥለን የማያስፈልገንን መልካም ልምድ መሸመት ይገባናል። ኑሮአችንን ልናሻሽል ብንፈልግ አስቀድመን ጉድለታችንን በማጥፋት ጽድቅን ባለን ኃይል ሁሉ መፈለግ አለብን። እንደዚህ ካላደረግን ሕይወታችን ይለወጣል ብለን አናስብ፤ መጥፎ ዝንባሌአችንን ሳናሸንፍ ቁም ነገር ፈጽሞ አናደርግም። ራሳችንን ካላሸነፍን የቅዱሳንን ፈለግ ልንከተል አንችልም። ሕይወታችን የማይለወጠው ከስንፍናችን ብዛት ነው። ጠዋት የወሰንነውን ማታ ሳንፈጽመው ውዝፍ ሆኖ ይቀራል፤ ዛሬ ተናዝዘን ነገ በኃጢአት የምንወድቅ ቁርጥ ፈቃድ ስለሚጐድለን ነው።

በዚህ ዓለም መጥፎ ልምዶችን መተው፣ ሕይወታችንን ማሻሻል የመንፈሳዊ ኃይል ጦር መሣሪያ መልበስ ብርቱ ሆኖ ከታየን በወዲያኛው ዓለም በንስሐ ቦታ ስቃይ ፊት ወይም ደግሞ በገሃነመ እሳት ቅጣት ፊት ምን ይውጠናል? እንዴት አድርገን እንሸከመዋለን? አሁን ሕይወታችንን ለመቀየር ጥረቱና ትግሉ ውጊያው ቀላልና የሚቻል ነው። ከሞትን በኋላ ግን በኃጢአት ምክንያት የሚጠብቀን ቅጣት ለዘለዓለም ብርቱ ነው።

የወዲያኛው ዓለም ስቃይ ኃይሉና ሚዛኑ ይህን ያህል ይሆናል ተብሎ የማይለካ ከባድና የማይቻል ነው። በሕይወታችን ዘመን በቀላል ተጋድሎ ያልካስነው ሥፍር ቁጥር የሌለው የኃጢአታችን ዕዳ ክምችት ከዚህ ለቀን ስንሄድ ሳንወድ የግድ በብርቱ ቅጣት እንከሰዋለን። ዛሬ ሕይወታችንን ለማሻሻል አስበን ካልሠራን በወዲያኛው ዓለም እንዴት ያለ ከባድ መከራ እንደሚደርስብን እናስብ። ሥጋዊ ሕይወታችን እየተሻሻለ ሲሄድ መንፈሳዊ ሕይወታችንም እየተሻሻለ መሄድ አለበት። ሕይወታችንን ለማሻሻል ከፈለግን ሃከተኞች አንሁን፤ ያጋጠመንን ችግር በመንፈሳዊ ተጋድሎ እያሻነፍን ሐሳባችንን እንፈጸም። «ሕይወቴን አሻሽላለሁ መንገዴን እቀይራለሁ” የሚለውን ውሳኔ ታጥቀንና ቆርጠን ወደ ፍጻሜ እናድረሰው።

 

 

16 May 2024, 11:24