ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቁርጠኛ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በዚህ ወቅት የሚያሳዩት ቁርጠኝነት የተሻለ የወደፊት ሕይወትን ለመፍጠር የሚያስችል እንደሆነ፥ በሰሜን ጣሊያን ሚላን ከተማ ለሚገኝ ታዋቂ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ጥናት ተቋም ፕሬዝዳንት ለሆኑት ለሊቀ ጳጳስ አቡነ ማሪዮ ዴልፒኒ በላኩት መልዕክት ገልጸዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን መልዕክታቸው የላኩት የትምህርት ተቋሙ የተቋቋመበት 100ኛ ዓመት እሑድ ሚያዝያ 6/2016 ዓ. ም. ማስቆጠሩን ምክንያት በማድረግ ነው። እንደ ዩኒቨርሲቲው ድረ-ገጽ ገለጻ መሠረት የበዓሉ ዝግጅት ዋና ዓላማ የአዲሶቹን ትውልዶች የወደ ፊት ፍላጎት ለመቃኘት እና ይህም የሕይወት ትርጉም ፍለጋ እና የውይይት መድረክ መክፈቻ እንደ ሆነ ተገልጿል።
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በመልዕክታቸው፥ መጪው ጊዜ ቀድሞ የሚመጡ የሚመስሉ ቦታዎችን እንዳሉ ተመልክተው፥ ከእነዚህ ቦታዎች መካከል አንዱ የዩኒቨርሲቲው ዓለም እንደሆነ በማስረዳት፥ “የነገ ባለሙያዎች የሚዘጋጁበት እና ብዙውን ጊዜ ለሰው ልጅ ቤተሰብ ዕድገት እጅግ ወሳኝ የሆኑ የፈጠራ ውጤቶች የሚታዩበት የምርምር ማዕከል በመሆኑ ነው” በማለት ገልጸዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማበረታቻ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዩኒቨርሲቲው የተቋቋመበትን 100ኛ ዓመት ባከበረበት እሑድ ሚያዝያ 6/2016 ዓ. ም. ረፋዱ ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች ጋር ወደ እመቤታችን ቅድስት ማርያም የሰማይ ንግሥት የጋራ ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት ለዩኒቨርሲቲው ልዩ ሰላምታ ማቅረባቸው ይታወሳል። በዕለቱ ባሰሙት ንግግርም፥ ዩኒቨርሲቲው ለዛሬው ወጣት ትውልድ እና ለአዳዲስ የኅብረተሰብ ፈተናዎች ዘወትር ትኩረት እና አስፈላጊውን የስልጠና አገልግሎት በመስጠት ተልዕኮውን በታማኝነት እንዲቀጥል የግል ማበረታቻ ምክር የሰጡ ሲሆን፥የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊንም በአካዳሚው ዘርፍ ያሉ ወጣቶች ተግዳሮቶችን ተገንዝበዋል።
የዛሬው ቁርጠኝነት ሁኔታዎችን ሊቀይር ይችላል
“ዛሬ አስፈላጊ እና የሚጠበቁ ጥረቶች በወደ ፊት ሕይወት ላይ ያተኮሩ ናቸው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ነገር ግን እንደዚሁም አስጊ ደመናዎች ያሉ እንደሚመስል ተናግረው፥ ወጣቶች በምርምር ዘርፍ ይህን ውጥረት በልዩ ክብደት እንደሚገነዘቡት እና እንደሚለማመዱት አስረድተዋል።
“በዚህ አድማስ አንድ ሰው ያለፈ ጊዜ እስረኛ ሆኖ ሊቆይ እንደማይችል ወይም ራሱን በቸልተኝነት እና በችኮላ ወደ ነገ ማምጣት አይችልም” ሲሉ አስምረውበታል። “ይልቁንስ ሁሉም ነገር በዚህ ሰዓት እየተካሄደ መሆኑን የመገንዘብ ችሎታን ማሳደግ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረው፥ ዛሬ በሙላት ካልተኖረ ተጨባጭ የወደፊት ጊዜን መኖር አይቻልም” ብለዋል።
“ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የወደፊት ዓለምን መገንባት እንዲቻል ለወጣቶች ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር አጣዳፊነት” የሚለውን የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲው መሥራቾች ዓላማ ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰዋል። ብፁዕነታቸው ከዚህም ጋር ወጣቶች ከቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጋር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1984 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለመጀመሪያ ጊዜ ያከበሩት የዓለም የወጣቶች ቀን 40ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልንም አስታውሰው፥ የዓለም ወጣቶች ቀን ፍሬ እያበበ መምጣቱን በመመልከት በዓለም የወጣቶች ቀን እና ለዩኒቨርሲቲዎች በሚደረግ ሐዋርያዊ እንክብካቤ መካከል ያለው ግንኙነት እየጠበቀ እና እየተቀራረበ መምጣቱን በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል።
ለጤናማ ጥረት ትርጉም ያለው ምላሽ መስጥት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ውስጥ በተከበረው የዓለም የወጣቶች ቀን ከዩኒቨርሲቲው ዓለም ጋር ልዩ ስብሰባ ማድረጋቸውን ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰው፥ ይህን በማሰብ፥ መጪው ጊዜ ከወጣቶች ልብ ሊሰረቅ የማይችል በመሆኑ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በወጣቶች አእምሮ እና ልብ ውስጥ ለሚገኘው ትክክለኛ ጥረት ምላሽን በድፍረት መስጠት እንደሚገባ መጋበዛቸውን ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ገልጸዋል።