በዓለማችን ባለፉት አሥርት ዓመታት የዓለም አቀፍ ሃይማኖታዊ ገጽታ እየተለወጠ መምጣቱን የፔው ጥናት አመላከተ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የሃይማኖት ገጽታ መለወጥ ላይ አስተዋጽዖ ያላቸው ፈጣን የማህበራዊ፣ የባህል እና የስነ-ሕዝብ ለውጦች እየታየበት በሚገኘው ዓለማችን ውስጥ፣ በቅርብ ጊዜ የወጣው የፔው የምርምር ማእከል (በ1996 ዓ.ም. በዋሽንግተን ዲሲ የተመሰረተ እና ሥነ-ህዝብ ላይ የተለያዩ መረጃዎችን የሚሰጥ ተቋም) ሪፖርት እንደሚያሳየው የሃይማኖት ትስስር እና ስነ-ሕዝብ በጎረጎሳዊያኑ ዘመን አቆጣጠር ከ 2010 እስከ 2020 ባሉት አሥርት ዓመታት ውስጥ እንዴት እንደተለወጡ አጠቃላይ እይታን ይሰጣል ተብሏል።
እያደገ እና ብዝሃነቱ እየጨመረ የመጣው የህዝብ ቁጥር
የዓለም ሃይማኖታዊ የህዝብ ቁጥር ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን አጉልቶ ያሳየው ሪፖርቱ፥ እ.አ.አ. በ 2010 ዓ.ም. 5.9 ቢሊዮን የነበረው የህዝብ ቁጥር በ 2020 ዓ.ም. ወደ 6.9 ቢሊዮን መድረሱን በጥናቱ አመላክቷል።
ይህ ጭማሪ በአብዛኛው የተከሰተው ከፍተኛ የወሊድ መጠን እና የሃይማኖታዊ ማህበረሰቦች ቁጥር በአስገራሚ ሁኔታ እየጨመረ ባሉባቸው ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ክልሎች እየታየ ያለው የስነ-ሕዝብ አወቃቀር ልማዶች አዝማሚያ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ከአጠቃላይ የዓለም ህዝብ ቁጥር ከ 23.2 በመቶ ወደ 24.1 በመቶ በመጨመር እየተስፋፋ የመጣው የህዝበ ሙስሊሙ ቁጥር እስልምና በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን አጉልቶ ያሳያል ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ክርስትና ከአጠቃላይ የዓለም ህዝብ ቁጥር 31.2 በመቶ በመሆን አሁንም ድረስ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያለው ሃይማኖት ቢሆንም፥ ከዓለም አቀፍ የህዝብ ቁጥር እድገት ጋር አብሮ ባለመሄድ ወደ ኋላ መቅረቱ ተመላክቷል።
ከዚህም በተጨማሪ ክርስቲያኖች በብዙ ክልሎች ውስጥ ትልቅ ቁጥር ያላቸው በዓለም ላይ በእኩል ደረጃ የተከፋፈሉ ቡድኖች መሆናቸውን እና በዓለም ዙሪያ ያሉ አብዛኞቹ ሙስሊሞች ከ 50 ዓመት በታች እንደሆኑ፥ በሌላ በኩል የቡድሃ እምነት ተከታዮች ከሌሎች የሃይማኖት ቡድኖች በዕድሜ የገፉ መሆናቸው አስገራሚ ነገር ነው ተብሏል።
በአህጉራት ውስጥ ያሉ ለውጦች እና ልዩነቶች
ሪፖርቱ እደሚያሳየው ምንም እንኳን አጠቃላይ እድገት ቢኖርም በአህጉራት መካከል ያለውን ልዩነት በጉልህ እንደሚታይ ያሳየ ሲሆን፥ በተለይ አውሮፓ ሃይማኖታዊ መለያቸው እያሽቆለቆለ መምጣቱን፣ ከሃይማኖት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው የሚቆጥሩ እና አንዳንዴም “ሃይማኖት ዬላቸውም” እየተባሉ የሚጠሩት ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየበዙ መምጣቱን ይፋ አድርጎ፥ ይህ ቡድን በአሁኑ ወቅት 17 በመቶ የሚሆነውን የአውሮፓ ህዝብ እንደሚይዝ እና ይህም ሰፊ የዓለማዊነት አዝማሚያዎችን እና የማህበራዊ አመለካከቶች መለወጥን ያሳያል ተብሏል።በሰሜን አሜሪካ አሁንም ድረስ ከፍ ያለ ክርስቲያናዊ ቁርኝት እንዳለ በጥናቱ የተመላከተ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር ዓለማዊ እና ሃይማኖታዊ ያልሆኑ ማንነቶች መጠነኛ ጭማሪ ማሳየቱ፥ ይህም እምነትን እንዴት መለማመድ እና መግለጽ እንደሚቻል ያለውን ለውጥ ያሳያል ተብሏል።
አዲስ ብቅ ያሉ ልማዶች እና እንቅስቃሴዎች
በእነዚህ አስርት ዓመታት ውስጥ በተለይ በክርስትና ውስጥ ደማቅ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች መበራከታቸው የተጠቆመ ሲሆን፥ የጴንጤቆስጤ እና የወንጌላውያን ማህበረሰቦች በአፍሪካ እና በላቲን አሜሪካ በፍጥነት መስፋፋቱ በእነዚህ ልማዶች ውስጥ አዲስ ሃይልን ያቀጣጥላል ተብሏል።
በብዙ ክልሎች ፍልሰት እና ግሎባላይዜሽን ለሃይማኖታዊ ብዝሃነት መጨመር አስተዋፅዖ ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን፥ ይህም የበለጠ ብዝሃነትን ያማከለ ማህበረሰብ እንዲኖር አድርጓል ተብሏል። በአንጻሩ አንዳንድ አካባቢዎች በፈጣን ማኅበራዊ ለውጥ ውስጥ ልማዳዊ ድርጊቶች አዲስ ጠቀሜታ እያገኙ በመሆናቸው ሃይማኖታዊ መነቃቃቶች እንዳጋጠማቸው ተገልጿል።
“የሃይማኖት አልባ” ቁጥር መጨመር
በጣም እየተለመዱ ከመጡ አዝማሚያዎች ውስጥ አንዱ ሃይማኖታዊ ግንኙነት እንደሌላቸው የሚገልጹ ሰዎች መበራከታቸው ሲሆን፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይህ ቡድን በተለይ ባደጉት ሀገራት እየተስፋፋ መምጣቱ እና ዓለማዊነት በማህበራዊ አመለካከቶች ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መምጣቱ ተገልጿል።
የፔው ጥናትና ምርምር ማዕከል እንደጠቆመው ይህ ለውጥ ለሃይማኖት ተቋማት እና ፖሊሲ አውጪዎች በሕዝብ ሕይወት ውስጥ ስላለው የወደፊት የእምነት ሚና ጥልቅ ጥያቄዎችን እንደሚያመጣ አስታውቋል።
የፔው ዘገባ በማጠቃለያው፣ ዓለማችን በሃይማኖታዊ ማንነት ረገድ ሁለንተናዊ እና ውስብስብ እየሆነች መምጣቱን አጉልቶ በማሳየት፥ የህዝብ ቁጥር እያደገ እና እየተቀየረ እንዲሁም ሰዎች መንፈሳዊ እርካታን እንዴት እንደሚያገኙ እና ከማህበረሰባቸው ጋር እንዴት እንደሚገናኙም ጭምር ያለው ልማድ እየተቀየረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት፥ በዓለም ዙሪያ ላሉ ቤተክርስቲያናት እና የእምነት ማህበረሰቦች ለውይይት አዲስ መነሳሳትን እንዲሰጡ እና ፍላጎቶቹን በተሻለ ሁኔታ ለማሟላት ስለ መንፈሳዊው ገጽታ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲያሳድጉ ጥሪ በማቅረብ አጠቃሏል።