ፈልግ

የዓለም የምግብ ፕሮግራም በሱዳን፣ ታላቋ ካርቱም አካባቢ በምትገኘው ኦምዱርማን የምግብ እርዳታ ሲሰጥ   የዓለም የምግብ ፕሮግራም በሱዳን፣ ታላቋ ካርቱም አካባቢ በምትገኘው ኦምዱርማን የምግብ እርዳታ ሲሰጥ  

ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሱዳን ህዝብ እየተባባሰ ለመጣው የምግብ ዋስትና እጦት መጋለጡ ተነገረ

የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) ከዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ጋር በመሆን በቅርቡ ባወጡት ሪፖርት ላይ እንደተመላከተው በተለያዩ ሀገራት ለተከሰተው የረሃብ ችግር ዋነኛው መንስኤ ግጭት መሆኑ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሱዳን ላለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው የእርስ በርስ ግጭት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ወደ ደቡብ ሱዳን እንዲሰደዱ እና 12.4 ሚሊዮን ዜጎች እንዲፈናቀሉ ያደረገ ሲሆን፥ በቀጠናው ያለው ግጭት ያደረሰውን አደጋ አስመልክቶ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደዘገበው 57 በመቶው የሱዳን ህዝብ “ከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት” እንዳጋጠማቸው ገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደገለጸው በአስቸጋሪ የእርስ በርስ ግጭት፣ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ እና የኢኮኖሚ ውድቀት ውስጥ ያለችው ሱዳን፥ በዓለም ላይ በከፍተኛ ሁኔታ በረሃብ ከተጠቁ አምስት ሃገራት ቀዳሚውን ስፍራ እንደያዘች አመላክቷል።

ጦርነቱ ቀጥሎ ባለበት፣ በአከባቢው የጎርፍ መጥለቅለቅ የተለመደ በሆነበት እና የኢኮኖሚ ሁኔታዎች እያሽቆለቆለ ባለበት በአሁኑ ወቅት፥ በመጪዎቹ የክረምት ወራት ነገሮች እየተባባሱ ይሄዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና የምግብ እና እርሻ ድርጅት የምግብ ዋስትና እጥረቱን ምንነት ለመገመት ወቅታዊ መረጃዎችን የሚተነተን ሪፖርት ሰሞኑን ይፋ ያደረጉ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ፍልስጤም፣ ማሊ እና ሄይቲ አፋጣኝ ሰብዓዊ ዕርዳታ ካላገኙ ከፍተኛ የረሃብ እና የሞት ሥጋት እንደሚጠብቃቸው ተጠቁሟል።

የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኩ ዶንግዩ አፅንዖት ሰጥተው እንደተናገሩት “ረሃብ ሚሊዮኖችን እያጠቃ የሚገኝ ዕለታዊ ድንገተኛ አደጋ መሆኑን ጠቁመው፥ ህይወትን ለማዳን እና ለማስቀጠል አሁኑኑ እርምጃ መውሰድ እና በጋራ መስራት አለብን ብለዋል።

ግጭት ረሃብን ያስከትላል
ይህ የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) ከዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ጋር በመተባበር ያወጡት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ግጭት በዋናነት የረሃብን ቀውስ እንደሚያስከትል፥ ቀውሱም በአየር ንብረት ለውጥ እና በኢኮኖሚ ተግዳሮቶች እንደሚባባስ አመልክቷል።

የምግብ እና እርሻ ድርጅት የምግብ ዋስትና ትንተና ዳይሬክተር ዣን ማርቲን ባውሰር በሱዳን ቀጣይነት ያለው ረሃብ እንዳለ እና በጋዛ የረሃብ አደጋ እየጨመረ መሆኑን ያመላከቱ ሲሆን፥ እነዚህ ሁሉ ችግሮች የመጡት በግጭት እና በሰብአዊ እርዳታ እጥረት እንደሆነ አመላክተዋል።

2.1 ሚሊዮን የሚሆነው የጋዛ ህዝብ በመጪዎቹ ወራት ውስጥ ተጠናክሮ በቀጠለው ወታደራዊ ዘመቻዎች ምክንያት በሁለተኛ ደረጃ የምግብ ዋስትና እጦት ይገጥማቸዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ወደ 500,000 የሚጠጋው ህዝብ ደግሞ በአስከፊ ደረጃ ለምግብ ዋስትና እጥረት እንደሚጋለጡ ሪፖርቱ ይጠቁማል።

ሳውሳን የተባለች አንዲት እናት እና አርቲስት ለዓለም የምግብ ፕሮግራም እንደገለጸችው እሷና አራት ልጆቿ መፈናቀላቸውን ጠቅሳ፥ በጋዛ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ሁሉንም ነገር እንዳጡ እና በአሁኑ ወቅት ልጆቿን ለመመገብ መኮሮኒ በመፍጨት ዳቦ እንደምትሰራ ገልፃለች።

እየተቃረበ የመጣው የመጨረሻ ቀን
ከዚህም በተጨማሪ እንደ ጋዛ እና ሱዳን አካባቢዎች ያሉ ሰዎች ሰብዓዊ የምግብ አቅርቦት ሥራዎች እጥረት እና የሰብአዊ እርዳታን በቀላሉ አደገኛ በሚያደርጉ ጂኦግራፊያዊ ሁኔታዎች ምክንያት እርዳታ ማግኘት እንዳልቻሉ ተነግሯል።

የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት እንዲሁም የዓለም የምግብ ፕሮግራም በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ የዓለም ማህበረሰብ ለምግብ እና ለስነ-ምግብ ነክ ሰብአዊ እርዳታ የሚሰጠውን ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሳድግ እና ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ግፊት እንዲያደርግ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ሲንዲ ማኬን በበኩላቸው ይሄንን አስከፊ ረሃብ ለመከላከል የሚያስችሉ አማራጭ መንገዶች በፍጥነት በመዘጋታቸው አስቸኳይ፣ ቀጣይነት ያለው የምግብ ዕርዳታ እና የማገገሚያ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን በአፅንዖት ገልጸዋል።
 

18 Jun 2025, 16:31