ፈልግ

ፍልስጤማውያን በሰሜናዊ የጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ቤታቸውን ለቀው ሲሸሹ አንዳንድ ንብረቶቻቸውን ይዘው ለመውጣት ጥረት ያደርጋሉ  ፍልስጤማውያን በሰሜናዊ የጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ቤታቸውን ለቀው ሲሸሹ አንዳንድ ንብረቶቻቸውን ይዘው ለመውጣት ጥረት ያደርጋሉ  

በጋዛ በተፈጸመ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸው ተነገረ

ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ሐሙስ ዕለት እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 150 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሃማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ባለስልጣናት ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እስራኤል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የገደለው ለቀናት የዘለቁ ከባድ ጥቃቶችን ተከትሎ በጋዛ ሰርጥ ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ መክፈቷ ተነግሯል። የዓይን እማኞች እንደጠቆሙት እስራኤል በጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ በፈጸመችው ጥቃት 13 ሕጻናትን ጨምሮ በርካቶች መገደላቸውን ተናግረዋል።

የእስራኤል ጦር ይሄንን የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻውን “የጌዲዮን ሰረገላዎች ኦፕሬሽን” በማለት የሰየመው ሲሆን፥ ይህ ጥቃት የተፈጸመው በኳታር፣ ዶሃ በሐማስ እና በእስራኤል መካከል አዲስ ዙር የጋዛ የተኩስ አቁም ድርድር እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው።

አንድ የሀማስ ባለስልጣን ቅዳሜ ዕለት ለሮይተርስ እንደተናገሩት አዲስ የተኩስ አቁም የውይይት ዙር መደረጉን ያረጋገጡ ሲሆን፥ ሁለቱ ወገኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በሁሉም ጉዳዮች ላይ እየተወያዩ ነው ብለዋል። ነገር ግን፣ ምንም እንኳን ሸምጋዮች ድርድሩን ስኬታማ እንዲያደርጉ ሁሉም ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም አሁንም ድረስ “በጠረጴዛው ላይ የቀረበ ምንም ዓይነት ነገር ዬለም” ብለዋል።

የእስራኤል መከላከያ በጋዛ ሊያደርግ ካቀደው ሰፊ ቦታዎችን በቋሚነት የመቆጣጠር ውጥን በፊት የሃማስ ተዋጊዎች እና መሰረተ ልማቶች ናቸው በሚሏቸው ላይ የቦምብ ድብደባውን አጠናክሮ ቀጥሏል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በሐማስ ላይ ወታደራዊ ጫና በማጠናከር ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል ጋዛን ሲገዛ የቆየውን ታጣቂ ቡድን ለማጥፋት ቃል መግባታቸውን ተከትሎ እንደሆነ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወሩ መጀመርያ ላይ ሃማስን "ለማውደም" እንዲቻል ጋዛን ለመውረር እና በቁጥጥር ስር አውሎ ማቆየት የሚያስችል ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ እንደሚያካሄዱ ዝተው ነበር።

“የጌዲዮን ሠረገላ ዘመቻ” የተጀመረው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤልን ሳያካትቱ በባሕረ ሰላጤው አገራት ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ሲሆን፥ የትራምፕ ጉዞ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ውጤት እንደሚያመጣ ወይም ለጋዛ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደገና የመጀመር እድልን ይጨምራል የሚል ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።

እስራኤል ላለፉት 10 ሳምንታት ምግብ፣ ውሃ እና ነዳጅን ጨምሮ ወደ ጋዛ ምንም ዓይነት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች ሙሉ በሙሉ እንዳይገቡ መከልከሏ የሚታወቅ ሲሆን፥ ሳውዲ አረቢያ እና ኢጣሊያ የተኩስ አቁም ጥሪ በማቅረብ ከዓለም አቀፍ ድምጾች ጋር ተቀላቅለዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ ሃማስ ቅዳሜ ዕለት አዲስ የተኩስ አቁም ድርድር ከተካሄደ በኋላ ተጨማሪ ታጋቾችን ለመልቀቅ ሃሳብ ማቅረቡ ተነግሯል።

እንደ ጎረጎሳዊያኑ የዘመን አቆጣጠር ጥቅምት 7 ቀን 2023 ዓ.ም. የሃማስ ታጣቂ ቡድን እስራኤል ላይ ጥቃት አድርሶ 1,200 ሰዎች መገደላቸውን እና 251 ሰዎች መታገታቸውን ተከትሎ የእስራኤል ጦር ሃማስን ለማጥፋት ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሩ ይታወሳል።

እስካሁን ድረስ በጋዛ ቢያንስ 53,000 ሰዎች በእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ መገደላቸውን በሃማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
 

19 May 2025, 16:40