ፈልግ

አዲስ አበባ ከሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት ጊቢ ውስጥ የአፍሪካ ህብረት ባንዲራዎች ሲውለበለቡ የሚያሳይ የማህደር ምስል አዲስ አበባ ከሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት ጊቢ ውስጥ የአፍሪካ ህብረት ባንዲራዎች ሲውለበለቡ የሚያሳይ የማህደር ምስል  

ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የሰላም፣ የአብሮነትና የልማት ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሄደ

በአዲስ አበባ የተካሄደው 3ኛው ዓለም አቀፍ የሰላም፣ የአብሮነት እና የልማት ጉባኤ ዓለም አቀፍ የእምነት መሪዎችን በማሰባሰብ እንደ ሰላም ግንባታ፣ የአየር ንብረት ፍትህ እና የሃይማኖት ነፃነት በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር የተደረገበት ሲሆን፥ በጉባኤው ላይ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠንካራ ተሳትፎን አድርጋበታለች።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት 3ኛው ዓለም አቀፍ የሰላም፣ የአብሮነት እና የልማት ጉባኤ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ግንቦት 05 እና 06/2017 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው ሂልተን ኢንተርናሽናል ሆቴል የተካሄደ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የጀመረችው አገራዊ ምክክር ውጤታማ እንዲሆን የሃይማኖት አባቶች ሚና የጎላ መሆኑን በተጠቆመበት በዚህ ጉባኤ ላይ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ከ80 በላይ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ የሀገር በቀል ዕውቀት እና የባሕል መሪዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና ተመራማሪዎች በኮንፈረንሱ ላይ እንደታደሙ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉኀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ጉባኤውን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ጉባኤው አፍሪካ የኮንፈረንስ ማዕከል እንድትሆን ዕድል እንደሚፈጥር በመግለጽ፥ በ2063 የአፍሪካን የልማት አጀንዳዎችን ለማሳካትም የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ያስችላል ብለዋል።

እንደ ጠቅላይ ጸሐፊው ገለጻ ከኮንፈረንሱ የሚገኙ ውጤቶች ተለይተው በአፍሪካ ኅብረት እና የቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ እንዲቀርቡ እና ለፖሊሲ አውጭዎች፣ ለሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅቶች፣ ለልማት እና ማኅበራዊ ጉዳዮች በመነሻ ግብዓትነት ይቀርባሉ ተብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ በእምነት ቡድኖች መካከል አንድነትን እና ትብብርን ለመፍጠር ያለመው ይህ ዝግጅት የአፍሪካ ህብረት በቅርቡ የ ጂ20 አባል ሆኖ በተካተተበት ወቅት ላይ መደረጉ ልዩ እንደሚያደርገውም ተገልጿል።

‘ዘላቂ የልማት ግቦች፣ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 እና የ 2025 የደቡብ አፍሪካ የጂ20 ጉባኤ አጀንዳዎች’ በሚል ጭብጥ ውይይት ያደረገው እና “ሌሎች እንዲያደርጉልህ በምትፈልገው ልክ ለሌሎች አድርግ” በሚለው “ወርቃማው ህግ” እና “ኡቡንቱ” ተብሎ በሚታወቀው የአፍሪካ ፍልስፍና መንፈስ የተካሄደው ይህ ጉባኤ በርካታ ሃይማኖታዊ ማህበረሰቦችን አንድ ላይ አሰባስቧል።

በጉባኤውም ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ባስተላለፋት መልዕክት የሃይማኖት መሪዎች ለአገር የሰላም ግንባታ ሚናቸው የጎላ መሆኑን በመግለጽ፥ በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ የሃይማኖት አባቶች ያላቸውን የማይተካ ሚና የበለጠ ማጉላት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

ፕረዚዳንቱ በማከልም እርስ በእርስ መረዳዳትና መደጋገፍ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቀላሉ ለመወጣት እንዲሁም ሰላምና ልማትን ለማስቀጠል ወሳኝ ነው ብለዋል።

የካቶሊክ መገኘት እና ምስክርነት
በመድረኩ ላይ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የአዲግራት ሃገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑትን ብጹእ አቡነ ተስፋ ስላሴን ጨምሮ በርካታ ካህናትን፣ ገዳማዊያትን እና የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪዎች በማሳተፍ ቁልፍ በሆኑ ውይይቶች ላይ ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ አስተዋፅዖ ያደረገች ሲሆን፥ በጉባዔው ወቅት የተነሱት ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የእምነት ማህበረሰቦች ለ ጂ20 አጀንዳ ከሚያበረከቱት አስተዋጽኦ ጀምሮ ስለ ሰላም ግንባታ፣ የአየር ንብረት ተግዳሮቶች፣ የሴቶች አመራር፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር እና የሃይማኖቶች ተቋማት ለሰላም ግንባታ የሚያበረከቱት አስተዋጽዖ የሚሉት ቁልፍ ውይይቶች ተደርገዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በጉባኤው ላይ ስለ ሃይማኖት ነፃነት እና ሰብአዊ ክብር እንዲሁም የጥላቻ ንግግርን፣ ‘ዜኖፎቢያ’ ተብሎ የሚታወቀውን የውጭ ሃገራት ሰዎችን የመጥላት ስሜትን እና ሙስና መከላከል ስለሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ያተኮሩ ውይይቶች ተደርገዋል።

ብጹእ አቡነ ተስፋሥላሴ መድህን በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት “የሃይማኖት መሪዎች” ከግለሰቦች እና ከምእመናን ጋር ባላቸው ቅርበት እና ቀጣይነት ያለው ግንኙነት አንፃር ለተጀመረው የሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ያላቸውን ንቁ አስተዋፅዖ በአጽንዖት ገልጸዋል።

ጉባኤው የኢዮቤልዩ ዓመት እና “የተስፋ ነጋዲያን” በሚል መሪ ቃል እንዲሁም የቤተክርስቲያንን ተልእኮ በዘመናዊው ዓለም ምን መሆን እንዳለበት እና በሁሉም የእምነት ሰዎች መካከል ያለውን አንድነት አስፈላጊነትን ያረጋገጠው የ2ኛ የቫቲካን ጉባኤ 60ኛ ዓመትን ጨምሮ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን እየተከበሩ የሚገኙትን በዓላት አስተጋብቷል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጥረቶች
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ፣ በተለይም ሦስተኛው ሃዋሪያዊ መልዕክታቸው በሆነው ‘ፍራቴሊ ቱቲ’ የሃይማኖት ተቋማት ተባብረው መስራት እንደሚገባቸው እና ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት እንዲነግስ በተደጋጋሚ ጥሪያቸውን ሲያቀርቡ እንደነበር በጉባኤው ተነስቷል።

በጉባኤው እንደተጠቀሰው መከፋፈል እና የደህንነት እጦት በተንሰራፋበት በአሁኑ ወቅት፥ አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ሚና በመቅረጽ እና የጋራ ስነ ምግባራዊ እና መንፈሳዊ እሴቶችን ያካተተ እድገትን በማስተዋወቅ ረገድ እያደገ የመጣውን በሃይማኖት ተቋማት መካከል ያለው ትብብር ያለውን ተጽእኖ አመላክቷል።

በጉባኤው ላይ “ወርቃማው ህግ” በሰላም አብሮ ለመኖር መሰረታዊ መመሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል የተገለጸ ሲሆን፥ እነዚህ ህጎች ከአንዳንድ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች ተሽለው ስለሚገኙ እና ስለጋራ ሰብአዊ እሴቶች የሚናገር ስለሆነ ብዙ ጊዜ በሃይማኖቶች እና በሰላም ግንባታ ጥረቶች ውስጥ በተደጋጋሚ እንደሚነሳ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ ዩናይትድ ሪሊጅየስ ኢኒሼቲቨ አፍሪካ እና ዘ ጂ20 ኢንተርፌይዝ ፎረም (IF20) ከአፍሪካ ዩኒየን ሲትዝን እና ዲያስፖራ ዳይሬክተቶሬት (CIDO)፣ እንዲሁም ከአፍሪካ ህብረት የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ ካውንስል (ECOSOCC) ጋር በመተባበር፥ “የአፍሪካ የእምነት ማህበረሰብ ዘላቂ የልማት ግቦች ስኬትን ከማፋጠን እና ከማሳለጥ፣ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 እና የአፍሪካ የ2025 ቡድን 20 ሂደት ማሳካት” በሚል ጭብጥ ላይ ያተኮረው 3ኛው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሀመድ ዓሊ የሱፍ፣ የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ፣ የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች፣ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት መሪዎች፣ አምባሳደሮች፣ ምሁራን፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ኃላፊዎችና ሌሎችም ታድመዋል።

3ኛው ዓለም አቀፍ የሰላም፣ የአብሮነት እና የልማት ጉባኤ በእምነት ተቋማት መካከል ድልድይ በመገንባት እና ለድሆች፣ ለተገለሉት እና ለምድራችን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሲሰሩ ለነበሩት እና ከዚህ ዓለም ድካም ላረፉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮን የህሊና ጸሎት በማድረግ ተጠናቋል።
 

19 May 2025, 14:59