ፈልግ

አባ ሪፍታ ባዳር በዮርዳኖስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀበት አከባቢ የተሰራው ቤተክርስቲያን ጥር 2 በተመረቀበት ወቅት ንግግር ሲያደርጉ አባ ሪፍታ ባዳር በዮርዳኖስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀበት አከባቢ የተሰራው ቤተክርስቲያን ጥር 2 በተመረቀበት ወቅት ንግግር ሲያደርጉ 

አባ ሪፋት ባዳር ‘በቅድስት ሀገር ያለው ተስፋ በዮርዳኖስ ውስጥ ሊገኝ ይችላል’ ማለታቸው ተነገረ

በቫቲካን ‘ዮርዳኖስ፡ የክርስትና ተስፋ’ በሚል ጭብጥ በመጪው ቀናት ከሚካሄደው ዐውደ ርዕይ በፊት፥ በኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓት ተከታይ ቤተክርስቲያን ካህን የሆኑት ዮርዳኖሳዊው አባ ሪፋት ባዳር አገሪቱ ለስደተኞች እንዴት ተስፋ እንደምትሰጥ ገልጸው፥ መንፈሳዊ ነጋዲያን በተለይ ዮርዳኖስ የ2030 ኢዮቤልዩ በዓል ከማክበሯ በፊት ሃገሪቷ የክርስትናን መሠረት መሆኗን እንዲገነዘቡ ጋብዘዋል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እ.አ.አ. በ2030 የሚዘጋጀው ኢዩቤልዩ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ጀምሮ ከ2000 ዓመታት በኋላ የሚከበር ሲሆን፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ታሪክ ያላት ቅድስት ሀገር ዮርዳኖስ ለመንፈሳዊ ነጋዲያን እና ለአደጋ ተጋላጭ ሰዎች ተስፋ እና እምነትን ትሰጣለች ተብሏል።

በዮርዳኖስ የሚገኘውን የካቶሊክ የጥናት እና የመገናኛ ብዙሃን ማዕከልን የሚመሩት እና በኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓት ተከታይ ቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት ዮርዳኖሳዊው የሮማ ካቶሊክ ካህን አባ ሪፋት ባደር ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ያላቸውን ሃሳብ አጋርተዋል።

አባ ሪፋት ከዚህም በተጨማሪ ከቅድስት ሀገር፣ ከዮርዳኖስ እና ከመካከለኛው ምስራቅ የተውጣጡ ዜናዎችን፣ አስተያየቶችን እና መጣጥፎችን የሚያቀርብ ‘አቦና ኦርግ’ (abouna.org) የተባለውን ድህረ ገጽ በአረብኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚዘጋጀውን ክፍል የሚመሩ ሲሆን፥ በቃለ ምልልሳቸው ወቅት በሮም እየተከበረ በሚገኘው የኮሚዩኒኬሽን ኢዮቤልዩ ላይ ስለነበራቸው ቆይታ፣ ከቅዱስ አባታችን ጋር ስላሳለፉት ጊዜ፣ እንዲሁም በዚህ ሳምንት መገባደጃ ላይ በቫቲካን በሚገኘው ፓላዞ ዴላ ካንሴሌሪያ ውስጥ 'ዮርዳኖስ፡ የክርስትና ተስፋ' በሚል ጭብጥ ስለሚከፈተው ኤግዚቢሽን እና የክርስትና መሰረት ወደ ሆነችው ዮርዳኖስ እና ወደተቀረው የቅድስት ሀገር ክፍል ስለሚደረገው ሃይማኖታዊ ንግደት በማንሳት ውይይት አድርገዋል።

በዚህ ሳምንት ለምን ወደ ሮም እንደመጡ የተጠየቁት አባ ሪፋት የካቶሊክ ጥናትና ሚዲያ ማዕከል ዳይሬክተር ስለሆኑ በውይይቱ እንዲካፈሉ መጋበዛቸው ከገለጹ በኋላ፣ በዮርዳኖስ የሚገኘውን የላቲን ሥርዓት ተከታይ ሃገረ ስብከት የሚዲያ ጽ/ቤትን በመወከል በሮም እየተከበረ በሚገኘው የዓለም የመገናኛ ባለሞያዎች የኢዮቤልዩ በዓል ላይ መሳተፋቸውን ገልጸው፥ በኢዮቤልዩ በዓል ላይ ከሚሳተፉት ከ138 ሀገራት ከተውጣጡ ባልደረቦች ጋር እንደ ሚዲያ መሪ በመሆን በመካፈላቸውም ደስተኛ መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ እሑድ ዕለት ከቅዱስነታቸው ጋር ሥርዓተ ቅዳሴ ላይ ተካፍለው የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ዕድል ማግኘታቸውን የገለጹት አባ ሪፋት፥ ከዛ በፊት ቅዳሜ ዕለት ለመገናኛ ባለሙያዎች በተዘጋጀው ሳምንታዊ ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ ላይ መገኘታቸውን ጠቁመዋል።

በወቅቱም እንደ [የመገናኛ ዳይሬክተሮች] በተናጠል በተዘጋጀላቸው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ መርሃ ግብር ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በዘመናችን ስላለው መገናኛ ብዙሃን በቤተክርስትያን አገልግሎት ላይ ስላለው ጠቀሜታ ማንሳታቸውን ጠቅሰው፥ እዚህ መገኘታቸውን እና በዓለም ዙሪያ ካሉ ሁሉም የካቶሊክ ሚዲያ ቢሮዎች ከተውጣጡ ባለሙያዎች ጋር አንድነትን መፍጠራቸው በጣም እንዳስደሰታቸው አብራርተዋል።

ሰኞ ጥዋት በተደረገው ስብሰባ ወቅት ለቅዱስ አባታችን ያዘጋጁትን ምስል ለብጹዕነታቸው ስለማበርከታቸው ያስታወሱት ካህኑ፥ ዮርዳኖስ እያሉ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር በግል በጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደሚገናኙ በተነገራቸው ወቅት ለቅዱስ አባታችን በዮርዳኖስ በሚገኘው የመጠመቂያ ስፍራ የተመሰረተችውን እና በጥጥር ወር መጀመሪያ ላይ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ልዩ መልዕክተኛ በሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ተመርቆ የተከፈተውን ቤተክርስቲያን የሚያሳይ ምስል አዘጋጅተው ሰኞ ዕለት ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

በምስሉም ላይ ቅዱስ አባታችን ባለፈው ጥቅምት ወር በመካከለኛው ምስራቅ ለሚገኙ ክርስቲያኖች በላኩት ሃዋሪያዊ መልዕክት በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ክርስቲያኖች በተቀደሰ ሀገራቸው ላይ በሚኖሩበት ወቅት “የተስፋ ቡቃያዎች እንዲሆኑ” ከመከሩበት መልዕክት ላይ የተወሰደ አንድ ጥቅስ መፃፋቸውን ተናግረዋል።

በምስሉ ላይ የኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመትን የሚያሳዩ ቡቃያዎችንም ማካተታቸውን የገለጹት ካህኑ፥ ምስሉን ለቅዱስ አባታችን በማሳየት በጥምቀት ሥፍራ የሚገኝ አዲስ ቤተክርስቲያን እንደሆነ እና በመካከለኛው ምስራቅ ላሉ ክርስቲያኖች የተናገሩት ቃላትም በምስሉ ላይ እንደሚገኙ አብራርተውላቸዋል።

ባለፈው ወር በዮርዳኖስ ወንዝ ላይ በተከበረው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ወቅት በተካሄደው የአዲሱ ቤተ ክርስቲያን ምርቃት ላይ ቁልፍ ሚና የተጫወቱት አባ ሪፋት፥ አከባቢው ለመንፈሳዊ ነጋዲያን ያለውን ጠቀሜታ፣ ለቅድስት ሀገር በተለይም ለዮርዳኖስ የሃይማኖታዊ ቱሪዝም እና ሃይማኖታዊ ጉዞ አስፈላጊነትን አስረድተዋል።

ከቫቲካን ዜና ጋር በመሆን በዮርዳኖስ ወንዝ ምሥራቃዊ ክፍል በሚገኘው የጥምቀት ቦታ ላይ ታሪካዊ ጊዜ ማሳለፋቸውን ያወሱት ካህኑ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ክርስትና መወለዱን ጠቅሰው፥ ምክንያቱን ሲገልጹ ጌታችን ተጠምቆ ብዙም ሳይቆይ የምሥራቹን ቃል መስበክና የአምላክ መንግሥት መቅረቧን መናገር በመጀመሩ ነው ብለዋል።

“ይህንን ቤተ ክርስቲያን የገነባነው ከ15 ዓመታት ጥበቃ በኋላ ነው” ያሉት ካህኑ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ፣ በግርማዊ ንጉሥ አብዱላህ እና በንግሥት ራኒያ ፊት የመጀመሪያውን መሰረተ ድንጋይ ማስቀመጣቸውን አስታውሰው፥ በዘንድሮው የጥምቀት በዓል ላይ እስከተመረቀበት ቀን ድረስ ለመጠባበቅ በጣም ረጅም መንገድ እንደ ነበር በመግለጽ፥ አምስት ዓመታት ያክል ለሚቀሩት ለታላቁ የዮርዳኖስ ኢዮቤልዩ ከአሁኑ ዝግጅት መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

በጎረጎሳዊያኑ 2030 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ 2000 ዓመታትን ያስቆጥራል ያሉት አባ ሪፋት፥ የቫቲካን ግዛት በሆነው በፓላዞ ዴላ ካንሴላሪያ 'ዮርዳኖስ፡ የክርስትና ተስፋ' የተሰኘውን ኤግዚቢሽን ለማስጀመር ሮም ከተማ ላይ እየተጠባበቁ መሆኑን አመልክተው፥ የጥምቀት ቤተ ክርስቲያንን ማስመረቃቸውን እና ለታላቁ ኢዮቤልዩ የአምስት ዓመታት ዝግጅት በመጀመራቸው በጣም ደስ እንደተሰኙ ገልጸዋል።

የተስፋ ታሪኮችን እንዲያቀርቡ ቅዱስ አባታችን የመገናኛ ባለሙያዎችን ስለመጠየቃቸው እና ይህን የቅዱስ አባታችንን ጥሪ እንዴት እንደተቀበሉት የተጠየቁት ካህኑ፥ ዮርዳኖስ በተለይ ለስደተኞች ሁሌም የተስፋ ምድር እንደሆነች በማረጋገጥ በሃገሪቷ መኖር መባረክ ነው ካሉ በኋላ፥ ከኢራቅ፣ ከሶሪያ፣ ከፍልስጤም እና ከጋዛ የተፈናቀሉትን እና የተጎዱትን ሰዎች የምታስተናግድ እንግዳ ተቀባይ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፥ እንደ ዮርዳኖስ ተስፋ እየፈጠርን እንቀጥላለን ብለዋል።

የተስፋ ታሪክን መናገር እና የዮርዳኖስን ታሪክ መተረክ ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ተስፋ የሚሰጥ ነገር ነው ያሉት ካህኑ፥ በቅድስት ሀገር እንደሚገኙ የዮርዳኖስ አብያተ ክርስቲያናት ‘እኛም የምንረዳቸውን ህዝቦቻችንን እና በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ ላሉ ተማሪዎቻችንን ተስፋ እንፈጥራለ’ ያሉ ሲሆን፥ በተለይም ትምህርት ቤቶቻችን ለሁሉም ክፍት የሆኑ የሃዋሪያዊ ሥራ ትምህርት ቤቶች በመሆናቸው በተለይ ለትርፍ የተቋቋሙ ሃብታም ትምህርት ቤቶች ከፍለው መማር ለማይችሉ ምስኪን ተማሪዎች ተስፋን እንፈጥራለን ብለዋል።

እሳቸውም በካሪታስ ዮርዳኖስ፣ በሚሰጠው በማንኛውም እርዳታ እና በእያንዳንዱ የበጎ አድራጎት ኮሚቴ፣ ደብር እና ቤተ ክርስቲያን በኩል ተስፋ እንደሚሰጡ አስታውሰው፥ በዚህ ዓመት ከተስፋይቱ ምድር ዮርዳኖስ ብዙ የተስፋ ታሪኮችን እንደሚጠብቁ ጠቁመዋል።

አባ ሪፋት በመጨረሻም ቅዱስ አባታችን ቀኑ ፋሲካ ላይ ሊሆን ስለሚችልበት ሁኔታ ሲናገሩ መስማታቸውን አስታውሰው፥ ይህ ለእነሱ በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ ለሚኖሩ በርካታ ቤተ እምነቶች እና አብያተ ክርስቲያናት ትልቅ ትርጉም አለው ካሉ በኋላ፥ የብጹእነታቸውን ምርጫ በታላቅ ደስታ እና በታላቅ ተስፋ እንደሚቀበሉ ገልጸው፥ ሌሎች እህት አብያተ ክርስቲያናት ወንድሞቻችን ይህንን ግብዣ ተቀብለው በሙሉ አንድነት እንዲሰሩ እና ፋሲካን በጋራ ለማክበር በጉጉት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
 

30 Jan 2025, 14:04