በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተባብሶ የቀጠለው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲሰደዱ ማድረጉ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ምስራቃዊ ክፍል ሰሞኑን በተካሄደው ውጊያ ኤም 23 ተብለው የሚጠሩት አማፂያን አዳዲስ አካባቢዎችን ጨምሮ የሰሜን ኪቩ ግዛት ዋና ከተማ የሆነችውን የጎማ ከተማን መቆጣጠራቸው ተነግሯል።
በማዕድን የበለፀገችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ላለፉት 30 ዓመታት በግጭት ስትታመስ ቆይታለች። በተለይ ደግሞ ከሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ በኋላ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ሰላም ሰፍኖ አያውቅም።
የተለያዩ የታጠቁ ቡድኖች ማዕከላዊውን መንግሥት ለማውረድ እና ሰፊዋን ሀገር ለመቆጣጠር በተለያየ ጊዜ በርካታ ሙከራዎችን አድርገዋል።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያለው አለመረጋጋት ጎረቤት ሀገራትንም የሚነካ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ በተለይ በ1990ዎቹ የአፍሪካ የዓለም ጦርነት በተባለለት ግጭት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸው ይነገራል።
በሩዋንዳ መንግስት የሚደገፉት ኤም 23 ተብለው የሚጠሩት ሚሊሻዎች በአሁኑ ወቅት በኮንጎ ጦር ሃይል (FARDC) ወታደሮች በተዋቀሩ ጥቂት ሚሊሻዎች እና የመንግስት ደጋፊ ከሆኑት የዋዛሌንዶ ሚሊሻዎች ጋር እየተፋለሙ እንደሚገኙ ተነግሯል።
ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ የተከሰተውን የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፍን ተከትሎ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ የደቡብ አፍሪካ ሃገራት ልማት ማህበረሰብ ተልእኮ አባል የሆኑ አራት ተጨማሪ የደቡብ አፍሪካ ወታደሮች በግጭቱ ህይወታቸውን አጥተዋል።
ኤም23 የተባለው አማፂ ቡድን በምሥራቅ ዲሞክራቲክ ኮንጎ የምትገኝ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ያላትን ጎማ ከተማ በቅፅበታዊ ጥቃት በቁጥጥር ሥር አውሏል።
ጎማ ከሩዋንዳ ጋር በሚዋሰነው ድንበር ላይ የምትገኝ ሲሆን፥ ከተማዋ በማዕድን ለበለፀጉ በርካታ ሥፍራዎች ቅርብ ናት። በተለይ ወርቅ፣ ኮልተን እና ቲን የተባሉ ማዕድኖች የሚወጡት ከዚህ አካባቢ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። ቲን እና ኮልተን ለሞባይል ስልክ እና ለኤሌክትሪክ መኪናዎች ባትሪ ማምረቻ የሚውሉ ተፈላጊ ማዕድኖች ናቸው።
አማፂያኑ ከተማዋን መቆጣጠራቸውን ያሳወቁ ሲሆን፥ ነገር ግን የኮንጎ መንግሥት ወታደሮቹ አሁንም ቁልፍ የሚባሉ ቦታዎችን እንደተቆጣጠረ ገልጿል።
ጦርነቱ ትኩረት አድርጎ በስፋት ሲካሄድ የነበረው በሃገሪቱ አየር ማረፊያ አካባቢ ሲሆን፥ አየር ማረፊያው በአሁኑ ወቅት በኤም 23 ቁጥጥር ስር ነው ተብሏል።
የጎማ ከሌሎች ከተሞች መነጠል
ጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም. የጎማ ሊቀ ጳጳስ ዊሊ ንጉምቢ ንጌሌ እንደተናገሩት በጥቃቱ ምክንያት ከተጎዱት ተቋማት መካከል በቻሪቴ የእናቶች አጠቃላይ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኝ የማዋለጃ ክፍል አንዱ ሲሆን፥ ይህም “ለጨቅላ ሕፃናት ሞት ምክንያት ሆኗል” ተብሏል። ከዚህም በተጨማሪ በሃገረ ስብከቱ የሚገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጽ/ቤት ህንፃ ጉዳት እንደደረሰበትም ለማወቅ ተችሏል።
በአሁኑ ወቅት ወደ ከተማዋ የሚያስገቡ ዋና ዋና መንገዶች እየተካሄደ በሚገኘው ከባድ ውጊያ እና የዘረፋ ተግባሮች ምክንያት በመዘጋታቸው የአከባቢው ህዝብ ከፍተኛ ወጥመድ ውስጥ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ ሌሎች በርካቶች ደግሞ ወደ ጎረቤት ሩዋንዳ ለመሰደድ ተገደዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ድርጅት በአካባቢው የሚካሄደው የሰብዓዊ እርዳታ ስርጭት መቆሙ እንዳሳሰበው በመግለጽ፥ በዚህም ምክንያት በቀጣዮቹ ቀናት ውስጥ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቋል።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል
ካፎድ ተብሎ የሚታወቀው በእንግሊዝ እና በዌልስ የምትገኝ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ይፋዊ የእርዳታ ኤጀንሲ (CAFOD) የሃገሪቱ ተወካይ የሆኑት አቶ በርናርድ ባሊቡኖ እንደገለጹት በጎማ ከተማ ያለው የሰብአዊ ፍላጎቶች በአሁኑ ወቅት በጣም ሰፊ መሆናቸውን በመጥቀስ፥ “ከተማዋ በግጭቱ ምክንያት ከሌሎች ከተሞች ጋር ያላት ግኑኝነት ተቋርጧል” ያሉ ሲሆን፥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን እና በርካቶች ደግሞ ወደ ጎዳና ወጥተው ለልመና መዳረጋቸውን አክለው ገልጸዋል።
በአከባቢው በሚከሰተው ተደጋጋሚ ግጭት ምክንያት አንዳንዶቹ በቅርብ ቀናት ውስጥ፣ ብዙዎች ለብዙ ጊዜያት፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ከአንድ ጊዜ በላይ ከመኖሪያ ቤታቸው ስለተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ካፎድ ያለውን ስጋት ገልጿል።
በአከባቢው የሚገኙ የድንበር የለሽ የዶክተሮች ቡድን (MSF) ሰራተኞች በበኩላቸው እንደገለጹት በመሀል ከተማ በርካታ ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ የቦምብ ጥቃት፣ ተኩስ እና ዘረፋ በመፈጸሙ ሽብር እና ከፍተኛ የህዝብ መፈናቀል መፈጠሩን ገልጸዋል።
ችላ የተባሉ ቀውሶች
በኮንጎ መንግስት እና በአማፂ ቡድኖች መካከል ያለው ግጭት ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፥ የአሁኑ ደግሞ ወደ ሩዋንዳ ተሻግሮ ወደ ቀጠናዊ ግጭት ሊሸጋገር ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እየተካሄደ ያለው ግጭት በዓለም ዙሪያ ከተረሱ በርካታ ቀውሶች ውስጥ አንዱ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ የምዕራቡ ዓለም አይኖች በመካከለኛው ምስራቅ እና በዩክሬን ላይ ያተኮሩ በመሆኑ በሃገሪቷ በተከሰተው ረሃብ፣ በሽታ እና አመጽ ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት መጥፋቱ ተዘግቧል።