የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት  (AFP or licensors)

አቶ አሌሳንድሮ፥ "የፖለቲካ ስልጣንን በውዴታ መልቀቅ በሕዝብ ዘንድ ክብርን ያሰጣል!"

በቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ “ሎዘርቫቶሬ ሮማኖ” ዝግጅት ክፍል የቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ምክትል ዳይሬክተር አቶ አሌሳንድሮ ጊሶቲ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የስልጣን ስንብት ጠቀሜታን በማስመልከት አስተያየታቸው ጽፈዋል። ዳይሬክተሩ በአስተያየታቸው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ውሳኔ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1999 በኔልሰን ማንዴላ ለሁለተኛ ጊዜ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ላለመወዳደር ያደረጉትን ውሳኔ ያስታውሳል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ወደ ኋላ መመለሱ ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል ያሉት አቶ አሌሳንድሮ፥ የስልጣን ቦታን ወይም ከፍተኛ ደረጃ መያዝ የግድ አይደለም ብለዋል። አንዳንድ ጊዜ የተቋቋመውን የሥራ ልምዳችንን ወይም ጠንክረን ያገኘንበትን የስልጣን ቦታ መተው በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል ያሉት ዳይሬክተሩ፥ “በሕዝብ ዘንድ ታዋቂ የነበረ ሰው ወደ ኋላ ሲመለስ ወይም ስልጣን ለመልቀቅ ሲወስን ወዲያው ከሕዝቡ ርኅራኄ እና ክብር የሚቸርለት ለዚህ ነው” ብለዋል። የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የካቲት 11/2013 ዓ. ም. የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያዊ መሪነት ስልጣን ለማስረከብ ያደረጉት ታሪካዊ ውሳኔ አስደናቂ ሁኔታን እንደፈጠረብን እናስታውሳለን ብለው፥ ሁኔታውን የምንረዳው በተለየ መንገድ ቢሆንም፥ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በ “ዋይት ሃውስ” ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የሚያደርጉት የእጩነት ዕድልን ለሌላ አዲስ እጩ አሳልፈው መስጠታቸውን ገልጸው፥ ዶናልድ ትራምፕን ለመተካት ምክትላቸው ካማላ ሃሪስን ብቁ እንደሆኑ አስቀድመው በይፋ መናገራቸውን አቶ አሌሳንድሮ ተናግረዋል።

እንደሚታወቀው ውሳኔው ለተወሰነ ጊዜ ሲወራ የቆየ እና በርካታ ታዋቂ ዴሞክራቶች ጆ ባይደን በድጋሚ ለመመረጥ የሚያደርጉትን የምርጫ ቅስቀሳ እንዲያቋርጡ መጠየቃቸውን አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ የምርጫው የመጨረሻ ውሳኔ ለ “ዋይት ሃውስ” የሚተው ቢሆንም ለሌላ አራት ዓመት ለፕሬዝዳንትነት የመወዳደር ውሳኔ ለጆ ባይደን የሚተው ቀላል ያልሆነ ውሳኔ እንደነበር አቶ አሌሳንድሮ ጊሶቲ በአስተያየታቸው ገልጸዋል።

በርካታ ታዛቢዎች የታዘቡት የተከበረ የጆ ባይደን ውሳኔ ከግል ጥቅም ይልቅ ለአገር ጥቅም ቅድሚያ እንደሰጡ የሚያሳይ እንደሆነ አቶ አሌሳንድሮ ጊሶቲ ገልጸዋል። ይህም በፕሬዚዳንትነታቸው ላይ ከሚደረጉ የፖለቲካ ግምገማዎች የዘለለ እነንደሆነ የተናገሩት አቶ አሌሳንድሮ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1999 ዓ. ም. የደቡብ አፍሪካው የነጻነታ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ለሁለተኛ ፕሬዝዳንታዊ የስልጣን ዘመን ላለመወዳደር ወስነው በጡረታ መገለላቸው በአንዳንድ መልኩ የበለጠ ጠንካራ እና አሳማኝ ውሳኔ ማድረጋቸው የአፓርታይድ አገዛዝን በማሸነፍ በሚወዷት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የእርቅ መንገድ ማስጀመሩን አቶ አሌሳንድሮ አስረድተዋል። “ኔልሰን ማንዴላ ለሃያ ሰባት ዓመታት በእስር ቤት ውስጥ ያሳለፉትን የመከራ ፍሬ ሌሎች የሚያጭዱበት ጊዜው አሁን ነው” በማለት አቶ አሌሳንድሮ አክለዋል።

የፖለቲካ ዕድሜ አጭር ቢሆንም ፍሬያማ ሊሆን እንደሚችል የገለጹት አቶ አሌሳንድሮ፥ ጆ ባይደን በሚቀጥለው 2017 ዓ. ም. ስልጣናቸውን ለማስረከብ የቀራቸው 6 ወራት ብቻ እንደሆኑ፥ ከአሁን በኋላ ለምርጫ ዘመቻ ብቻ ምርጫዎችን ማድረግ እንደማያስፈልግ፥ አዲስ ተመራጭ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በዩክሬን እና በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ግጭቶችን ከማስቆም ጀምሮ በታሪክ ውስጥ በተለይም በውጭ ፖሊሲ ውስጥ ያላቸውን ሕዳሴ የሚገልጹ ግቦችን ለማሳካት የሚያግዙ ደፋር እና አዳዲስ ዕድሎችን ለመክፈት ተስፋ ማድረግ እንደሚገባ በመግለጽ፥ በቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ “ሎዘርቫቶሬ ሮማኖ” ዝግጅት ክፍል የቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ምክትል ዳይሬክተር አቶ አሌሳንድሮ ጊሶቲ አስተያየታቸውን ደምድመዋል።

 

23 July 2024, 16:50