የሮሂንጊያ ስደተኞች ሰብአዊ እርዳታ እንዲደረግላቸው እንዲሁም ለማንነታቸው ክብር እንዲሰጣቸው ጠየቁ ።
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ነሐሴ 19 2015 ዓ.ም. ዕለተ ዓርብ በሰሜናዊ ራኪን ግዛት ውስጥ የሚገኙትን የሮሂንጊያን ህዝቦች እና ሌሎች አናሳ ጎሳዎች በኃይል የተፈናቀሉበትን የማይናማር በጭካኔ የተሞላ ወታደራዊ ዘመቻ 6ኛ ዓመትን የሚያከብሩበት ቀን ነው። 800,000 የሚጠጉ ግለሰቦች በባንግላዲሽ ድንበር አቋርጠው ከማይናማር ሠራዊት “ዘርን የማጥራት” ዘመቻ ለማምለጥ ተስፋ አስቆራጭ ስደት የጀመሩት እና ሙከራ ያደረጉት በዚሁ ቀን ነበር።
ብዙ የሮሂንጋ ተወላጆች በኮክስ ባዛር "ቤታችን ፥ ክብራችን" የሚሉ ፖስተሮች እና መፈክሮችን ይዘው ተሰብስበዋል። ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ፍላጎታቸውን በመግለጽ የእናት ሀገራቸውን ብሔራዊ መዝሙር ሲዘምሩም ነበር።
የህዝቡ ህመሞች
790,000 የሚደርሱ የሮሂንጊያ ስደተኞች የኮክስ ባዛር ጊዜያዊ ካምፖችን ወደ ዘላቂ እና ንጽህና የጎደላቸው መጠልያነት ለውጠውታል። የቡድን ጥቃት፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር እና የአደንዛዥ ዕፅ ሽያጭ እየጨመረ በመምጣቱ የባንግላዲሽ ባለስልጣናት ስለስደተኞቹ ደህንነት መናገር ከጀመሩ ሰነባብተዋል። በዚህም የተነሳ የደህንነት ባለስልጣናቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ፖሊሶችን ወደ ስደተኛ ካምፖቹ ልከዋል።
እንደ ዩክሬን ባሉ በጦርነት በተጠቁ ቦታዎች የሰብአዊ እርዳታ አስፈላጊነት እየጨመረ በሄደ ቁጥር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና የእርዳታ ድርጅቶች ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ የዋሉ መገልገያዎችን ለድንገተኛ አደጋዎች እንደ ሮሂንጊያ ላሉ አከባቢዎች አሰራጭተዋል። እንደ ወርሃዊ የምግብ መመገቢያ ካርዶችን የመሳሰሉ ብዙ መጠቀሚያዎች አገልግሎት ላይ ውለዋል።
መዲሲንስ ሳን ፍሮንታየርስ (ድንበር የለሽ የዶክተሮች ቡድን) የተባለው ተቋም በባንግላዲሽ ካምፖች ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የበሽታ ወረርሽኝ የመነሳት ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል። በካምፑ ውስጥ ያለው ሁኔታ ተባብሶ ብዙ ሮሂንጋዎች በጥገኛ ኢንፌክሽን የሚሰቃዩበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህም ገና ለሚመጣው በጣም የከፋ የጤና ሁኔታ መጀመሪያ ሊሆን ይችላል ተብሎም ተሰግቷል።
ከዓለም አቀፍ ለጋሾች የሚሰጠው የገንዘብ ዕርዳታ መቀነስ እና የተጨናነቀ የጤና አጠባበቅ አገልግሎቶች በቂ ያልሆነ የንጹህ ውሃ አቅርቦትን እና እጅግ በጣም በተጨናነቁ ካምፖች ውስጥ ያለውን የንጽህና ጉድለት ስጋት ጨምሯል።
የሮሂንጊያ ተወላጆች ሰብአዊ መብቶቻቸው ሊከበሩ እንደሚገባ እና በሠላም ወደ አገራቸው እስኪመለሱ ድረስ ደህንነታቸው ሊረጋገጥ ይገባል ሲሉ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ቮልከር ቱርክ ሃሙስ ዕለት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ሮሂንጊያዎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ቅድመ ሁኔታዎችን ለማዘጋጀት ሲደረጉ የነበሩትን ዓለም አቀፍ የተጠያቂነት ጅምሮች ሙሉ በሙሉ እንዲደግፉ እና ሌሎች ሃገራትም ተሳትፎዋቸውን እንዲያጠናክሩ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።