ፈልግ

FILE PHOTO of emerging technology

ኢንዶኔዢያ የዲጂታል ነፃነቱ በማሽቆልቆሉ ምክንያት የ2024 ምርጫ ተአማኒነቱ ቀንሷል ተባለ

ኢንዶኔዢያ እ.አ.አ በ2024 አጠቃላይ ምርጫዋን ልታደርግ በተቃረበች ቁጥር የዲጂታል ነፃነቱ ቀስ በቀስ እያሽቆለቆለ መምጣቱ የደቡብ ምስራቅ እስያ ህግ አውጪዎችን እያሳሰበ መጥቷል።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የደቡብ ምሥራቅ እስያ የሕግ አውጭዎች ኢንዶኔዥያ የመናገር ነፃነት ላይ የምታረጋቸው እገዳዎች ያሳስባቸዋል ፥ ምክንያቱም ዲጂታል አሰራሮቹ በሚቀጥለው ዓመት ከሚደረገው የሀገሪቱ ምርጫ በፊት ክትትል እየተደረገባቸው ነው።

‘የእስያ ፓርላማዎች ለሰብአዊ መብቶች’ (APHR) የሚባለው ስብስብ ማክሰኞ ግንቦት 22 በሰጡት መግለጫ የኢንዶኔዥያ ኤሌክትሮኒክስ ፣ መረጃ እና ግብይት (ITE) ህግ ተቺዎችን ወንጀለኛ ለማድረግ እና ዝም ለማሰኘት በሀይለኛ ግለሰቦች መጠቀምያ ሆኗል ብለዋል።

የሕግ አውጭዎቹ እውነታውን ለማወቅ ባካሄዱት ጥረት ፥ ‘ሥም ማጥፋትን’ በተመለከተ የወጡት የሕጉ አሻሚ አንቀፆች በሰላማዊ መንገድ የተቃውሞ ሃሳባቸውን የሚያወጡትን እንኳን ሳይቀር በማጥቃት ላይ መሆናቸውን ደርሰውበታል።

የ ‘እስያ ፓርላማዎች ለሰብአዊ መብቶች’ አባል እና የቲሞር ሌስቴ የህግ ባለሙያ የሆኑት ኤልቪና ሶሳ ካርቫልሆ እንዳሉት “በኤሌክትሮኒክስ መረጃና ግብይት ህግ ውስጥ ያሉት አሻሚ ድንጋጌዎች በግልጽ አላግባብ ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሆነ እና በኦን ላይን በሚደረጉ ምክክሮች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ትርጉም ያለው ውይይት ለማድረግ ትልቅ ስጋት ይፈጥራሉ” ብለዋል።

“ይህ ተቋም የኢንዶኔዥያ መንግስት እና የተወካዮች ምክር ቤት አጠቃላይ የህግ ማሻሻያ እንዲያወጡ እና ባለስልጣናት ሕጉን በማይሆን አግባብ መጠቀም እንዲያቆሙ ጥሪውን በማስተላለፍ የኢንዶኔዥያ ሲቪል ማህበረሰብን ንቅናቄ ተቀላቅሏል” ሲሉ አቶ ካርቫልሆ አክለዋል።

እ.አ.አ. በ 2008 የፀደቀው የዚህ የኤሌክትሮኒክስ መረጃና ግብይት ህግ አንቀጽ 27 ክፍል 3 ፥ የአንድን ሰው ስብዕና የሚያዋርድ እና የሥም ማጥፋት ይዘቶች ያሉበትን የኤሌክትሮኒክስ መረጃ እና ሰነዶች ስርጭትን ይከለክላል።

“በዚሁ ህግ ላይ በሚነሱት ክሶች ምክንያት መጪው ምርጫ በእውነት ዲሞክራሲያዊ ስለመሆኑ ጥያቄ ውስጥ ይጥላል” ብለዋል.

 ምርጫ እና የዲጂታል ነፃነት

በኢንዶኔዥያ የሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መንግስት የማህበራዊ ሚዲያ ይዘትን በጥልቀት መከታተል በመጀመሩ ያላቸውን ስጋት ገልፀው ፥ እነዚህ የኢንተርኔት ነፃነት ገደቦች አስጨናቂ ውጤት አስከትለዋል ሲሉ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች የህግ ትንኮሳን ለማስቀረት በውይይት እንዳይሳተፉ አድርገዋል።

“በአሁኑ ጊዜ ዜጐች እና መራጮች የመናገር መብትን በብዛት ከሚጠቀሙባቸው ቦታዎች አንዱ ኢንተርኔት ነው። እነዚህ ዲጂታል ቦታዎች ከተዘጉ ለመጪው ምርጫ ነፃነት እና ፍትሃዊነት ላይ አደጋን ይፈጥራል” ሲሉ ‘የእስያ ፓርላማዎች ለሰብአዊ መብቶች’ አባል እና የማሌዥያ የህግ ባለሙያ የሆኑት ዩነስዋራን ራማራጅ ተናግረዋል ።

“ምርጫ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተለይም የተገለሉ ወገኖች ሃሳባቸውን በግልፅና በሰላማዊ መንገድ የሚገልጹበት እና ስለ ሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ትርጉም ያለው ውይይት የሚያደርጉበት እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሂደት ሊሆን ይገባል” ሲሉ ‘የእስያ ፓርላማዎች ለሰብአዊ መብቶች’ አባል እና የፊሊፒንስ የህግ ባለሙያ ሳራ ኤላጎ አስተጋብተዋል።

ሳራ ኤላጎ በማከልም “ስለዚህ ‘የእስያ ፓርላማዎች ለሰብአዊ መብቶች’ በምርጫው ሂደት ውስጥ ጤናማ እና በመረጃ ላይ የተመሰረተ የኦን ላይን ንግግርን ለማበረታታት በዲጂታል ነፃነት-ነክ ፖሊሲዎች ውስጥ የህዝብ ተሳትፎን እንዲያሳድጉ የኢንዶኔዥያ መንግስት ተቋማትን ይጠይቃል” ብለዋል ።

የኢንዶኔዢያው አምባገነን መንግስት ከወደቀ በኋላ ሃገሪቷ በዴሞክራሲ ምስረታ ላይ የ25 ዓመታትን ውጤት አስመዝግባለች።

 

01 June 2023, 21:25