ፈልግ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ   (AFP or licensors)

አድልዎ እና ኢፍትሃዊነት በዓለም አቀፉ የገንዘብ ሥርዓት ውስጥ መንሰራፋቱን አንቶንዮ ጉተሬዝ ገለ

የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ ታሪካዊ ኢፍትሃዊነትን እና የስርዓት አድልዎ ለመፍታት በዓለም አቀፉ የፋይናንስ ስርዓት ውስጥ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሃላፊ የሆኑት አንቶኒዮ ጉተሬዝ ተቋሙ የበለጠ ጠንካራ ፣ ፍትሃዊ እና ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን የዓለምአቀፉ የፋይናንስ መዋቅር ማሻሻያ እንዲደረግበት አሳስበዋል።
ባለፈው ሰኞ ግንቦት 28 2015 ዓ.ም. በኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ ጉተሬዝ ንግግር ሲያደርጉ ፥ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት እንደ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ደህንነት መረብ ዋና ተልእኮውን በመወጣት ረገድ ‘በአብዛኛው አልተሳካለትም’ ብለዋል ።
እንደ ጉቴሬዝ ገለጻ ከሆነ ‘ሥርዓቱ ለታዳጊ ሀገራት ለማገገሚያ የሚሆን በቂ የገንዘብ ድጋፍ አላቀረበም ፥ በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ ሃገራት አሁን ላይ ከፍተኛ የፋይናንሺያል ቀውሶች እያጋጠሟቸው ነው’ በማለት ተችተዋል። በማከልም “ሃምሳ ሁለት ታዳጊ ሀገራት በብድር ጫና ችግር ውስጥ ናቸው ወይም ለዚህ ችግር በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛሉ። የዋጋ ንረት እና የወለድ ምጣኔ እየጨመረ በመጣ ቁጥር በታዳጊ ሀገራት ላይ ያልተረጋጋ የፋይናንስ ጫና እየፈጠረ ነው” ብለዋል።
ዋና ጸሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሦስት አዳዲስ የፖሊሲ ዕቅዶችን ያቀረቡ ሲሆን ፥ ከነዚህም አንዱ በስድስት የተለያዩ አካባቢዎች ‘ታሪካዊ ኢፍትሃዊነትን እና ሥርዓታዊ አድሏዊነትን ለመፍታት’ ያለመ ነውም ተብሏል ።
ለዓለም አቀፍ ፋይናንስ የታቀዱ ማሻሻያዎች
አጭር የማሻሻያው መግለጫው የሚያተኩረው በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ አስተዳደር ፣ የዕዳ ቅነሳ ፣ የሉዓላዊነት ብድር ወጪ ፣ የዓለምአቀፍ የፋይናንሺያል ሴፍቲኔት እና የዓለም አቀፍ የታክስ አከፋፈል ላይ ነው። ከታቀዱት ማሻሻያዎች መካከል ፥ የገንዘብ ተቋማት በሆኑት በዓለም ባንክ እና በዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) ዉስጥ የታዳጊ ሀገራትን የቦርድ አባላት ድምጽ ማጠናከር እንዳለበትም ይጠቁማል።
ጉቴሬዝ የልማት ፋይናንስን ከንግድ አበዳሪዎች ጋር ለማገናኘት የዕዳ ስረዛ የአሠራር ዘዴ መፈጠሩን ጠቅሰዋል። በተጨማሪም አጭር መግለጫው እንደሚያሳየው የዓለምአቀፍ የገንዘብ ድርጅት የሀብት ተደራሽነት ኮታው ላይ ማሻሻያዎችን በማቅረብ እና አጠቃላይ ስርዓቱን የሚቆጣጠር ተወካይ ከፍተኛ አካል ማቋቋም በሚለው ላይም መሰራት እንዳለበት ይገልፃል።
በአጠቃላይ የማሻሻያው ሀሳቦች ሀብታሞችን ብቻ ተጠቃሚ ከሚአደርገው ስርዓት ለመውጣት እና ለአጭር ጊዜ ትርፍ ቅድሚያ የሚሰጥ ፍትሃዊ እና ዘላቂ የልማት ግቦች ፣ የአየር ንብረት እርምጃዎች እና የወደፊት ትውልዶች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ያለመ ነው ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኃላፊ አብራርተዋል።
ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ተሻግሮ ማየት
በተጨማሪም ጉቴሬዝ እንደተናገሩት ፥ የሀገር ውስጥ ምርት ጠቃሚ ሆኖ ሳለ የጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርትን (GDP)ን እንደ ብቸኛ የእድገት መለኪያ አድርጎ ከማየት መሻገር አስፈላጊ መሆኑን እና እድገትን ለመገምገም ሌሎች መለኪያዎች መካተት እንዳለባቸው አፅንዖት ሰጥተውበታል። “ጂዲፒ ምናልባት የሁሉንም ነገር ዋጋ ሊነግረን ይችል እንደሆን እንጂ የምንንም ነገር ጥቅም ሊነግረን አይችልም። ዓለማችን ግዙፍ ኮርፖሬሽን አይደለችም ፥ የፋይናንስ ውሳኔዎች ከትርፍ እና ኪሳራ ቅጽበታዊ እይታ በላይ መሆን አለባቸው” በማለትም አክለውበታል።
ጉቴሬዝ የሰው ልጅ እድገት በበርካታ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልፀው ፥ በድህነት እና የረሃብ ደረጃዎች ፣ በእኩልነት ፣ በማህበራዊ ትስስር ፣ ለአየር ንብረት መበከል እና ለሌሎች አደጋዎች ተጋላጭነት የሰው ልጅ ዕድገት ሊለካ ይችላል ብለዋል። ለለውጡ እና ውጤቶቹ እውቅና እየሰጡ እድገትን ለመከታተል እና ለመተንተን ሰፋ ያሉ ጠቋሚዎችም እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል።
የፍራንቺስኮ ኢኮኖሚ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት እኩል የተጠቃሚነት እድል እንዲኖራቸው እና የእድገታቸውን እምቅ አቅም ከሚያሳጣው አዙሪት እንዲወጡ የተሻሻለ የኢኮኖሚ ሞዴል እንዲደረግ ደጋግመው ጠይቀዋል።
እ.አ.አ. በ2019 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ‘የፍራንቺስኮስ ኢኮኖሚ’ የተሰኘ ፕሮግራም ጀምረው ነበር ፤ ይህም ማበረታቻ ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ለውጥ እንዲመጣ ግፊት በማድረግ የወደፊቱ የዓለም ኢኮኖሚ ማንንም ወደ ኋላ ሳይተው ፍትሃዊ ፣ አካታች እና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን በማሰብ ነው።
 

08 June 2023, 09:33