ፈልግ

ሱዳናውያን ስደተኞች በቻድ ሱዳናውያን ስደተኞች በቻድ  

በሱዳን የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግም የሰብዓዊ ዕርዳታው ምንም እመርታ አላሳየም ተባለ ።

አንድ ሳምንት ሙሉ እየተደረገ በነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት ሁለተኛ ቀን ላይ በሱዳን ዋና ከተማ በተቀናቃኝ ወታደራዊ አንጃዎች መካከል ያለው ግጭት ሌሊቱን የቀጠለ ሲሆን ፥ የዚህም ስምምነት ዋናው የታቀደለት ዓላማ ሰብአዊ ዕርዳታን ለተጎጂዎች ለማድረስ እና ለዘላቂ የእርቅ ስምምነቱም መሰረት ይጥላል ተብሎ ተስፋ ተደርጎበታል።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ አዲስ አበባ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሱዳን ውስጥ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 25 ሚሊዮን ከፍ ብሏል ያለ ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ የህዝብ ብዛት ከግማሽ በላይ እንደሆነ ገልጿል።

ሚያዝያ 15 በመንግስት ወታደራዊ ሃይሎች እና በኃያሉ የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ 300,000 በላይ ሰዎች ከሱዳን ወደ ጎረቤት ሀገራት የተሰደዱ ሲሆን ከነዚህም አንዳንዶቹም በተመሳሳይ ሁኔታ በድህነት ውስጥ የነበሩ እና የውስጥ ግጭት ታሪክ ያላቸው ናቸው።

በሱዳን ግዛት ውስጥም ጭምር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል የነበራቸውንም ሁሉ ነገር አጥተዋል።

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ እንዳመላከተው ለጋሾች ለስደተኞቹ የሚያበረክቱት ዕርዳታ በቂ እንዳልሆነ ገልፆ ስደተኞችን የሚያስተናግዱ ሀገራትን ለመደገፍ የገንዘብ ድጋፍ በአስቸኳይ እንደሚያስፈልግ ገልጿል።

የተኩስ አቁም ስምምነት

በሳዑዲ አረቢያ እና በአሜሪካ አስተባባሪነት እንዲሁም በተፋላሚ ወገኖች መልካም ፍቃድ በጅዳ የተደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት ለአምስት ሳምንታት በዋና ከተማይቱ ካርቱም በተደረገ ከፍተኛ ጦርነት እና በሀገሪቱ ምዕራባዊ የዳርፉርን ግዛት ጨምሮ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ብጥብጥ ከተከሰተ በኋላ ነው።

ምንም እንኳን ስምምነቱ በካርቱም ውስጥ አንጻራዊ በሆነ ሁኔታ ውጊያ ቀዝቀዝ ያለ ቢሆንም በጣም አስፈላጊ በሆነው የሰብአዊ እርዳታ ላይ ግን ፈጣን መሻሻልን የሚያሳይ ምልክት እስካሁን አልታየም።

አንዳንድ የዕርዳታ ሠራተኞች እንደሚናገሩት በቀይ ባህር ዳርቻ ላይ በሚገኘው ፖርት ሱዳን ወደብ ከሚደርሱት እቃዎች እና የዕርዳታ ቁሳቁሶች አብዛኛዎቹ የጸጥታ ፍቃድ እና ዋስትና እየጠበቁ ባለበት በዚህ ሠዓት ነዋሪዎቹ ለረጅም ጊዜ በሚቆይ የውሃ እና የመብራት መቆራረጥ የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በመፈራረሳቸው አገልግሎት በማጣት እንዲሁም በመጠነ ሰፊ የህግ ጥሰት እና ዝርፊያ እየተሰቃዩ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

25 May 2023, 11:14