ፈልግ

ደቡብ አፍሪካ ደቡብ አፍሪካ 

በደቡብ አፍሪካ የብዙዎቹን ‘ክብር የማስጠበቅ’ እና ሕይወትን የመለወጥ ሥራ እየተሰራ ነው

በደቡብ አፍሪካ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የተያዙ ሰዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ከእጥፍ በላይ መጨመሩን ታዛቢዎች አስጠንቅቀዋል። ደቡብ አፍሪካዊቷ የመብት ተሟጋች ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ከመንገድ ላይ ሴተኛ አዳሪነት ለማዳን እንዲሁም ክብራቸውን ጠብቀው የወደፊት እጣ ፈንታቸውን እንዲወስኑ ለመርዳት በምትጥርበት ወቅት ፥ መንግስት የተሻሉ ፖሊሲዎችን እንዲያወጣ ግፊት ለማድረግ ስላደረገችው ትግል ተናግራለች።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ገለልተኛ የሆነ እና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሚሰራው ተቋም (ቲ አይ ፒ) እንደዘገበው ከሆነ ሴቶች እና ልጃገረዶች ለሴተኛ አዳሪነት ሥራ ለሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በጣም የተጋለጡ ሲሆኑ ፥ በደቡብ አፍሪካ በዚህ ህገ ወጥ ሥራ ላይ የተሳተፉ አካላት ገቢ እየጨመረ መምጣቱም ተነግሯል።

የሀገሪቱ ‘ብሔራዊ የነፃነት ህብረት’ የተባለው ተቋምም እንደዘገበው ፥ በአሁኑ ጊዜ 155,000 የሚገመቱ ሰዎች በዚህ በፍጥነት በማደግ ላይ ባለው ኢንዱስትሪ ሰለባ እየሆኑ ሲሆን ፥ በደቡብ አፍሪካ የወሲብ ንግድ ትሥሥሩ እስከ አስር ዓመት የእድሜ ክልል ላይ ያሉ ልጃገረዶችን ተጋላጭ አድርጓል ብሏል።

ከፍተኛ የሥራ አጥነት ፣ ዝቅተኛ ደመወዝ እና ከስደት ወረርሽኙ ጋር የተያያዘ የጸጥታ ችግር ምክንያት አብዛኛው ለዚህ ሥራ የተጋለጡ ሲሆን ፥ በተለይም የወጣቶች ፣ የአፍሪካዊ ሴቶች እና የውጭ ስደተኞች ተጋላጭነታቸው ይጨምራተብሏል።

 ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ “በክርስቶስ አካል እና በሰው ልጆች ላይ ክፍት የሆነ ቁስል” በማለት የገለጹትን ይህን መቅሰፍት ለማስቆም የምትታገል ደቡብ አፍሪካዊት ሴት ፥ በጆሃንስበርግ ከተማ ውስጥ የምትሰራ ጋዜጠኛ ፥ እንዲሁም ‘ክብርን ማስጠበቅ’ የተባለ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት መስራች እና ሥራ አስፈፃሚ የሆነችዋ ፒንኪ ክሆባኔ የምትባል ሴት አለች።   

ፒንኪ ከቫቲካን ረዲዮ ጋር ባደረገችው ቆይታ ‘የዛሬ 3 እና 4 ዓመት አካባቢ በመኪና ተጉዤ ብዙ ወጣት ልጃገረዶችን በመንገድ ዳር በማየቴ ፥ የብዙ አቅመ ደካማ ሴቶችን ህይወት ለመቀየር ቆርጬ ተነሳው’ ስትል ተናግራለች።

“በመኪናዬም እየተጓዝኩ የሚያደርጉትን ነገር ለማየት ቆምኩና እየተሸጡ ወይም ገላቸውን እየሸጡ እንደሆነ ተረዳሁ። አብዛኛው 18 ዓመት እንኳ ያልሞላቸው ልጃገረዶች ስለሆኑ በጣም ደነገጥኩ” ትላለች።

 ክሆባኔ ስለጉዳዩ በትዊተር ገጿ ላይ ያላትን ጭንቀት ገልፃለች ፥ አንዳንድ ምላሾች በጣም እንዳሳዘኗት ነገር ግን በአብዛኛው ዓይን ከፋች እንደነበሩ ፥ እንዲያውም ‘ወሲባዊ ብዝበዛን ለማስወገድ የሚሠራውን ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ እንድቀላቀል አድርጎኛል’ ብላለች።

 “በብዛት በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ እየተሳተፍኩ ስሄድ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ከዝሙት አዳሪነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን ተረዳሁ። በተጨማሪም አሁን የምግብ ዋስትናም ከዚህ ህገ ወጥ ኢንዱስትሪ ጋር በጣም የተቆራኘ መሆኑንም ተረዳሁ” ትላለች።

ስለዚህ “ክብርን ማስጠበቅ” ላይ አክላ ለዝሙት አዳሪነት ትኩረት በመስጠት የህግ ማሻሻያ እንዲደረግ ግፊት ማድረግ የጀመርን ሲሆን ፥ በዓመቱ መጨረሻ ላይም በፓርላማ ለውይይት የሚቀርብ ረቂቅ ህግ እንደሚመጣ ያላትን ተስፋ ገልጻለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ድርጅታቸው ስለ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ግንዛቤ በማሳደግ ስልጠና እና ክህሎት ማግኘት ለሚፈልጉ ተጎጂዎች የገቢ ማስገኛ ፕሮጄክቶችን በማካሄድ ራሳቸውን እንዲችሉ ‘የመውጫ መርሃ ግብሮችን’ ለማቋቋም እየሰራ መሆኑን ተናግራለች።

የሰብአዊ መብት እና ክብር ሻምፒዮና

ሁለት ጥቅሶች “ክብርን ማስጠበቅ” በሚለው በራሪ ወረቀት የመጀመሪያ ገጽ ላይ ተጽፈዋል።

የመጀመሪያው ፥ በኔልሰን ማንዴላ የተነገረው “በእያንዳንዷ ሴት እና ልጃገረድ ላይ ጥቃት በደረሰ ጊዜ ስብእናችን ወርዷል ማለት ነው ፥ እያንዳንዷ ሴት ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንድትፈጽም የተገደደች ጊዜ ፥ ክብርችንን እና ኩራታችንን አጥፍተናል ማለት ነው። ህይወቷን ለወሲብ በሸጠች ሴት ላይ የሚፈረደውን እድሜ ልክ እስራት እናወግዛለን። በእያንዳንዱ ድርጊት ላይ ዝም በምንልበት ጊዜ በሴቶቻችን ላይ እንዳሴርን እንቆጠራለን” የሚል ሲሆን ፤

ሁለተኛው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ አባባል ሲሆን “ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው። ተጎጂዎችን ነፃ ለማውጣት እና ይህን ወንጀል ለማስቆም ትግላችንን አንድ ማድረግ አለብን” የሚለው ነው።

ክሆባኔ የሁለቱ ሰዎች ውግዘት እና በተግባር የታየ አቤቱታ የእርሷን እምነት እና ጥረት እንደሚያስተጋባ ተናግራለች።

“በእኛ አመለካከት ፥ በዓለም ላይ እየተካሄደ ያለው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በዚያ ጥቅስ ላይ እንዳሉት ፥ ኢፍትሐዊነት ብቻ ሳይሆን መቆም ያለበት ፥ የወንጀል ድርጊቶችም ጭምር መቆም አለባቸው” ስትል ተናግራለች። “የወሲብ ንግድ ፣ አጠቃላይ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ኢንዱስትሪው ፣ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት እና የሰብአዊ መብት ጥሰት እነዚህን ሁሉ የወንጀል ድርጊቶች ለማስወገድ ጠንክረን መስራት አለብን” ብላም አክላለች።

 ፍትሃዊነት ላይ የተመሰረተ ብዝበዛ

ደቡብ አፍሪካ አህጉሪቱ ውስጥ ካሉ ሃገሮች እጅግ የበለጸገች ሀገር ብትሆንም ፥ ታሪኳ የተመሰረተው በቅኝ አገዛዝ እና በአፓርታይድ ስለሆነ ፥ ያለፈው የግፍ ቁስአሁንም እያመረቀዘ በመምጣቱ ፥ በድሃው እና በሃብታሙ መሃል ባለው ሰፊ ልዩነት ምክንያት ፍትህ እጦት እና በእኩልነት ጥያቄ በሚሰቃዩ እንዲሁም የብዝበዛ ሰለባ በሆኑ ህዝቦች የተሞላች ሃገር ናት።

በተጨማሪም ከድህነት ፣ ከግጭት እና ከአየር ንብረት ቀውስ ለሚሰደዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ስደተኞች የመዳረሻ (እና መነሻ) ወደብ ነች። ክሆባኔ እንዳረጋገጠችው ፥ እነሱም ፥ ስደተኞቹን ማለቷ ነው ፥ ለሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች በጣም የተጋለጡ እንዲሁም የወሲብ ንግድ ሰለባዎችናቸው ብላለች።

ክሆባኔ በማከል “ደቡብ አፍሪካ የህገወጥ አዘዋዋሪዎች ኢላማ ናት ፥ ከብዙ ሃገራት የሚመጡ ሰዎች ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት ለመሸጥ ሲሉ መዳረሻቸው እና መውጫቸው ጭምር ናት” ስትል ተናግራለች።

በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ደቡብ አፍሪካ የሕገወጥ የሰአዘዋዋሪዎች መዳረሻ እና መውጫ መንገዶች አንዷ መሆኗን የአሜሪካኑ የተራድኦ ድርጅት የሆነው ኤ አይ ዲ ይፋ ያደረገውን ዘገባ አስታውሳለች።

“ሕገወጥ የሰአዘዋዋሪዎቹ እንደሚሉት ፥ ህጉ ልል እና ደካማ ከመሆኑ የተነሳ ፥ በደቡብ አፍሪካ አንድሰው ለማስወጣት በጣም ቀላል ነው ይላሉ ፥ ስለዚህ ለመግባትም ሆነ ለመውጣት በጣም ቀላል ነው” ብላለች ክሆባኔ።

የወሲብ ንግድን ህጋዊ ለማድረግ ያቀደው ሰነድ

የደቡብ አፍሪካ የህግ አውጭዎች በአሁኑ ጊዜ የወሲብ ንግድን ህጋዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ነው ፥ እንደ ክሆባኔ ገለጻ ከሆነ ፥ ይህ ደግሞ ብዙ ሰዎችን ለሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ተጋላጭ ያደርጋል።

“ምንም እንኳን መንግስት የወሲብ ንግድን ህጋዊ ለማድረግ ደህንነቱ የተጠበቀ መንገድ እንደሆነ እንድናምን ቢፈልግም ፥ ተጋላጭነታቸውን ግን ይበልጥ እያሳደጉት እንደሆነ ማወቅ አለባቸው” ስትል አስጠንቅቃለች።

በዚህ ጉዳይ ላይ ተጋላጭነቱ ምን ያህል እንደሆነ ስትገልፅ ፥ ከድህነት እና ከስራ አጥነት ጋር ተያዘው ያሉት ተጋላጭነታቸው ከ30-40 በመቶ ሲሆን ፥ አጠቃላይ የወጣቶቹ ደግሞ ከ60-65 በመቶ እንደሆነ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ያመላክታሉ ብላለች።

ከዚህም መረጃ እንደምናስተውለው በህገወጥ የሰአዘዋዋሪዎች በጣም የሚፈለጉት ወጣቶች እንደሆኑ እና ይህ ሁሉ ከወሲብ ንግድ ጋር ሲያያዝ ከባድ ችግር ይፈጥራል ብላለች።

 ክብርን ማስጠበቅ’

ፒንኪ ክሆባኔ የ ‘ክብርን ማስጠበቅ’ ተልእኮ እና ሥራን ስታብራራት ፥ ቡድኗ ያለፉትን ሶስት እና አራት ዓመታት ያሳለፈው “ሴተኛ አዳሪነትን ሕጋዊ ከማድረግ የተለየ አማራጭ እንዳለ ለመንግስት ለማሳየት በመሞከር ነው” ብላለች።

 “የእኛ አመለካከት በዚህ ድርጊት የሚሳተፉትን ደላላዎች እና የሆቴሉ ባለቤቶቹን ወንጀለኛ አድርጉ የሚል ነው። ወንጀለኞቹ እነዚእንጂ ሴቶቹ አይደሉም” ትላለች።

“ነገር ግን ይህን ህጋዊ ማድረግ’’ ትላለች ክሆባኔ “ሁሉም ሰው ከወንጀሉ ነፃ ማድረግ ማለት ነው ፥ ይህ ደግሞ ንግዱን ማን እየመራው እንደሆነ ለማወቅ ያዳግታል” ስትል አስረድታለች።

“ክብርን ማስጠበቅ” በተጨማሪም “ከዚህ ሥራ የተረፉትን ሴቶች በምግብ የምንረዳበት ፣ የኤችአይቪ ምክር የምንሰጥበት ፣ እና አሁን ለመመስረት ያሰብነውን “የስብእና እርሻ” የምንለውን እና ሴቶች የራሳቸውን ምግብ አምርተው የሚጠቀሙበትን ዘዴ የምናስተምርበት እና የምክር አገልግሎት የምንሰጥበት ተቋም ለመመስረት አንድ እርምጃ ወደ ፊት ወስደናል።

እነዚህም ድርጅቶች የተቋቋሙት ከዚህ ህገወጥ ሥራ የተመለሱ ሰዎች የራሳቸው ገቢ እንዲኖራቸው የሚያስችላቸውን ክህሎት የሚማሩበት እና ሁሉንም ነገር ወደ ኋላ ትተው ህይወታቸውን እንደገና እንዲጀምሩ የሚያስችላቸው ሁለንተናዊ ማዕከላት እንዲሆኑ በማሰብ ነው።

የዚህ “ክብርን ማስጠበቅ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ተቋም መስራች የሆነችው ክሆባኔ “ወደ ሴተኛ አዳሪነት የሚመራውን ህገ ወጥ የሰው ዝውውርን ጨምሮ በዓለማችን ላይ የሚደረጉ መጥፎ ተግባራትን በመቃወም የሚታወቁትን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን በተለየ ሁኔታ በማመስገን ፥ ብጹእነታቸው ደጋግመው የሚናገሩትን “ይህ የተደራጀ ወንጀል ነው!” የሚለውን ንግግር ፒንኪ ክሆአባኔ በድጋሚ በማስተጋባት ፥ ለእሳቸው እና በዓለም ላይ ላሉ ግፍ እና ኢፍትሃዊነትን በመቃወም ለሚናገሩት ሌሎች ሰዎች ሁሉ ምስጋናችን ይድረሳቸው በማለት ሃሳቧን አጠቃላለች።

24 May 2023, 15:22