ፈልግ

Ukrainian serviceman looks on inside a tank at a position near a frontline in Zaporizhzhia region

ለዩክሬን የሚሰጡት የጦር አውሮፕላኖች ውጥረቱን አባብሰውታል ተባለ!

ምንም እንኳ ከሞስኮ ማስጠንቀቂያ እና ይህ ድርጊታቸው ጦርነቱን እንደሚያባብሰው ቢነገራቸውም ፥ ስሎቫኪያ እና ፖላንድ የጦር አውሮፕላኖችን ለዩክሬን ጦር እንደሚሰጡ አረጋግጠዋል። በተመሳሳይ ጊዜ ፥ በጦርነቱ ቀጠና አቅራቢያው የምትገኘው ሃንጋሪ ፥ የኔቶ ወታደራዊ ህብረት መስፋፋት ላይ የምትሰጠውን ድምጽ እንደገና ለሌላ ጊዜ አስተላልፋለች ፥ ይህም በአራቱ በመካከለኛው እና በምስራቅ አውሮፓ ሀገራት መሃከል ውጥረት እንዲፈጠር አድርጓል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ አዲስ አበባ

የስሎቫኪያ ጠቅላይ ሚኒስትር አገራቸው ፖላንድ የወሰደችውን ተመሳሳይ እርምጃ በመከተል ፥ በሶቪየት ሕብረት ዘመን የተሰሩ ከ12 በላይ የጦር አውሮፕላኖችን ለዩክሬን እንደምትሰጥ አረጋግጠዋል። እነዚህ የጦር ጄቶች ምንም እንኳን እድሜ ጠገብ ቢሆኑም አሁንም ተፈላጊነታቸው አልቀነሰም።

ጠቅላይ ሚንስትር ኤድዋርድ ሄገር ፥ መንግስት 13 ሚግ-29 አውሮፕላኖችን እና የአየር መከላከያ ስርዓትን ለዩክሬን ለማቅረብ በአንድ ድምፅ ወስኗል ብለዋል። ይህን በማድረጋቸው ከተለያየ አቅጣጫ ትችቶች ቢደርስባቸውም ፥ “በሕገ መንግሥታችን መሠረት ነው ይሄን ውሳኔ የወሰነው” ብለዋል።

እርምጃው የተወሰደው ፖላንድ የዩክሬን አብራሪዎች ለመብረር የሰለጠኑበትን አራት ሚግ-29 የጦር አውሮፕላኖችን ለመላክ ቃል ከገባች ከአንድ ቀን በኋላ መሆኑ ታውቋል። ስሎቫኪያ እና ፖላንድ እነዚህን ተዋጊ ጄቶች ለመስጠት የወሰኑት ፥ ሩሲያ ለዩክሬን ከአጋሮቿ የሚሰጧትን ማንኛውንም የጦር አውሮፕላን እንደምትመታ ማስጠንቀቂያ ከሰጠች በኋላ ነው።

ይህ እርምጃ ፥ ስሎቫኪያ፣ ፖላንድ፣ ቼክ ሪፐብሊክ እና ሃንጋሪን ያቀፈው ፥ የፖለቲካ እና የባህል ጥምረት በሆነው በ ‘ቪሴግራድ ቡድን’ ውስጥ ውጥረትን አስፍኗል። ከአራቱም ሀገራት ሃንጋሪ ከሩሲያ ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዳላት ይታመናል። በመሆኑም የተኩስ ማቆም እና የሠላም ንግግርን እመርጣለሁ በማለት ምንም አይነት መሳሪያ ለዩክሬን ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነችም። በተጨማሪም ሃንጋሪ በሞስኮ ላይ የተጣሉ በርካታ ማዕቀቦችንም መቃወሟን አስታውቃለች።

የሰሜን አትላንቲክ የቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) መስፋፋት

ከቱርክ በተጨማሪ ሃንጋሪ አሁንም ኔቶ ፊንላንድን እና ስዊድንን በማካተት ወታደራዊ ህብረቱ እንዲስፋፋ ያላፀደቀች ብቸኛዋ የአውሮፓ የኔቶ አባል ሀገር ነች። የሃንጋሪ ዋናው ገዥ የሆነው ፊደስ ፓርቲ ፥ ከብዙ የቀን ማራዘም በኋላ በጉዳዩ ላይ ድምጽ ለመስጠት እ.ኤ.አ. መጋቢት 31 ላይ ተዘጋጅቷል።

አንዳንድ የሃንጋሪ ህግ አውጪዎች በስዊድን እና በፊንላንድ የኔቶ አባልነት ጥያቄዎችን መደገፍ አለመቻሉን በተመለከተ ጥርጣሬን አንስተዋል ፤ ይህም ከስቶክሆልም እና ከሄልሲንኪ የሚነሱትን የሃንጋሪ የህግ የበላይነት እና የዲሞክራሲ ደረጃዎች ጥሰትን በተመለከተ “ግልጽ ውሸት” የሚሉትን በመጥቀስ ነው።

የሚገርመው ነገር የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ሀገራቸው የፊንላንድን የአባልነት ጥያቄ እንደምትቀበል አርብ ዕለት አስታውቀዋል። የፖለቲካ ሽኩቻው በቀጠለ ቁጥር በዩክሬን ያለው ደም መፋሰስም እንዲሁ እየተጠናከረ ይሄዳል። በተጨማሪም በሄግ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ ፈፅመዋል ባለው የጦር ወንጀሎች ምክንያት የእስር ማዘዣ ማውጣቱ ፥ የፕረዚዳንቱን የጉዞ እቅድ ሊያወሳስበው ይችላል ተብሏል።

ባለፈው አመት የካቲት ወር ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች እና ሲቪሎች ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል ተብሎ ሲታመን ፥ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

 

 

 

20 March 2023, 10:48