ፈልግ

የሚያንማር ፖለቲካ እና ወታደራዊ ኃይል የሚያንማር ፖለቲካ እና ወታደራዊ ኃይል 

የሚያንማር ወታደራዊ መሪ፣ ሁሉንም የተቃውሞ ድምጾች ለማጥፋት ዛቱ

የሚያንማር ወታደራዊ ገዢ ወይንም ጁንታ ፥ የጦር ሃይሎች ቀንን ባከበረበት ቀን ‘አሸባሪ’ ብሎ በሚጠራቸው ተቃዋሚ ቡድኖች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ እና በአምባገነንነት አገዛዝ ፣ በአመጽ እና በኢኮኖሚ ለተንኮታኮተችው ሃገር ፥ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ፥ በሀገሪቱ ላይ የወታደራዊ አገዛዝ ህግ እና ቁጥጥርን ተግባራዊ አደርጋለሁ ብሎ መዛቱ ተነግሯል።

የዘገባው አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ፤  አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

እ.አ.አ. በየካቲት 1/2021 በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን የአንግ ሳን ሱ ኪን መንግስት ከገለበጠው መፈንቅለ መንግስት በኋላ ሶስተኛው የሆነው ይህ ወታደራዊ ሃይል ፥ የሀገሪቱን የጦር ሃይሎች ቀን ለማክበር በመቶዎች ከሚቆጠሩት ወታደሮች ጋር በሚያንማር ዋና ከተማ ናይፒዳው አስደናቂ የጦር መሳሪያ ትዕይንት ትላንት ሰኞ ዕለት አሳይቷል። ከዚያን ጊዜ ማለትም ከ2021 መፈንቅለ መንግስት ጀምሮ ከ17,000 በላይ ሰዎች ታስረዋል ፤ ከእነዚህ ዉስጥ 13,689 በእስር ላይ እንደሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ ማህበር አስታውቋል።

የወታደራዊ አገዛዙ ወደ 3,000 የሚጠጉ ሰዎችን ገድሏል ፥ ይህም ቁጥር የዲሞክራሲ አቀንቃኝ ሆነው በወታደራዊ እርምጃዎች በጥይት ተገድለው የታወቁት ብቻ ሲሆን ፥ ሰራዊቱ በሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች ላይ ባደረሰው ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል። በሀገሪቱ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ልዩ ዘጋቢ ባለፈው ዓመት ብቻ ከ13,000 በላይ ህጻናት ተገድለዋል ብሏል።

በአናሳ ማህበረሰቦች ላይ የሚወሰደው ጥቃት

የጁንታው መንግስት በአናሳ ሀይማኖቶች እና በርማ ያልሆኑ ብሄረሰቦች ላይ ያለው ግልጽ ጥላቻ እና የሚያደርሰው ጥቃት ፥ አብዛኛውን ሙስሊም ሮሂንጊያዎችን ወደ ባንግላዲሽ እና ታይላንድ እንዲሰደዱ ያደረገ ሲሆን በክርስቲያኖች ላይ ደግሞ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን አስከትሏል።

በዚህም የተነሳ ቢያንስ 1.3 ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቅለዋል ፥ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ፈርሰዋል ፥ በደርዘን የሚቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናትም ወድመዋል። ከመፈንቅለ መንግሥቱ ወዲህ ፥ ባለፈው ዓመት የተገደሉትን ሁለት የዴሞክራሲ አቀንቃኝ የፓርላማ አባላትን ጨምሮ ፥ ከ140 በላይ ሰዎች የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸዋል ፥ እንዲሁም የብሔራዊ የዲሞክራሲ ሊግ መሪ የሆኑት አውንግ ሳን ሱ ኪ የ33 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል። ለእምነት ነፃነት እና ለሰብአዊ መብቶች በሚያቀነቅኑ ሰዎች እና የክርስቲያን መሪዎችን ጨምሮ ፥ በድብቅ እና ዝግ በተካሄዱ ሚስጥራዊ የፍርድ ሂደቶች በኋላ በርካቶች በእስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ድምፅ

ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ፣ የሚያንማር ብፁዕ ካርዲናል ቻርለስ ቦ እና ሌሎች ጳጳሳት ምንም እንኳ ምላሽ ባያገኝም ፥ የሠላም እና የውይይት ጥሪዎችን በተደጋጋሚ አቅርበው ነበር። በዚህ ዓመት መፈንቅለ መንግስቱ በተከበረበት ዋዜማ ላይ የሚያንማርማር ከተማ የሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳሳት እና የመንደሌይ ሊቀ ጳጳስ ማርኮ ቲን ዋን ፣ የታውንጊ ሊቀ ጳጳስ ባሲልዮ አታይ ፣ ከካርዲናል ቦ ጋር በመሆን ለሠላም መደፍረስ እና የህይወት መጥፋትን እንዲሁም ማህበረሰቦች ሠላም እና እርቅ የሚሹባቸው ማምለኪያ ቦታዎች እና ገዳማት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በማውገዝ የሰላም ጥሪ አቅርበዋል።

በስቃይ ውስጥ ያለ ህዝብ

የሰኞው ዕለት ወታደራዊ ትርኢት እና የጦር መሪው በሁሉም ተቃዋሚ ቡድኖች እና ተቀናቃኞች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የገባው ቃል በአሜሪካ መንግስት በኩል "በህዝቡ ላይ በደል እና ስቃይ በማድረስ" በሚል አዲስ ማዕቀብ ሊጣልባት ይችላል እየተባለም ነው።

ሚያንማር እ.ኤ.አ. በ 1948 ነፃነቷን ከተጎናጸፈች በኋላ ፥ ከጥቂት የነፃነት ጊዜ በስተቀር ህዝቦቿ ለ76 ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት እና ለአስርት አመታት ጭካኔ የተሞላበት ወታደራዊ አምባገነን አገዛዝ ስር ያሳለፈ ህዝብ ነው።

28 March 2023, 17:05