ፈልግ

ፍቅር ጽኑ ናት! ፍቅር ጽኑ ናት!  (ANSA)

“የሕይወት ትውስታ!”

በአንድ ወቅት ሁሉም ዓይነት ስሜቶች በኅብረት የሚኖሩባት ገለልተኛ ደሴት ነበረች። ደስታ፣ ሐዘን፣ እውቀት፣ ቁጣ፣ ሃብት፣ እምነት እና ፍቅርን ጨምሮ አብረው በደሴቷ ይኖሩ ነበር። አንድ ቀን ደሴቷ ልትሰምጥ እንደሆነ ስለተሰማቸው ሁሉም በተቻለ ፍጥነት ደሴቲቱን ለቀው መውጣት አልያም ሰምጠው መሞት ነበረባቸው።

ሁሉም ስሜቶች በተቻለ ፍጥነት ለመልቀቅ ጀልባዎቻቸውን በፍጥነት ማዘጋጀት ጀመሩ።  እስከ መጨረሻው እስከተቻላት ድረስ ለመቆየት የወሰነችው ፍቅር ብቻ ነበረች። ደሴቷ ልትሰምጥ ስትቃረብ እና ፍቅር መልቀቅ ስትፈልግ፣ ጀልባ ስላልነበራት የምትሆነው ጠፋት። ፍቅር ጨንቋት እርዳታ ለመጠየቅ ወሰነች። ሃብት በጣም በሚያምር ጀልባው እያለፈ አይታው፦ “ሃብት ሆይ! ከአንተ ጋር ልትወስደኝ ትችላለህ?” ስትል ጠየቀችው። ሃብትም እንዲህ ሲል መለሰላት፡- “አይ፣ አልችልም። በጀልባዬ ውስጥ ብዙ ወርቅ እና ብር አለ፤ እና በሚያሳዝን ሁኔታ ለአንቺ የሚሆን ምንም ቦታ የለም” ብሏት መንገዱን ቀጠለ። ቀጥሎም ፍቅር ሐዘንን አየችውና እሱም እንዲሁ በሚያምር ጀልባ ሆኖ እያለፈ ነበር። “ሐዘን ሆይ! እባክህ እርዳኝ!” ስትል ፍቅር ተማጸነች። ሐዘን ድብርት በተጫጫነው ስሜት እንዲህ ብሎ መለሰ፣ “ኦ…ፍቅር፣ በጣም አዝናለሁ፤ እኔ ብቻዬን መሄድ እመርጣለሁ!” ደስታም እንዲሁ በፍቅር በኩል አለፈ፤ ነገር ግን በጣም በደስታ ውስጥ ስለነበረች ፍቅር ሲትጠራት ምንም አልሰማችም!

ከደሴቲቱ ጋር ለመስመጥ ተቃርቦ ሳለ በድንገት “ነይ ፍቅር፣ እኔ እወስድሻለሁ” የሚል የአረጋዊ ድምፅ ሰማች። ታድጓት በጀልባው ይዞ ወደ ደረቅ መሬት ካደረሳት በኋላ መንገዱን ቀጠለ። ፍቅርም በተደረገላት ውለታ ተገርማ እና ተደስታ የሽማግሌውን ስም ለመጠየቅ፣ ሌላ ሽማግሌ የሆነውን ጥበብን “ሕይወቴን የታደገኝ ማን ነበር?” ብላ ጠየቀችው። “ጊዜ ነበር!” በማለት ጥበብ መለሰላት። “ጊዜ? ግን ጊዜ ለምን ረዳኝ?” በማለት ፍቅር ጠየቀች። ጥበብ ፈገግ አለና በርህራሄ እንዲህ ብሎ መለሰ፡- “ፍቅር ምን ያህል ዋጋ እንዳላት የሚረዳው ጊዜ ብቻ ነው።”

ታዋቂዋ የዓለም ሃብታም ዲዛይነር እና ጸሐፊ ክሪስዳ ሮዲሪጌዝ በካንሰር በሽታ ከመሞቷ በፊት ማስታወሻዋ ላይ እንዲህ ብላ ፅፋ ነበር!

1. በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ ውድ መኪናዎች ውስጥ አንዱ በኔ ገራጂ የተቀመጠ ነው። አሁን ግን በዊልቸር ነው የምንቀሳቀሰው! 2. ቤት ውስጥ በምርጥ ዲዛይነሮች የተሰሩ ውድ የሆኑ የሚያምሩ ልብሶች እና ጫማዎች አሉኝ! አሁን ግን ከሆስፒታል በተሰጠኝ ስስ ጨርቅ ነው ገላዬን የሸፈንኩት! 3. ባንክ አካውንቴ ላይ ከበቂ በላይ ገንዘብ አለኝ ግን እሱን አሁን ልጠቀምበት አልችልም! 4. ቤቴ ፓላስ የሚባል ዓይነት ነው ግን እኔ አሁን ሆስፒታል ውስጥ በምትገኝ ትንሽዬ አልጋ ላይ ነው የተኛሁት! 5. ካንዱ ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴል እንዳሻኝ ወደ ሌላው ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል እንሸራሸር የነበርኩ ሴትዮ አሁን እዛው ሆስፒታል ውስጥ ካንዱ የላቦራቶሪ ክፍል ወደ ሌላኛው ላቦራቶሪ ክፍል መመላለስ ግዴታዬ ነው! 6. በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ፈርሚልን ብለው እንዳላስጨነቁኝ አሁን ግን የሚያክመኝ ዶክተር እንኳን አንድም ቀን ፊርማዬን ጠይቆኝ አያውቅም! 7. ፀጉሬን የማስውብበት ውድ የተባሉ ሰባት ዓይነት አልማዞች እና ወርቆች ነበሩኝ፤ አሁን ግን ይህንን ማድረግ አልችልም ምክንያቱም ፀጉር የለኝም! 8. በግል አውሮፕላኔ ዓለም ላይ የፈለኩበት ቦታ ብቻዬን መሄድ እችል ነበር፤ አሁን ግን ለመናፈስ ስፈልግ እንኳን የግድ የሁለት ሰዎች እርዳታ ያስፈልገኛል! 9. ቀን በቀን በብፌ የተዘጋጁ የተመረጡ ምግቦችን እመገብ ነበር፤ አሁን ግን በቀን ሁለት ፍሬ ታብሌት እና ትንሽ ጠብታ ጨው ነው ማታ የምወስደው! ይህ ሁሉ ሃብት እና ድሎት ግን እኔን ከበሽታዬ ሊያድነኝ አልቻለም! እውነተኛ ሕይወት ማለት ከፈጣሪ ጋር መኖር፣ ለትዕዛዛቱም መገዛት ነው። ሕይወት አጭር ናት! ሳትቀድማችሁ ቅደሟት።

በአካል መኖር ብቻውን ኖሯል አያስብልም። ህያው የሚያደርገን ራእይና የመኖር ዓላማ እንጂ ቆሞ መሄድ አይደለም። ቆሞ ለመሄድ በአራት እግር አህያም ይሄዳ። አህያ ግን የሰውን ሥራ ከማቅለሉ ውጪ የራሱ ራዕይ የለውም። ስለሌለውም የሌሎች ባሪያ ሆኖ ይኖራል።

በሰው ራእይና ዓላማ የለሽ ሕይወት፣ ሕይወት ሳይሆን ሞት ነው። ዓላማ የሌለው ሰው ለመቀበር ነፍሱ ከስጋው እስክትነጠል ይጠበቃል እንጂ ሙትማ ሙት ነው። ከዓላማ ውጪ የሚኖር ሕይወት ከሕይወት አይቆጠርም። ዓላማ ቢስ ወይም ከባለራዕይነት ወደ ዓላማ የለሽነት የመጣ ሰው ኖሯል ለማለት ከባድ ነው።

የሰው ልጅ ትናንት በበላው ብቻ ዛሬ አይኖርም። ትናንት አዲስ ብሎ የገዛው ጨርቅ ዛሬ ይሠለቸዋል። በአሮጌ ልብስ አይዘነጥም። ባረጀና ባፈጀ ሃሳብም ሕይወትን ማሳመር አይቻልም። ለዓመት በዓል በተበላ ምግብ አመቱን ሙሉ አይረካም። ያለፈው እርካታ ያለፈውን ጊዜ ነው የሚወክለው። የትናንቱ ጥጋብ ለዛሬ ዋስትና አይሰጥም። የትናንትናው እንጀራ የትናንቱን ረሃብ ነው የሚያስታግሰው። ለዛሬ ረሃቡ ዛሬም መመገብ አለበት።

ሰው ተፈጥሮው በየሰዓቱና በየዕለቱ የሚታደስና የሚለወጥ በመሆኑ ዘወትር ግብዓት ይፈልጋል። ሆድ በሰዓቱ የሚፈልገውን ካላገኘ ጥያቄ ያነሳል። ጥያቄውን መመለስ የሚቻለው በጊዜው የሚፈልገውን ማቅረብ ሲቻል ነው። በርግጥ ሰው ምግብ ሳይበላ ለቀናት ሊቆይ ይችል ይሆናል። ነገር ግን ቆይታው የስቃይ ነው የሚሆነው። ምግብ ያላገኘ ሰው መላ ሰውነቱ ይደክማል፤ ማሰብ ያቅተዋል፤ በእጆቹ ሊሠራቸው የሚፈልጋቸውን ሥራዎች በቀላሉ መሥራት አይችልም። አቅም፣ ጉልበትና ብርታት ያጣል።

የሰው ልጅ አዕምሮም እንደዛው ነው። በየቀኑ የሚፈልገውን አዲስ ሃሳብ፣ የተለየ መረጃና ዕውቀት ካላገኘ ይራባል። ማዕዱ ካልተሟላ ነፍስ ያው እንደተራበ፣ መንፈሱ እንደከሳ ዕድሜውን ይጨርሳል። ውስጣዊ ደስታው ይራቆታል። ማሰብ፣ መመራመር፣ ነገሮችን አብጠርጥሮ ማወቅ አይችልም። አቅሙና ጉልበቱ ድሮ በተመገበው ሃሳብ ብቻ ይወሰናል። ወደፊት አሻግሮ ማየት ይሳነዋል። ጊዜውን የሚዋጅ ሃሳብ ያጣል። ከዘመኑ ጋር መስተካከል ያቅተዋል። ነፍሱ ይመነምናል፤ መንፈሱ ይከሳል፤ አዕምሮው ይደክማል፤ ሚዛኑ ይዋዥቃል፤ አስተውሎቱ ይጠባል፤ አስተሳሰቡ ያንሳል፤ ዕይታው ይጭበረበራል። ዕውቀት የተራበ ጭንቅላት፤ ሃሳብ የታረዘ ሕሊና ለዓለሙ ያለው ምልከታ የተሳሳተ ይሆናል። ለፍረጃና ለጭፍን አመለካከት ይጋለጣል። በደረሰበትና በቆመበት የሃሳብ ሳጥን ብቻ ተወስኖ ሰፊውን ዓለም ሳይመረምርና ሳያውቅ በነሲብ ይደመድማል።

(እሸቱ ብሩ ይትባረክ)

18 March 2023, 17:03