ፈልግ

2023.03.25 Abrahamic Family House Abu Dhabi UAE (WAM-Emirates News Agency)

በአቡዳቢ የሚገኘው ‘የአብርሃም ቤተሰቦች ቤት’ የሚባለው ድርጅት ነዋሪዎችን ለአምልኮ እንዲጠቀሙ እቀበላለሁ አለ።

አብርሃሚክ ፋሚሊ ሃውስ ወይም በአማሪኛው የአብርሃም ቤተሰቦች ቤት የሚል አቻ ትርጉም የሚሰጠው ድርጅት ፥ የክርስትና፣ የአይሁድ እና የእስልምና እምነት ተከታዮች አቡ ዳቢ በሚገኘው ገነታዊ ጸጥታ በነገሰበት ስፍራው ማምለክ እንደሚችሉ እና ሃይማኖታዊ ውይይቶች ውስጥ መሳተፍ እንደሚችሉ አስታወቀ። ድርጅቱ እ.አ.አ. ከመጋቢት 1/ 2023 ጀምሮ ጎብኚዎችን መቀበል የጀመርው ሶስት የተለያዩ የአምልኮ ቤቶችን የሚያጠቃልል ስፍራ አዘጋጅቶ ሲሆን ፥ ከእነዚህም ዉስጥ ፥ መስጊድ፣ ቤተ ክርስቲያን እና ምኩራብ ይገኙበታል።

የእዚህ ዜና አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ አዲስ አበባ

በአቡ ዳቢ ውስጥ ፥ በሳዲያት የባህል አውራጃ ውስጥ የሚገኘው ፥ የአብርሃም ቤተሰብ ቤት የተመሰረተው በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ህዝቦችን እና ባህላዊ እሴቶቻቸውን አንድ ላይ ለማጣመር ታስቦ የተቋቋመ ድርጅት ነው። ይህ ስፍራም ከወዲሁ ከተለያዩ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ አመለካከት ላላቸው ሰዎች ማራኪ መዳረሻ ሆኗል።

ሳምንታዊ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች

የጁምዓ ሰላትን ጨምሮ ሁሉም ጸሎቶች በአሚነንስ አህመድ ኤል-ታዬብ መስጂድ ይካሄዳሉ። ቅዳሴ በእንግሊዘኛ ዘወትር እሁድ ከቀኑ 6፡00 ሠዓት ላይ በቅዱስ ፍራንቸስኮ ቤተ ክርስቲያን ይካሄዳል። ዕለታዊ አገልግሎቶች ደግሞ በሙሴ ቤን ማይሞን ምኩራብ ውስጥ ይከናወናሉ ተብሏል።

እያንዳንዱ ሕንፃ ከ200 እስከ 350 ምእመናን የማስተናገድ አቅም ያለው ሲሆን ፥ ጎብኚዎችም ጊቢው ዉስጥ ሲዘዋወሩ በአረብኛ ፣ በእንግሊዝኛ እና በዕብራይስጥ በተፃፉ ምልክቶች ይመራሉ ። ቦታውን ለመጀመሪያ ጊዜ ከጎበኙት የመገናኛ ብዙሃን መካከል የኢምሬትስ የዜና አገልግሎት (WAM) ከምእመናን ፣ ከጎብኝዎች እና ከሰራተኞች ጋር ቆይታ አድርጓል።

የሃይማኖቶች ውይይት ማዕከል

 ማዕከሉ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የመማሪያ እና የሃይማኖታዊ ውይይት ማድረጊያ ቦታ ነው። አስጎብኚዎችም በእንግሊዝኛ ወይም በአረብኛ ለጎብኚዎች ማብራሪያ የሚሰጡ ሲሆን ይህንንም አገልግሎት የሚሰጡት ያለ ክፍያ ነው።

ከሶስቱ የአምልኮ ቤቶች በተጨማሪ ፥ ደስ የሚል ካፌ፣ የቤተመፃህፍት ማዕከል እና የስጦታ መሸጫ ሱቅ ያካተተ ትልቅ የእንግዳ መቀበያ ቦታ አለው።

አከባቢው የሸንጎ ስፍራ ተብሎ እንደመጠራቱ ፥ ይሄንን አካባቢ የሚጎበኙ ጎብኚዎች ምኞታቸውን እና አላማቸውን እንዲጽፉ የሚጋበዙበት ‘የሃሳብ መግለጫ ግንብ’ የተባለ ግድግዳ አለ። በሶስት ማዕዘን ቅርጽ የተሰሩ ሰሌዳዎች ፥ በተለያዩ ቋንቋዎች በተፃፉ የፍቅር እና የሠላም መልእክቶች ተሸፍነዋል።

በጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ፕሬዝዳንት የልዑል ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም ፥የምክትል ፕረዚዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ፥ የዱባይ ገዥ ፣ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና የታላቁ የአል አዝሃር ኢማም ዶ/ር አህመድ ኤል ታዬብ በእብነ በረድ ላይ የተቀረፁ ፊርማዎች ይገኛሉ።

ሰላማዊ አካባቢ

ምንም እንኳን በዛ ያሉ ሰዎች በአከባቢው ቢኖሩም ፥ ግድግዳው ላይ የተሸፈነው ለየት ያለ የድምፅ መከላከያ መሳሪያ ፥ አካባቢውን ሠላማዊ አድርጎታል።

በሱቁ ውስጥ የሚሸጡ ዕቃዎች በሙሉ አብሮ የመኖር መልእክት ተፅፎባቸዋል ፥ ለአብነትም በሶስቱም ሃይማኖቶች ጥቅም ላይ የሚዉለው የሻማ መቅረዝ እና ኪፓ (በተለምዶ በአይሁድ ወንዶች የሚለብሱት ኮፍያ) በየሱቆቹ መግቢያ ላይ ይታያሉ።

ኒኮላ ኮስሞ የተባለው የስጦታ ዕቃ መሸጫው ሥራ አስኪያጅ ስለ ቦታው ሲገልጽ “ጎብኚዎቹ በቦታው በጣም ተማርከዋል ” ብሏል። “በእርግጥ ሰዎች በእንባ ሲያለቅሱ አይቻለሁ። ‘መቼም ቢሆን’ ይላል ኒኮላ ‘የቱሪስቶች ቡድን አውቶቡስ ሹፌር የሆነውን ፖላንዳዊ  ሰው መርሳት አልችልም ፥ ሰውዬው እዚህ ስፍራ አጠገቤ ተቀምጦ ነበር ፥ እየተንቀጠቀጠም ያለቅስ ነበር ፥ ምክኒያቱ ደግሞ ቤተሰቦቹ አይሁዳዊ እንደሆኑ እና ለግል ታሪኩ ትርጉም ያለው ቦታ ላይ በመገኘቱ ስሜቱ እንደተነካ አጫውቶኝ ነበር’ ብሏል ኒኮላ።

እራሷን ያለወላጆቿ ሥም የገለፀችው ማሪያ ፥ ለሁለተኛ ጊዜ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስን የጎበኘች ሩሲያዊት ቱሪስት ነች። ‘የሥነ ሕንፃውን ዘመናዊነት አደንቃለሁ ፣ ዘይቤው በተለይ ለወጣት ትውልዶች ማራኪ ነው። ማህበራዊ ሚዲያን እጠቀማለሁ ፥ ቦታው በጣም ማራኪ እና አስተማሪ ስሎሆነ ዛሬ ብዙ ፎቶዎችን አንስቼ ለመልቀቅ ወስኛለሁ ፥ በአሁኑ ጊዜ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ሥዕሎቼን በስቶሪዎቼ ላይ አድርጌ እንደ ጠንካራ የሠላም መልዕክት እጠቀማለሁ’ ብላለች ማሪያ።

አስደናቂ ሥነ ህንጻ

 በአቡ ዳቢ የምትኖረው ፈረንሳዊት ኮሪን ኤስ በበኩሏ “በጣም ግሩም ነው ፥ ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ ነገር ነው። ከአምዶች ባሻገር ምን እንደሚኖር ለማወቅ ጓጉቼ ነበር። ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ ሁሉም ነገር በጣም ደስ የሚል እና ሰላማዊ እንደሆነ ይገነዘባሉ ፥ በእቅፍ ዉስጥ እንዳሉም ይሰማዎታል’ ትላለች።

ሌላኛዋ በአቡ ዳቢ የምትኖረው ጣሊያናዊቷ ሴሬና ሲ ስለ ቦታው ማራኪነት ምስክርነቷን ስትሰጥ ፥ ‘በአትክልቱ ስፍራ ስትዘዋወር ሁሉም ሰው በሠላም አብሮ የመኖር ህልም እዉን ሲሆን እያየች እንደሆነ እንደተሰማት’ ተናግራለች።

“ቀጥተኛ መስመሮች ፥ በጣም ዝቅ ያሉ ፥ ግን በተመሳሳይ ጊዜ ታላቅ እና ግርማ ሞገስ ያለው ፥ ፀጥታውን እና ዝምታውን የሚያቋርጠው የወፎቹ ጫጫታ እና የነፋሱ ድምፅ ብቻ ነው ፥ እንዲሁም በሥነ ሕንፃው ውስጥ የቀለም አለመኖር የሚያሰክን እና የሚያረጋጋ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ፥ በመሆኑም የዛፎቹን አረንጓዴነት፣ የውሃውን ሰማያዊነት የበለጠ እንዳስተውል እና እንዳደንቅ አድርጎኛል” ትላለች።

 መንፈሳዊ ግንኙነት

በቤተክርስቲያኑ የመጀመሪያ ረድፎች ላይ ተቀምጦ የነበረው በአቡ ዳቢ በነዳጅና በጋዝ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚሠራውን እና ከአርጀንቲና ሮዛሪዮ ግዛት የመጣውን ወጣት መሐንዲስ አሌሃንድሮ ኤም በበኩሉ ፤ "በእኛ ቤት ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንቺስኮስን በጣም እንወዳቸዋለን ፥ እሳቸው እንደ እኔው የአርጀንቲና ተወላጅ ናቸው ፥ እናም እንደ አንድ የቤተሰቡ አካል ነው የምናያቸው ፥ እዚህ ስመጣ ለመጀመሪያ ጊዜዬ ነው ፥ ጉብኝቴን ለመጀመር የፈለኩት በአሁኑ ሰአት ታሞ ላለው አባቴ በመጸለይ ነው” ሲል ተናግሯል።

ይህ ‘የአብርሀም ቤተሰብ ቤት’ የተባለው ሥፍራ ለተለያዩ የአቡ ዳቢ ማህበረሰብ እና ለተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ጎብኝዎች የመረጋጋት፣ የመንፈሳዊ ትስስር እና የመማሪያ እንዲሁም የውይይት መለዋወጫ ቦታ ሆኖ እያገለገለ እነደሚገኝ ታውቋል።

 

 

 

 

27 March 2023, 21:11